
By Admin
ትላንትና፦ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በህዝብ ተውካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ያስተላለፉትን መልዕክት አዳምጬ ሳበቃ፥ ኣንድ ነገር ግን አልዋጥልህ አለኝ። “ታዲያ ለምን እሳቸው አዘነብነው ባሉት ዝናብ አርሰህ ልታኝከው አልሞከርክም?” ብላችሁ እንደማትቀልዱብኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ዝናብን በartificial ደመና ማዘነብ ያረጀ – ያፈጀ፥ በማደግ ላይ ናቸው የሚባሉት የAsia ሀገራት እንኳ ሳይቀር ከሁለት ኣሥርት ዓመታት በፊት የተጠቀሙት ሳይንሳዊ ዕድገት ቢሆንም፤ የሀገራችን መልካ ምድር ለዚህ ሰው ሰራሽ ጠብታ መብቃቱ፥ ተመስገን የሚያስብል፣ የምናናንቀው ሳይሆን የምናደንቀው ኣንድ እመርታ ነው። አለበለዚያ ግን … ወየው ለአንተ! መንግስትን ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ብለህ ስትጋፋ የዶፍ ናዳ ለሚወርድብህ።
ጦርነት፦ እንዲህ ህፃናት ጭቃ ተቀብተው የሚጫወቱት ጨዋታ እንዳልሆነ ባውቅም፤ ጦረኛነትን ግን አልቃወምም። ይህን ደግሞ የምለው፥ እንደ Dracula የሰው ደም ተጠምቼም አይደለም። እንኳን አሁን፦ ጦርነት የሰው ነፍስ እንደሚበላ በማውቅበት ዕድሜ ቀርቶ፥ ድሮም ቢሆን ልጅ እያለሁ፦ በሰው የሚበላው ጦር ማስቲካም አምሮቴ ሆኖ አያውቅም። ነገር ግን፦ እንደ ኢትዮዽያ ላለ የውጭ ጠላት፣ የውስጥ ጥላሸት ሰርክ ለሚያውካት ሀገር፥ ጦረኛነት ብቸኛው፣ ፍትሐዊ የሀገርና የህዝብ ህልውና ማስጠበቂያ – የመሠረት ድንጋይ ነው። ጦረኝነት መርገምት የሚሆነው፥ ከትዕቢት ተወልዶ – በንቀት ሲፋፋ ብቻ ነው። ያኔ … “ጦርነት ባህላዊ ጭፈራዬ ነው” ያለ ነውረኛ፥ ወር ሳይሞላ፥ እንደ ናዝሬት በርሜል ምድር–ለምድር መንከባለል ባህላዊ የሀዘን ውዝዋዜው ይሆናል።
እናም ትላንትና … ጠቅላይ ሚንስትሩ “ጦረኝነቱ ከመሬት ላይ ሸሽቶ facebook ላይ መሽጓል፤ መቶ ሚልዮን ህዝብ በሚኖርባት ሀገር፦ ድንበር ጠባቂ ወታደር፣ ሰላም አስከባሪ ፖሊስ ማጣት ያሳፍራል” ሲሉ ብሰማ ግን አልዋጥልህ አለኝ። እውነት ለመናገር … ዛሬ ላይ ባለው እውነታ ያሚያሳፍረው፦ እነ አቶ እንደልቡን የመሳሰሉ ነውረኞች በሀገሪቱ ላይ ሾመው ጭንቅላቱ ላይ እያሸኑበት፣ መቶ ሚልዮኑን ህዝብ እንደ መቶ ብር፦ ቤተኛ እና “መጤ“፣ ጉራጌ እና ስልጤ – እያሉ በጎሳና ዘር እየዘረዘሩ፥ “ና! ለሀገርህ ሙት!” ብሎ መቀስቀስ ነው። በሰከንድ ሦስት ጊዜ የንጉስ ምኒሊክን ስም እንደ dumbbell ሲያነሳ፥ የምላሱ ጡንቻ አፉን አላዘጋ ያለው የኦዲፒ “ፖለቲከኛ“፥ ነጋ ጠባ “ነፍጠኛ” ፣ “ተስፋፊ” እያለ ህዝብ ሲገድል፣ ሲያስርና፣ ሲወርፍ ባልሰማ እያለፉ፤ ፓርላማ ማማ ላይ ተቀምጦ፦ መኖሪያ ሀገር አይደለም መሸሻ ጥሻ ያጣውን ዜጋ “ወታደር ሆኖ ለመቀጠር እምቢኝ አለ” ብሎ ለወቀሳ መነሳት ግብዝነት ነው።
ለእኔ እንደሚገባኝ፦ ወታደር ማለት በታረመ ትርጉም … ሀገር ለመጠበቅ ህይወቱን መስዋዕት አድርጐ የሚያቀርብ ዜጋ ነው። ምትክ–አልባ ህይወቱን መስዋዕት እንዲያደርግ ለሚጠየቅ ዜጋ ደግሞ አስቀድሞ ሀገር መስጠት ግድ ይላል። ሀገር ስል ደግሞ፦ አየርና አፈር ብቻ ሳይሆን አድሎ የሌለበት የዜግነት ክብርንም ይጨምራል። ምክንያቱም፦ የውትድርና ፍላጎት ቀመር ዋነኛ መሠረቱ ዜጎች የሚኖራቸው ያለተበላለጠ መብት ነውና። ሉዓላዊነትንም ለማረጋገጥ ወሳኙ የማዕዘን ራስ፥ ድንበር ላይ አጥር ሆኖ የሚቆመው ቃፊር ብዛት ሳይሆን መሬት ላይ ያለው ሀገራዊ መርሕ አቃፊነት ነው። ይህ ደግሞ የእኛ እና የዘንድሮ ተሞክሮ ብቻ ሳይሆን፥ ከጥንትም ቢሆን ሒደቱ እንዲሁ ነበር።
