Post

መሪ ፍለጋ

መሪ ፍለጋ

By Admin

የናፍቆት ሰመመን ቁጭ ካልኩበት ወንበር ላይ አንስቶ እንደ ንስር በክንፍ ይዞኝ ይበር ጀመር፤ ኢትዮጵያ፣ አውሮፓ፣ አሜሪካ . . . መሪ ፍለጋ። ልብ እምነቴን ጥዬበት ጉልበት ህይወቴን የምሰዋለት አንድ ቆራጥ ሰው ፍለጋ ከአድማስ አድማስ በምናብ ስጋልብ፥ እነ መግደላዊት ማርያም ክርስቶስን በዋሻ መቃብሩ ውስጥ ሲፈለጉት ድንገት ተከስቶ በስፍራው ያለመኖሩን ያረዳቸው መልአክ እኔንም “ሙታንን ከህያዋን መካከል ስለ ምን ትፈልጋለህ?” ሲል ከቀን ህልሜ ያነቃኝ መሰለኝ። እውነት የሀገራችን ጀግና መሪዎቻ ያለፉትና የሞቱት እነ ቴዎድሮስ፣ ሚኒልክአሉላባልቻበላይአብዲስ አጋ፣ እና የመሳሰሉት ብቻ ናቸው? በቃ? አሁን መሪ የለንም ማለት ነው? ብዬ አሰብኩ።

ኣንድ ሺህ ባሪያዎችን ነፃ አውጥቻለሁ፣ ባርነታቸውን ቢያውቁ ኑሮ ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ኣንድ ሺህ ባሪያዎችን ነፃ ማውጣት እችል ነበር ሲል በተናገረው Harriet Tubman ዘመን፡ የነፃነት ትግሉ ማንቆ፦ ባሮች መሆናቸውን የማያወቁ ባሪያዎች መብዛት እንጂ ከባርነት ነፃ ለመወጣት የሚደረገውን መራራ ትግል ታግለው ለማታገል የተዘጋጁ ቁርጠኛ መሪዎችን ማግኘት እንዳልነበረ አስታወስኩ። ዛሬ ላይ ሆኜ እራሴን፣ ህዝቤንና  ሀገሬን ስመለከት ግን እውነታው የተገላቢጦሽ ነው። ባሪያዎቹ ባርነታችን ገብቶናል – በዝቶም አንገሽግሾናል! ነገር ግን የትግልን ሀ ሁ ቆጥረናል፣ የማደራጀትን ስሌት ቀምረን ተክነንበታል የሚሉ መሪዎችን ማግኘት ተስኖናል።

ዛሬ በምድራችን ውስጥ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የበደል ፍም አለ። ግን የማን ትንፋሽ ጉልበት ኖሮት ችሎ እፍፍፍ ብሎ – አመድ አፈሩን ገልጦ ያቀጣጥለው? እንኳን የሚጨሰውን ማንደድ፡ የነደደውንም ሰደድ በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል አቅቶናል። የቅርቡን የባልቻን ልጆች አመፅ ብንመለከት እንኳ፦ ሁሉም የፖለቲካ መሪዎቻ አመፁ ፍጹም ፍትሀዊ ለመሆኑ ቅንጣት ጥርጣሬ የላቸውም፤ መንግስታዊ ዋልጌነት የወለደው አንደሆነም በየመገናኛ ብዙሃኑ ሲሰብኩን ይደመጣሉ። አንዳቸውም ግን “የእኛ እጅ የለበትም ” ከደሙ ንፁህ ነን ከማለት ወጪ ትግሉን ተቀላቅለው አቅጣጫ ለማስያዝና ለማሳካት ሲደፍሩ አላየንም። ታዲያ መሪ የመሆን ወይንም “መሪ ነኝ” የማለቱ ትርጉም ምንድነው? በቃለ-መጠይቅና በመግለጫ ብዛት ሰዓት እንጂ ስርዓት ሲያልፍ አላየንም። ይህንን እውን ለማድረግም ደግሞ እኛ የመጀመሪያዎቹ ልንሆን አንችልም።

ትግላችን እንደ ህፃናቶቹ የሹሌ ጨዋታ አንዴ ተራግጦ ቁጭ፤ ከዚያም ደግሞ ቆይቶ ብድግ፡ አሁንም ሮጦ ዘሎ ረግጦ ቁጭ – ጭጭ እንዳይሆን መሪና አስተባባሪ የግድ ያስፈልጋል። በእርግጥ ህወሀት እንደ መንግስት ለመቆምም ሆነ ለመራመድ ዋስትናው ጠመንጃ እንጂ እግሩ (ህዝቡ) ያልሆነበት ሰዓት ላይ ደርሷል። ከእንግዲህ ቦሃላ ለዘረኛው መንግስት ያለ ጦር መሳሪያ ድጋፍ ወጥቶ መግባት የማይታለም ህልም ሆኗል። ለዚህ ጽሁፍ feature image ባደረኩት የካርቱን ምስል ላይም ለማስተላለፍ የፈለኩት ሃሳብ ይህንኑ እውነት ነው። ያ በራሱ ግን ትግሉን ለማሳረፍም ሆነ ለማሳረግ እንደ ትልቅ ድል መቆጠር የለበትም።

