Post

መሪዎች  እግር ኳስ ተጫዋቾች አይደሉ … .

መሪዎች እግር ኳስ ተጫዋቾች አይደሉ … .

By Admin

ከዕለታት ኣንድ ቀን እንዲህ ሆነ። ኣንድ ዝናው በጣም የገነነ፣ በሁለት እግሩ ለሚራመድ የአዳም ዘር ነፃነት ትልቅ ምሳሌ የሆነ ትውልድ ልደቱን በጋራ ለማክበር መከረ። እናም፦ ከዚህም ከዚያም ተሰባስቦ፣ መልካም ልደት ሲል እየዘመረ ወደ ሰፊው አደባባይ ተመመ። ግና፥ ኣንድ ብልጣብልጥ ደፋር፥ ትውልድ ንቆ፣ ይሉኝታን ፍቆ፣ “surprise!አለው ጀማውን፥ ንጉስ አውርዶ … ሰቅሎ ፎቶውን።

ጽሑፌን በተረት መሰል ወግ ብጀምርም፥ ዋና ጭብጤ ግን ይህ አይደለም። ሀገራችን ካለችበት ፈታኝ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ የተነሳ፥ በሁለት ጐኑ ብቻ ሳይሆን፥ በኣራቱም ጠርዝ የተሳለ ድርብ ሰይፍ ጨብጦ የሚነሳ መሪ እና ተመሪ በምናፍቅበት በዚህ ወቅት፥ ለተረትም ሆነ ተረብ የሚሆን ኢትዮጵያዊነት ውስጤ የለም። እርግጥ ነው፥ አድዋን የመሰለ ታላቅ የጦርመስክ ወደ ቡጢመድረክ አሳንሶ፥ አሸናፊውን ሰብ ብቻ በግለሰብ ደረጃ ማወደሱ አግባብ ነው ብዬ አላምንም። ያም ሆኖ ግን፦ የታሪክ ሽሚያ እያሉ የሚያላዝኑ ቋሚ ፈሪዎች፥ ሙታን ጀግኖችን ማጅራት መተው፣ እንደ ንጉሰነገስት ሁሉ የዜጎችዜጋ ሆነው ታሪክ ሲሰርቁ መመልከት አሳፋሪ ነው። ስለዚህም የግሌን ትዝብት ተነፈስኩ።

የዓለማችንን ፖለቲካ ጥርስ (gears) ነው ከሚዘውሩት ጥቂት ሀገራት መካከል ኢትዮዽያ ኣንዷ መሆኗ አያጠያይቅም። ለዛም ነበር፦ በኣንድ ወቅት በንስርክንፍ ድረ ገፃችን ላይ ያሰራጨሁትን፣ ለዚህም ጽሑፍ ገላጭ ምስል አድርጌ የተጠቀምኩትን ካርቱን (cartoon) Tour de Monde / Grand Tour World የሚል ርዕስ የሰጠሁት።

በውቅቱ፦ ሀያላን የነበረችው ሀገረአሜሪካ፥ እንደ ውጪ ፖሊሲዋ ትኩሳት አንዴ ግብፅን ረግጣ ኢትዮዽያን አንስታ፥ ሌላ ጊዜም ኢትዮዽያን ረግጣ ግብፅን በማንሳት የኣንዱን ፍላጎት በሌላው እየነገደች (እያስፈራራች)፥ የዓለማችንን ፖለቲካ ወደ ፈቃድዋ ዋልታ ስትዘውረው ዘመናትን አስቆጥራለች። ወደ ኋላ በማፈንገጥ አልታዘዝ ያሉትን የቻይና፣ ራሺያ፣ ቬንዙዌላንና የመሳሰሉት ሀገራትንም ጫና (የኋላ ጎማ)፥ የኣውሮፓን ህብረት (የፊት ጎማ) በመጠቀም ሚዛን ፍላጎቷን አስጠብቃ፣ ለጡት ልጇም ‘free ride’ ሆና ረጅም ርቀት ተጉዛለች።

ይህን የካርቱን ምስል ባዘጋጀሁበት ወቅት (2015 G. C.)፥ ቻይና እና ሕንድን መሰል ሀገራት በኢኮኖሚው መስክ እያየሉ በመውጣታቸው … የኋላው ጎማ ተለምዶዋዊ ቅርፁን ለውጦ (ተንፍሶ)፥ ብስክሌቱ ከጥቂት ኪሎሜትር (ዓመታት) ጉዞ ቦኃላ መቆሙ ግድ ይሆናል የሚል እምነት ነበረኝ። ሆኖም፦ ልዕለሀያሏአሜሪካ በሀገራት ሉዓላዊነት ውስጥ የነበራት ጣልቃ ገብነት ዛሬም ቢሆን ጋብ አላለም። ይህን እውነት ለማሳየት ደግሞ፥ ንቀት በተሞላበት የድፍረት እርምጃ ተጉዛ … ልዘዝበትያለችውን የቤታችንን ደጃፍ ከመጠቆም ውጪ የሚፃፍ ሌላ ተጨማሪ ምዕራፍ አላስፈላጊ ነው።

