
By Admin
ከጥቂት ቀናት በፊት ከአሜሪካን ድምፅ የራዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ “መድረክ ምራልኝ ያለኝ አብይ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ደግ አደረኩ! ግጥም አድርጌ እደግፈዋለሁ!” ያሉት አቶ ደበበ እሸቱ፥ ዛሬ ደግሞ በኢትዮጵያ የኪነጥበብ ባለሞያዎች ማሕበር ስም “ህሊና-ቢስ ” ብለው አስክሬን ሲዘልፉ ብሰማ ይህቺን ትንሽ ፅሑፍ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ማስታወሻ ከትበኩ። ምናልባት “መግለጫ የሰጡት አቶ ደበበ እሸቱ፥ ማስታወሻው ለምን ለጠቅላይ ሚንስትሩ?” ብላችሁ ትገረሙ ይሆናል። ምክንያቴ ሁለት ነው፦
አንድ፦ አቶ ደበበ እሸቱ እንዲያደምጡኝ የማስመራቸው መድረክ የለኝም፣
ሁለት፦ አቶ ደበበ እሸቱ የኢትዮጵያ “የኪነ-ጥበብ ባለሞያ” ናቸው። ምን ለማለት እንደፈለኩ ይገባችኋል። ስለዚህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀዘን መግለጫ ሥነ-ስርዓት ላይ መንፅራቸውን አውልቀው እንባ ላሳዩን እና ትናንትናም በድጋሚ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌን “ፋሽስት” ብለው ለፈረጁት ጠቅላይ ሚንስትር ትንሽ ልበል።
መቼም የአንቱታ አክብሮቴ ከምን እንደሚዘል ይረዱኛል የሚል ግምት ይኖረኛል። እንደ መዝሙረኛው ዳዊት “እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጄን አላነሳም” ለማለት በግንባርዎ ላይ ነብይ ሳሙኤል ያፈሰሰውን ዘይት ባልመለከትም፥ በማንኛውም ግለሰብ የህይወት መዝግብ ላይ የአምላክ አሻራ እንዳለ አልጠራጠርምና፥ የእርሶም የዛሬው ስልጣን የአምላክ ፈቃድ፣ የጣቱ ፅሕፈት ነው ብዬ አምናለሁ።
እርሶ የሚኖሩት – እኔ የማነበው መፅሐፍ፦ “ልብስህን ሳይሆን ልብህን ቅደድ” ይላል። መነፅርዎን ከማውለቅ በተጨማሪ፥ የህዝብ ሰቆቃና ሃዘን እንዳያስተውሉ የጋረዶትን የዓይኖንም ጉድፍ ቢያስወግዱ ሀገር ምንኛ ባረፈ? በእርሶዎ መለኮታዊ ትዕግስት መተኪያ የሌላቸው በሺህ የሚቆጠሩ ነፍሳትን አጥተናል፥ እያጣንም ነው። ወንድ ልጅ የጀርባ አጥንቱ እንደ ቄጤማ ጠውልጎ፥ መቆም ተስኖት የመድረክ ፑልፒት ተደግፎ የሚያቃስተው፥ የመሰረት ድንጋይ ሲተክል ዝሎ ሳይሆን አባቱን ቀብሮ፣ በቤተሰቡ ሐዘን ቆስሎ ነው። እርሶ ይኼ የሚሰማዎት መቼ ይሆን?
የእርስዎ ስህተት የእኛም ሀዘን ከባድ ነው። ለእይታ ካልሆነ በስተቀር፥ የዓይን እንባ አይደለም የባህርም ውሃ ይህንን ህመም አያስውጠንም፤ ዘላለም አንቆ ከሚቆረቁረን ጉሮሮኣችን ላይ ጥቂት አይገፋውም። ደግሞም፦ ቆሞ የማይሟገቶትን – ነፍሱ ከስጋው የተለየችን ሰው በከንቱ አይክሰሱ። መቼም ቢሆን አይረቱትምና! ምክያቱም፦ ለፍርዱ ጠበቃ የሚያቆመው ከነፍሱ ማደሪያ ከሰማይ እንጂ ከስጋው መቀበሪያ ከምድር ስለማይሆን።
የሰው ልጅ ታሪክን የሚፅፍበት እርሳስ እንጂ የሚሰርዝበት ላጲስ አልተሰጠውም። ከንቱ መድከም ነው። ይመኑኝ ሀቅ ነው! የሰው ልጆች ታሪክ የሚሰራ ጥበብ እንጂ፥ ታሪክ የሚፍቅ አቅም ከአምላክ አልታደልንም። መቼም ቢሆን የልቦለድ ቃላት ጐርፍ በእውነት ካፊያ ላይ ሰልጥኖ የሀቅን ዘር ጠርጎ ወስዶ ከመብቀል ከልክሎ አያውቅም። የእርሶ “fascist” ለእኔና ለብዙዎች የነፃነት fashion እንደነበሩ የሚያውቁበት ጊዜ ሩቅ አይደለም!