አሁንም የዜጎች ትከሻ በግፍ ሰደፍ ይጎብጣል፤ ዛሬም የኣንድ ዘር ጠረን ብቻ የሚሸት ባሩድ የተሞላ ጥይት ህፃን አዛወንት፣ ሴት ወንድ ሳይል በጅምላ ይገድላል። ሃይማኖት፣ ብሔር ሳይለይ ከጫፍ ጫፍ ያሉ ህዝቦች በምሬት እየከፈሉ ያሉትን ዋጋ በዘላቂነት ለማስቆም ቆራጥ መሪና አስተባባሪዎች ያስፈልጉናል፤ ትግሉን ከጥንስሱ የሚያግዙ። ግንድ ከወደቀ ቦሃላ መጥረቢያ ይዞ መሮጥ እንጨት ፈላጭ እንጂ ዛፍ ቆራጭ አያደርግም።   

እዚህም እዚያም ከተዳፈነው ፍም ላይ አመዱን አራግፈው አንድ ሀገራዊ እሳት ማስነሳት የሚችሉ መሪዎች ያስፈልጉናል ብዬ ስል “ምሁራኖች” ማለቴ እንዳይደለ ላሰምርበት እወዳለሁ። ምሁር ሁሉ መሪ የመሆን ብቃት አለው ብዬ ስለማላምን። ትምህርት ለማሰብ የሚያስችል አቅምን ያጎለብታል እንጂ በራሱ ብቁ አሳቢ አያደርግም። ትምህርት ቤት የገባ ሁሉ ተምሮና አውቆ ይወጣል ብሎ ለመናገር መድፈር፥ ሆስፒታል የተኛ በሽተኛ ሁሉ ተፈውሶና ፍጹም ጤነኛ ሆኖ ይመለሳል ብሎ እንደመከራከር ነው። ከዚህም ባሻገር የሀገራችን ችግር ትምህርት ሳይሆን ትምክህት፣ የሰላም ማጣታችን መንስኤው ዕውቀት ሳይሆን ንቀት እንደሆነ ለማንም ግልፅ ነው። 

የዚያን ሰሞን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምሁራንን  ሰብስቦ የማወያየት እርምጃ አንድ-አንዶች እንደ መልካም ጅምር ቢያወድሱትም ለእኔ ግን “ምሁራኖችን” ያስተነፈሰ ወይንም ያናፈሰ ትርጉም አልባ  ስብሰባ ከመሆን በዘለለ ያለውና የሚኖሮው ፋይዳ ፈፅሞ አልታየኝም። በእርግጥ ጅማሬው በጎ ነው ከተባለ፡ በጐነቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የተወካዮቹ ምክር ቤት የካድሬዎችና የሆድ-አደሮች ስብስብ ነው ” ብለው ማመናቸው ላይ ይመስለኛል። እንደዚያ ብለው ባያምኑማ፦ ህዝቡ ሳቅና ለቅሶውን ሊያሳየን፣ ሀዘንና ደስታውን ሊያሳወቀን ወክሎ ሰጥቶናል ያሉትን የተወካዮች ምክር ቤት ተሻግረው “ለተፈጠረው ሃገራዊ ቀውስ መንስኤው ምንድነው?” ብሎ ምሁራኑን መጠየቅ ባላስፈለጋቸው ነበር።