ከክርስቶስ ልደት በፊት፦ የፐርሺያ ንጉስ የነበረው ዳሪየስ (Darius) ግዛቱን ለማስፋፋት ባደረገው ውጊያ በግሪኮች ከፍተኛ ጥቃት ደርሶበት ተሸነፈ። በወቅቱ ግሪኮች የነበራቸው የህብረተሰብ አስተዳደራዊ ዘዬ ከሌላው የዓለም ክፍል እጅግ የረቀቀ ከመሆኑም ባሻገር፥ “ፓለቲካ” መኖር የሚችለው በህግ እና በህግ ጥላ ስር ብቻ ነው ብለውም ያምኑ ነበር። በአንፃሩ ደግሞ፦ ለፖለቲካ ዲዳ የነበረችው ፐርሺያ የነበራት ንጉሳዊ መዋቅር፥ እራሱን የባሪያዎች ገዢ እንጂ የህዝቦች አስተዳዳሪ አድርጐ አይመለከትም ነበር። እናም … ከዳርዮስ ሽንፈትና ህልፈት ቦኃላ በእግሩ የተተካው ልጁ ዜረክሲስ ( Xerxes)፥ የአባቱን ሽንፈት ለመበቀል በማሰብ ለዓይን የሚታክት ቁጥር ያለው ጦር አዘጋጀ። በወቅቱ በግዛቱ ውስጥ በስደት የሚኖረውንም የስፓርታን ንጉስ ዴማራተስን (Demaratus) ወደ ባህር ዳርቻ ወስዶ … “እናስ ምን ታስባለህ? ግሪኮች መቼም ደፍረው ይህንን ያኽል ጦር ለመዋጋት አይሞክሩም” አለው። ዴማራተስ ግን፦ “አትሳሳት … በእርግጥም በድፍረት ይዋጉሃል” ብሎ እንቅጩን ነገረው። ዜረክሲስም የዴማራተስን አስተያየት መቀበል ስላልፈለገ … “በምን ተዓምር ነው ኣመስት ሺህ ቢበዛ ደግሞ ኣስር ሺህ ግፋ ቢልም ሃምሳ ሺህ የሚሆነው የግሪክ ወታደር ደፍሮ ይህን ያህል ለቁጥር ከሚያዳግት ሰራዊት ፊት የሚቆመው? ያውም ኣንድ እንኳ ጌታ ሳይኖራቸውና እያንዳንዱ የራሱን ፈቃድ እንዲያደርግ ፍፁም ነፃ ሆኖ?” ሲል ደግሞ ጠየቀው።
ዜረክሲስ፦ ለውጊያ ድፍረት የሚኖረው ከኋላው በጅራፍ የሚገረፍ ወታደር እንጂ፤ ጌታና አለቃ የሌለው ሀይል፦ ግዙፍ ጦር እንደመጣበት ሲመለከት በፍርሃት ርዶ በየአቅጣጫው እንደ ቆሎ የሚበተን መስሎት ነበር ። ነገር ግን ዴማራተስ፦ “ነገሩ ፈፅሞ አንተ እንደምታስበው አይደለም። ግሪኮችን እኔ በደንብ አውቃቸዋለሁ፤ አንተ እራስህ እንዳላቸው ያመንክላቸውን ነፃነት ለመጠበቅ ሲሉ በድፍረት ይዋጉሃል! ለመሞትም ቁርጠኞች ናቸው” ሲል መለሰለት። ዴማራተስ ቀጠለ … “አዎ አንተ እንዳልከው ነፃ ናቸው፥ ግን ደግሞ ፍፁም ነፃ አይደሉም። አለቃ እና ጌታ አላቸው፥ ያም ጌታቸው ሕግ ነው። ግሪኮች ደግሞ ይህን ጌታቸውን፦ ወታደሮችህ አንተን ከሚፈሩህ በላይ አጥብቀው ይፈሩታል። የጌታቸውም ትዕዛዝ ከአንዱ ለአንዱ ፍፁም ስለማይለያይ፥ የሚያዛቸውን ማንኛውንም ነገር ከመተግበር ወደኃላ አይሉም። ይህ ህግ ደግሞ በወፍራምና ቀጭን፣ በትንሽና ትልቅ መካከል ልዩነት ሳያደርግ ኣንዲትን ነገር ብቻ ያዛቸዋል፦ የቱንም ያህል አስፈሪ የሆነ ጦር ቢመጣ ተደጋግፎ መዋጋትና ማሸነፍ አለበለዚያም መሞት” ሲል መለሰለት።
ታላቁ የታሪክ አባት ሔሮድተስ ( Herodotus) ደግሞ የዚያን ዘመን ግሪኮች የገለፃቸው እንዲህ ሲል ነበረ … እንደ ወረደ … ” They were citizens, not subjects, and free men, not slaves; they were disciplined but self-disciplined.” (On Politics: A History of Political Thought from Herodotus to the Present.)
ጠቅላይ ሚንስትር ሆይ፦ ይሰሙኛል? ዜጋው ለውትድርና አገልግሎት ያለውን የእምቢተኝነት እንቆቅልሽ መፍታት ከተሳኖት፥ እኔ ልንገሮት። ግን ከዛ በፊት … ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለዜጋው በሙሉ ሀገር ይስጡ! ይሰማል?