Post

ለጥቂቶች የሚሞቱ ብዙሃን አይኖሩም!

ለጥቂቶች የሚሞቱ ብዙሃን አይኖሩም!

By Admin

ከጥቂት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከዛሬ ነገ ይዘንባል እየተባለ ሲጠበቅ ለደቂቃ እንኳ ሳያካፋ እንዲሁ እንደዳመነ አመታት ያስቆጠረውን የኢትዮ-ኤርትራን የጦርነት ደመና አስመልክቶ ሰጡ የተባለውን ወቅታዊ መግለጫ አዳመጥኩ። ባለፈው ሰሞን ያንን ምስኪን ህዝብ ከአባቱ ርስት፣ ከአያቱ ጉልት ሲያፈናቅሉት እያስፈቀዱት ይመስል “የኢትዮዽያን ህዝብ አስፈቅደን ጦር እንሰብቃለን ብለው ሲሳለቁ ታዝበን ዝም ባልን፣ ይባስ ብለው ዛሬ “የመንግስታችን ጥንካሬ ህዝባዊነቱ ነው … ለኣንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የማያዳግም ተግባር ፈፅመን እንወጣለን” አሉን። በቃ ሚኒስትሩ ድፍረት እና እፍረት እምቢ አሉ ማለት ነው?

አንዳንድ አንባቢዎቼ ሰውየው እፍረት ባይነካካቸውም ድፍረት ግን ጀምረዋል ብላችሁ፡ ከጥቂት ወራት በፊት ዘረኝነት እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቶ አስቸግሮናል ሲሉ ያማረሩባትን የፓርላማ ንግግር አንደ ዋቢ ትጠቅሱልኝ ይሆናል። እውነታው ግን- እንደ አገልጋይነታቸው፡ የዘር ባላባቶቹን ስጋትና ፍራቻ ነው ያስተጋቡት። አስፈላጊም ከሆነ፦ ለቀጣይ ህወሀት’ታዊ የዕርምት ዕርምጃ ፈር መቅደጃ በሉት። ደደቢት ጫካ ተረግዞ፡ ኣራት ኪሎ ቤተመንግስት የተወለደው ዘረኝነት፡ የአኖሌን ጡት ሲጠባ አድጎ፡ እንዲህ ሳይታሰብ በቶሎ መንጋጋ አብቅሎ ያጎረሰን ጣት ይነክሳል ብሎ ማን ጠብቆት? ዘረኝነት አረም ነው፤ ቤትም ይብቀል ጎረቤት መነቀል አለበት! ብዬ ባምንም፥ ጓሰኝነትን ከምንም ነገር በላይ አጥብቄ ብጠየፈውም፥ አንዲህ እንደ አሁኑ “ስራ ለሰሪው – እሾህ ለአጣሪው” ሆኖ ሳየው ግን ባልወደውም … 

ብቻ ግን- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ “ሀይላችን ህዝባችን ነው” ሲሉ ዘይቤአዊ በሆነ አማርኛ ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይን መጥቀሳቸው ካልሆነ በስተቀር መቼም ለኣንድ ክልላዊ መንግስት ሀይል የሚሆን ሀገራዊ ህዝብ አለ ብለው እንደማያስቡ እርግጠኛ ነኝ። ዛሬ ኢትዮጵያዊ የሆነው ወታደር ከዘረኛው የወያኔ መንግስት ጋር የሀገርን ሉዓላዊነት አስከብራለሁ ብሎ መታገል ማለት ፡ ወንድሙ ታስሮ ወፌ-ላላ የሚገረፍበትን የወህኒ-ቤት ደጃፍ ዘብ ቆሞ እንደመጠበቅ መሆኑን በሚገባ ተረድቶታል። ይህንን ጀግና እና ሀይማኖተኛ ህዝብ “ሀይላችን ነው” ብሎ ማጓራት- እናት እህቱ የሚደፈሩበትን ጫካ አጥር ሆኖ የሚያስከብር ነውረኛ ልጅ ወይንም ወንድም ነው ብሎ እንደመሳደብ ነው።

ታዲያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ “ለኣንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የማያዳግም ስራ ሰርተን እንወጣለን” ዛቻ ከየት መጣ? አውቶማቲክ ጠመንጃም ቢሆን እኮ የሚሸከመው ትከሻ፣ ቃታውን የሚስብለት ጣት ይፈልጋል። አውቶማቲክ ስለሆነ ብቻ እንዲሁ ከዱር – በረሃ፣ ከሜዳ – ገደል እየዘለለ በራሱ አይማርክም፣ አይገድልም፣ ዙፋንን አያደላድልም። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ያለ ህዝብ ድጋፍ ወደ ጦርነት መግባት እንጂ ከጦርነት መውጣት እንደማይቻል የረሱት መሰለኝ።