ገሚሱ የሀገራችን ምሁር ጭንቅላቱ ላይ የደፋውን የጨርቅ ቆብ እንደ ፅላት ቆጥሮ፡ ታቦት እንደተሸከም ካህን ስራመድ ቄጤማ ከልተበተነልኝ፣ ጀማው በእልልታ ካላበደልኝ ብሎ የሚኮፈስ – እሱ በራሱ የማህበረሰቡ ችግር መሆኑ አልገባቸውም ልበል ጠቅላይ ሚኒስትሩ? ቢገባቸው ኑሮማ ምሁሩን መሰብሰብ ሳይሆን ምክር ቤቱን መበትን ነበር መፍትሔው። “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” በሚል የዘረፋ ፉከራ ምክር ቤት የገባ ተወካይ፡ ምግብ ቤት የከረመ ተስተናጋጅ ይመስል ገና በሁለት ወሩ ሁለት ሰው መስሎ፣ ሰፍቶ እና ሰብቶ እንኳን ለወንበር ለምድር ከብዶ ብቅ ይላል። በአንፃሩ ደግሞ ወካዩ ከትላንት ዛሬ መንምኖ፣ ከስቶና ከስሎ ይታያል። ታዲያ “ተወካይ” “ወካይን” መሆን ቢያቅተው እንኳ መምሰል ከተሳነው ምኑ ላይ ነው ውክልናው? እንደ እኔ እንደ እኔ የዛሬይቱ ኢትዮጵያን ወክለው ለጠባቦች መርዝ ማርከሻ፣ ለዘረኞች ነቀርሳ መፈወሻ መፍትሔ ለማፈላለግ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጥ የሚገባቸው ከየመንደሩ የሚለቀሙት ካድሬና “ምሁራኖች” ሳይሆኑ፥ ባህልን ከብልሀት ጋር አጣጥመው በረጅም ዕድሜ ጥበብን የቀሰሙ አዛወንቶች ናቸው። አሁን ላላለንበትም ሆነ ወደፊት በአጭር የጊዜ ገደብ ወስጥ ያጋጥመናል ብዬ ለምሰጋው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ መፍትሔ መሆን የሚችሉት ከየብሔር ብሔረሰቡ፣ ሀይማኖትና  ፆታው አንድ አንድ ሆነው የተወከሉ የሀገር ሽማግሌዎች እንጂ ከየትምህርት ዘርፉ የተውጣጡ ባለ ዲግሪዎች ሊሆኑ እንደማይችሉ አጥብቄ እገነዘባለሁ።

የሰው ልጅ መብት ሚዛን አልባ ነው። በተለይም ደግሞ በዲሞክራሲ ስርዓት አንድ ሰው ከሌላው ያልበለጠ ወይንም ያላነሰ መብት አለው ብለን ማመናችን፥ ግለሰብ ከማህበረሰብ (ከግለሰቦች ስብስብ) ያላነሰና ያልበለጠ እኩል መብት አለው ወደሚል ፈልስፍናዊ ድምዳሜ ላይ ያደርሰናል። ያ ማለት፦ የኣንድ ብሔር፣ ሃይማኖት ወይንም ፆታ በቁጥር መብዛትም ሆነ ማነስ በተወካይ ሽማገሌዎቹ ቁጥር (በወንበር ድልድሉ) ላይ ተፅዕኖ ሳይኖረው ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሀይማኖቶችና ፆታዎች ኣንድ ኣንድ ተወካይ ብቻ እንዲኖራቸው ያስማማናል። ይህ በራሱ ደግሞ ማንኛውንም ሃሳብ በማስተናገዱ ሂደት የሽማግሌዎቹ ወሳኔ  ፍጹም ፍትሀዊ፣ ከዘረኝነት የፀዳና የሀገሪቷን ጥቅም ብቻ ያስቀደመ እንዲሆን ዋስትና በመስጠት ያግዛል። በሌላ አነጋገር ከአማራም ይሁን ከትግሬ፣ ከኦሮሞም ይሁን ከጉራጌ፣ ከወላይታም ይሁን ከአፋር፣ ከጋሞ ከጋምቤላም፣ ከማንም ቢሆን … እስላምም ይሁን ክርስቲያን፣ ከወንድም ከሴቱም ብዛትና ቁጥርን ያላገናዘበ አንድ አንድ የሆነ ውክለና መኖር ትክክለኛውን የዲሞክራሲ አስተሳስብና መርህ እንድንከተል ያደርገናል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው “የአብላጫ ድምፅ” መርህ ትክክለኛ ግንዛቤ የሚኖረን። “Majority Rules”  ብለን ስንል በሀሳብ እና በፍላጎት አንድ ሆኖ መብዛትን እንጂ በዘር፣ በቀለም አሊያም በሀይማኖት ተመሳስሎ መከመርን ለማሳየት እንዳልሆነ ከዘረኝነትና ከጠባብነት ለፀዳ አእምሮ ሀቅ ነው። 

ከላይ የተመለከታችሁትን የካርቱን ምስል አስመልክቶ ከቋጠርኩት ግጥም ላይ ትንሽ ልቆንጥርና እንሰነባበት

ስሙት ሲፎክር … እያለ ሲያቅራራ
አ’ጁዋ … አጁ’ዋ
ተነሳ ተራመድ … በነፍጥ ከዘራ
ለዘር ብልፅግና … ለሀገር መከራ

እንኳን ተወለድና … እንኳን ተፈጠርና

ይኼ ከንቱ …
ገደቢስ ባለ ዕጣ

መና አግኝቶ … መላ ያጣ
ትላንት በእግሩ ገብቶ … ዛሬ በእጁ ወጣ 

Comments are closed.