ለምዕራቡ ዓለም፥ ዲሞክራሲ” … ተስፋፊ የቅኝ ግዛት እግራቸውን የሚሸፍኑበት ሞቃት ካልሲ ነው። ለአሜሪካንም ሆነ ለኣውሮፓ ህብረት፥ ሰብዓዊ–መብት” … የታዳጊ ሀገራትን ቅርስ የሚዘርፉብት፣ ለጋ ኢኮኖሚያዊ ዕድገታቸውን የሚቀጩበት ወፍራሙን እና ወንጀለኛ እጃቸውን የሚከፍኑበት ጓንት ነው። ከዚህ ውጪ ግን አንተ ሌላ ትርጉም ካለህ … በእውነትም ቂል ነህ።

ወቅታዊው የኣሜሪካንና የኣውሮፓ ህብረት ኢሰብዓዊ ሰብአዊነት ኣንድ ክስተት እንዳስታውስ አደረግኝ። በ2016 እንደ ኣውሮፓውያን አቆጣጠር፦ እንኳን ቁጣው፥ ከስንት ኣንዴ ድንገት ብልጭ የምትለው የፊቱ ፈገግታ ምዕራብያውያኑን እንደ ተሳበ የጥይት ቃታ የሚያስደነብራቸው ፑቲን፥ ለሀገሩና ለቀጠናው ስጋት ነው ብሎ ያሰበውን አሸባሪ ሊፋለም ሶሪያ ገባ። ገብቶም፦ ለዓለም ባልተለመደ ፍጥነትና ድፍረት የአይሲስን ኩይሳ ሲምስ ሲንደው ምስጡ መተረማመስ መበታተን ጀመረ። ልማድ፣ ከዚያም አልፎ እንጀራነውና ግብዙ የምዕራቡ ዓለም ሰብዓዊመብት ተጣሰ!” ሲል ጮኸ። በኣንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ዕድል የተሰጣት ኣውሮፓዊት፦ ራሺያ ሰላማዊ ሰዎችንና ሲቪሊያንን ደበደበች ስትል ለራሱ ለፑቲን ከሰሰች። ፕሬዝደንቱም፦ በአየር ጥቃት የመታሁት አውሬዎቹን ነው፤ የተረፉትም የሲቪሉን ልብስ እየለበሱ በመሸሽ ኣውሮፓ እየገቡ ነውና፤ እኔን መክሰስ ትታችሁ እነዚህን ሰዎች ከውስጣችሁ አጽዱ። እነዚህ አውሬዎች ኣንድ ጊዜ ደም ቀምሰዋልና ከሲቪሉ ማህበረሰብ ጋር በፍጹም መቀላቀል አይኖርባቸውም ሲል ቆፍጠን ያለ መልስም ምክርም ሰጠ። ሰሚ ግን ጠፋ። ኣውሮፓ፦ ሰብዓዊ መብት!”ዴሞክራሲ!” ስትል ብዙ ዘመረች።

ነገር ግን ወር ሳይሞላ ፓሪስ የንፁሀንን ደም በገፍ ጠጥታ በሃዘን ሰከረች። የኣውሮፓ ህብረት መዲና ብራስልስ ጭምር በቦንብ መተራመስ፣ በደም መራስ ጀመረች። ይኼኔ ነበር የፑቲን ከሳሾች፦ አሸባሪነትን ለማስወገድ አብረን እንስራከማለትም አልፈው፥ የዘመሩለትን ሰብዓዊ መብትበመርገም ከቤት እስከ ጓዳና ያለምንም ማስረጃ የኣንድ እምነት ተከታዮችን ብቻ በስም፣ በአልባሳትና በቆዳ ቀለም እያሳደዱ መልቀም የጀመሩት። ዛሬም እየሆነ ያለው ይኸው ነው። ታዲያ ምን ዋጋ አለው መሪ (ፖለቲከኞች) እግር ኳስ ተጫዋቾች አይደሉ፤ በዚህ ጭንቅ ሰዓት በአሳማዎች ከመመራት፥ ፕሬዝደንት ፑቲንን ቢያንስ ለስድስት ወር እንኳ ኮንትራት እንዳናስፈርመው።

Comments are closed.