ትላንት የአይሲስ (ISIS) ካራ ወገኑን ሰይፎበት – “ኢትዮጵያዊነቱን እያጣራን ነው” ብለው ሲዘባበቱበት የተመለከተን ህዝብ፣ በቁሙ የነጠቁትን የዜግነት ክብር በሞቱ እንኳ ራርተው እንደማይሰጡት የተረዳን ወታደር፡ ዛሬ በምን ሒሳብ ነው ከጐኔ ቆሞ ይወይናል፣ ይቆስላል፣ ይሞታል ብለው የሚጠብቁት? ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፎከሩት ህዝብን ሳይሆን ህወሃትን ታምነው ከሆነ፡ መቼስ ምን እላለሁ – የሙት መንፈስ አይለዮት። ለምን ከከተማው ባቡር ለምርቃት ሲገቡ ብቻ፤ ከድንበሩም የጦር ሜዳ ለትግል ሲዘልቁ ይከተሎት እንጂ።

እንደው ነገርን ነገር ያነሳዋልና፡ ስለ ኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ሳወራ፡ ሰሞኑን ወደ ተፈጥሮአዊው ቀፎው የበረረው የአቶ ሞላ አስገዶም “መንጋ” የናዝሬት መስተንገዶ ዓይኔ ላይ ድቅን አለ። ያቺ የዋህ የኦሮሞ እህቴ በወፍራም እንጀራ ላይ ሙዳ ሙዳ ስጋ እየሰፈረች “ብላ … በሞቴ ተቀበለኝ” እያለች ስታግደረድረው አየሁና “አይ ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ ፤ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የተባለለት ያ ጀግና የአማራ አባቴ በላይ ዘለቀ ትውስ አለኝ። እንደው ያን ቀን ማታ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ምን በልቶ ይሆን ያደረው? 

ምን ያደርጋል … ጀግና ባልሆንም ጀግና ግን አውቃለሁ። ኣንድ ነፍሳቸውን በእጁ መዳፍ ላይ ያሳደሩ ጀሌዎቹን ቀድሞ የጫማውን ኮቴ ከጠላት አፈር ላይ ሲያሳርፍ ጀግና መሪ አውቃለሁ። የራሱን ነፍስ አቅድሞ፡ እንደ እባብ ምድር ለምድር ተስቦ አምልጦ ከፊት ለፊቱ ለተኮለኮሉት ጋጠ-ወጦች (ይቅርታ ጋዜጠኞች) “ቆይ ታያላችሁ ሰሞኑን የሚታሰሩና የሚገደሉ” አባሎች ይኖራሉ ብሎ በኩራት ሲደሰኩር ሳይሆን፤ በድልም ይሁን በሽንፈት ተከታዮቹን ሳይከዳ፡ ከጠላት ግዛት ከውጊያው ሜዳ ቀድሞ እንደገባ ቀድሞ ሳይወጣ፡ የቆሙትን በእግር፣ ቆስለው የወደቁትን በወሳንሳ አሻግሮ፡ ሁሉን አስቀድሞ ራሱን አዘግይቶ፡ የኮቴውን አሻራ መጨረሻ አትሞ ሲወጣ ጀግና አውቃለሁ“የቀሩት ሴቶች እና ህፃናቶች ብቻ ናቸው” ብሎ የእናት፣ የእህት፣ የሚስት፣ የልጅን ነፍስ እንደ አሮጌ ቆርቆሮ አራክሶ፣ ከጠላት እጅ ወርውሮ – ጥሎ ሲያመልጥ ሳይሆን፤ አቅመ ደካማዎችን አክብሮ፣ አላስነካም ብሎ ሲወድቅ – ሲዋደቅ ጀግና አውቃለሁ

ታዲያ ምናለ- አቶ ሞላ አስገዶም “የሻቢያን ሰራዊት ከውስጥ-ወደ-ውጭ ደምስሶ የወጣ” የተዋጣለት ጀግና ከተባለ፥ ታሪክ ራሱን ይደግማልና- እስቲ ዛሬ ደግሞ ከሰባት-ሞቶዎቹ (ይቅርታ ከሰባት-መቶዎቹ) ጋር ከውጭ-ወደ-ውስጥ ደርምሶ ይግባና ያስገርመና?

Comments are closed.