
By Admin
December 10, 2019 …
አመታዊው ክረምት በቅዝቃዜ ባኮራመታት የኦስሎ ከተማ ኣንድ ህንፃ ብቻውን ሞቅ ደመቅ ብሏል። ከመሠረት እስከ ጣሪያው አጠቃላይ ቁመናውን ጨምሮ ማጌጫ ሥዕሎቹም (paints) ሳይቀር በሀገር በቀል ምርቶች እና አርስቲስቶች የጥበብ ስራ ውጤት ብቻ ተገንብቶ እንዲዋብ የተደረገው የኦስሎ ከተማ መዘጋጃ ቤት (rådhus) ለኣንድ ታላቅ አለም-አቀፍ ትዕይንት ክፍት ሆኗል …
እንደ ወትሮው ሁሉ … ከንጉሳውያን ቤተሰብ እስከ ተራ ግለሰብ፣ ከዕውቀት ከበርቴው እስከ ትምህርት ለምኔው፣ ከውጉዙ እስከ ቅዱሱ፣ ሓብታም ደሃ ተብሎ መድሎ ሳይደረግ ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ ተጋባዥ-እንግዳ የኣመቱን የሠላም ኖብል ሽልማት ስነስርዓት ለመታደም ቦታ ቦታውን ይዟል …
ቀድሞ የኖርዌይ ፍትህና ፖሊስ ሚንስትር የነበሩት የኣሁኗ ኖብል ኮሚቴ ሊቀመንበር Advocat (ጠበቃ) Berit Reiss-Andersen መድረኩ ላይ በመውጣት የመክፈቻ ንግግር ካሰሙ ቦኃላ … የ 2019 የሠላም ኖብል አሸናፊ የሆኑት ግለሰብ ተለምዷዊውን ‘Noble Lecture’ እንዲያቅርቡ በፈገግታ እየተመለከቷቸው “ጠቅላይ ሚንስትር” ሲሉ ወደ ፖዲየሙ ጋበዙ …
ከ 87 ኣመቱ የእድሜ ባለፀጋ ብራዚላዊው Raoni Metuktire እስከ 16 ኣመቷ ስዊዲናዊ ታዳጊ Greta Thunberg፣ በትውልድ ሀገሯ መናገሻ ከተማ መቋዲሾ በስሟ ‘Elman Peace and Human Rights Center’ የሚል ተቋም ከመሰረተችው ከሶማሊያዊቷ ወጣት Ilwad Elman እስከ የአለማችን ህግ አስከባሪ ፖሊስ ነኝ ባዩዋ ኣሜሪካ ርዕሰ-ብሔር Donald Trump … በኣጠቃላይ 13 ግለሰቦች ተወዳዳሪ ዕጩ ሆነው በቀረቡበት ምርጫ አሸናፊ የሆኑት ኢትዮጵያዊው ጠቅላይ ሚንስትር ኣብይ ኣህመድ ኣሊ ገላቸውን በጥቁር ሱፍና ጥቁር ክራቫት፣ ፊታቸውን ደግሞ በብሩህ ፈገግታ ሽክ አድርገው ሸፍነው ወደ ፑልፒቱ መራመድ ጀመሩ። ይህን ጊዜ፦ በኣዳራሹ ውስጥ የተገኘው ነጭና ጥቁር በኣንድነት እንደ ዛሬው ግራ በመጋባት ሳይሆን በኣክብሮት እየተመለከተ በደማቅ ጭብጨባ ያጅባቸው ገባ …
በዘርፉ … ከኣፍሪካ ኣህጉር ለዚህ ኣለምዓቀፋዊ ሽልማት በመብቃት 12ኛ የሆኑት ግለሰብ የኖብል ኮሚቴ ሊቀመንበሯን በእጃቸው በመጨበጥ፣ ታዳሚውን ደግሞ ትሁት በሚመስል ግብረገብ ጭንቅላታቸውን ትንሽ ዝቅ በማድረግ ካመሰገኑ ቦኃላ ክብረ በዓላዊውን ንግግር አደበታቸውን በማለስለስ ማነብነብ ጀመሩ …
በታሪካዊው የኦስሎ መዘጋጃ ቤት መሰብሰቢያ ኣዳራሽ ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ በሚዘጋጅ ክብረ በዓል ላይ ሽልማታቸውን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚንስትር … ከጥቂት የመግቢያ ዓረፍተ-ነገሮች ቦኃላ እንዲህ አሉ …
ይህን ሽልማት የምቀበለው በኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን፣ በሰላም ጓዴ በፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቄ፣ በኣፍሪካውያንና በኣጠቃላይ የሰላም ህልማቸው ወደ ጦርነት ቅዠት በተለወጠባቸው የኣለማችን ሰዎች ሁሉ ስም ነው …
ሁላችሁም እንደምትረዱት … እኔ የጦር ተፋላሚ ብቻ ሳይሆን የጦርነትን አስከፊ ገፅታና በሰዎች ላይ ለሚያደርሰውም ጉዳት ምስክር የምሆን ግለሰብ ነኝ። ጦርነት ለመራራ፣ ለርህራሔ-የለሽና ለጨካኝ ሰዎች ነው። ከሃያ ዓመታት በፊት ለኣንድ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ቡድን (unit) በራዲዮ ኦፕሬተርነት ለማገልገል ባድመ ወደምትባል የጠረፍ ከተማ ዘምቼ ነበር። ከተማዋ በሁለቱ ሀገራት (ኢትዮጵያና ኤርትራ) መካከል ለተካሔደው ጦርነት ኣብይ ማዕከል ነበረች …
ጥሩ የሞገድ ግንኙነት ለማግኘት በማሰብ ለኣፍታ ከመሸግንበት የቀበሮ ጉድጓድ ብቻዬን ወጣሁ። ቆይታዬ የወሰደው ጥቂት ደቂቃዎችን ብቻ ቢሆንም ስመለስ ግን የተመለከትኩት ትዕይንት እጅግ ዘግናኝ ነበር። የመድፍ ጥይት እኔ የነበርኩበት ቡድን አባላት ምሽግ ላይ አርፎ ኣንድ ነፍስ እንኳን ሳይቀር በአጠቃላይ ሰዎቹን ከምድረ ገፅ አስወግዷቸዋል። እስከ አሁንም ድረስ እነዛን በክፉ እድልና ቀን ህይወታቸውን ያጡትን የትግል ጎደኞቼን እና ቤተሰቦቻቸውን አስታውሳቸዋለሁ …
በሐሰት ሀሴት የሚያደርጉት ጠቅላይ ሚንስትር ለበዓሉ ድምቀት በዕለቱ የተኩሱት የውሸት መድፍ ካልሆነ በስተቀር ይህንና አሳዛኝ ሌሎች ክስተቶችን የደሰኮሩበት ቀን ካለፈ እንሆ ኣራት ዓመት ሊሞላው ሦስት ወራት ብቻ ነው የቀረው። ውሎ አድሮ፦ በደም የሚደምቁት ጠቅላይ ሚንስትር … በየቀኑ ለሚታረዱት፣ በእርስ-በርስ ጦርነት ህይወታቸው ለሚያልፈውና ለሚፈናቀሉት ምስኪን ዜጎች የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል ርሕራሔ የሌለበት ስብዕናቸው እየተገለጠ ሲመጣ … እኔም እንደ እርሳቸው እነዛን በመድፍ ጥይት ህይወታቸውን ያጡትን የመከላከያ ሠራዊት ኣባላት አሟሟት ማስታወስ ጀመርኩ። እውነት የጠቅላይ ሚንስትሩ ‘የትግል ጓዶች’ ህይወት የጠፋው ‘በክፉ ቀንና እድል‘ ነው ወይንስ ሆን ተብሎ በድብቅ ለጠላት በተላለፈ የአቅጣጫ (location) መረጃ? ኣይኖቹ ለኣፍታ እንኳ የማይከደኑት ኣምላክ … በመድፍ አረር ወደ ኣቧራ የተቀየረውን የሚስኪኖቹን አጥንትና ሥጋ፣ የቋሚ ቤተሰቦቻቸውንም እንባ መዝኖ በራሱ ቀጠሮ ፍርድ ይሰጣል። ለእኔ ግን ይህ ክስተት እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ እንቆቅልሽ ሆኖ በኣእምሮዬ ውስጥ ተቀምጧል …
ዛሬ ላይ፦ በ 121 ዓመታት እድሜው ለ 110 ግለሰቦች እና ለ 30 ተቋማት ሽልማት በማበርከት ሰፊ ልምድ ያካበተው የኖብል ሠላም ኢንስቲትዮት በጨበጣ … ዘላለማዊ ስም፣ ወርቅና፣ በሚልዮን የሚቆጠር ረብጣ ብር ተበልቷል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። የሰላም ኖብል ኮሚቴውም ቢሆን ኣደባባይ ወጥቶ ‘convinced ’ አልያም ‘confused ’ ተደርጌ ነው ብሎ ቃሉን ባይሰጥም … በሻሻ በሿሿ ጨዋታ ወደር-አልባ ከተማ እንደሆነች ሳይገባው የቀረ አይመስልም። እንዴት? ቢባል፦ እንደ ሊቀመንበሯ ምስክርነት ከሆነ … የኖብል ሰላም ኮሚቴው ጠቅላይ ሚንስትሩን በእጩነት የተቀበለበትና በኣሸናፊነት የመረጠበት ኣንኳር ምክንያት ‘ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር የነበረውን የድንበር ግጭት ለመፍታት የተጫወቱትን ወሳኝ እና ግንባር-ቀደም ሚና ’ በመመልከት ነበር። ይህ ደግሞ የኮሚቴው እምነት ብቻ ሳይሆን አሸናፊው ጠቅላይ ሚንስትርም ቢሆኑ በመግቢያ ንግግራቸው ላይ ‘ይህን ሽልማት የምቀበለው በሰላም አጋር ጓዴ ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቄም ስም ጭምር ነው ’ ሲሉ ተደምጠዋል። ያኔ! …
ዛሬ ግን … ጠቅላይ ሚንስትሩ በስውርና በግል በሚደሰኩሩበት መድረክ ላይ ሁሉ ‘የሰላም አጋሬ፣ የሽልማቴ ምክንያትና ተካፋይ’ ካሏቸው ግለሰብ ጋር በወደብ ምክንያት ካልተደባደብኩ እያሉ ለገላጋይ እንደሚያስቸግሩ የኣደባባይ ሚስጢር ሆኗል። የቁማርተኛው ኦህዴድ ኣውራ እንደ ኣፍላ የኣውሮፓ ጎረምሳ (teenager) ለኖብል ሰላም ኮሚቴውም ሆነ ለሰላም አጋራቸው የመሐል ጣታቸውን በማውጣት “ይኼ ነው!” ያሉ ይመስላል። ወደ እኛው ሀገር ትርጉም ስንመልሰው “መስሎሃል!” እንደማለት።
N.B.: የጠቅላይ ሚንስትሩ ኖብል ሌክቸር ንግግር ኣጭር የኣማርኛ ትርጉም የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ ሲሆን ቀጥተኛ የእንግሊዝኛ ፅሑፉን ለማንበብም ሆነ ለማዳመጥ እዚህ ይጫኑ።