Post

መከላከያን የሚከላከል መከላከያ እንገነባለን!

መከላከያን የሚከላከል መከላከያ እንገነባለን!

By Admin

የዛሬ ፅሑፌን አየር ላይ ላውለው ያሰብኩት ከጥቂት ቀናት በፊት … ኣመቱን ሙሉ የሚያከበረው ጨረባ፣ የሚዘክረው በዓል የማያጣው የጨረቃው መንግስት “የመከላከያ ሳምንት” ብሎ ውሾች ኣንገት ላይ ሁሉ ሳይቀር የኣበባ ቀበቶ ባጠለቀበት ወቅት ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው …  ሰው የሚውለው በኣምላክ እንጂ በራሱ ሓሳብ አይደለምና ይኸው ጥቂት ቀናት አለፉ።

ወደ ቁምነገሩ ለመንደርደር … በኣጠቃላይ የሚል ድምዳሜ ላይ ባያስደርስም፥ ወንድም ይሁን ሴት ኢትዮጵያዊ ድንገት ከእጁ ላይ ዕቃ ሲወድቅ አሊያም ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ድምፅ በቅፅበት ሲሰማ ሳያስበው ከኣፉ አምልጦ የሚወጣ ቃል ወይንም ሓረግ አለ።

ሳት ብሏት የውሽማዋን ስም ጠርታ “እከሌ ድረስ!” ያለች ደፋር ድንጉጥ ባታጋጥመኝም፥ አብዛኞቹ ባለ ትዳር ሴቶች ግን የባሎቻቸውን ስም በመጥራት ድንጋጤያቸውን እንደሚገልፁ በደንብ አውቃለሁ። ከእጇ ላይ ማማሰያ፣ ከመክተፊያው ላይ ቲማቲም በወደቀ ቁጥር ስሙን እየጠራች ያማረረችው ባል “ኣሥር ጊዜ ስሜን በየማድቤቱ እየጠራሽ ጥላሸት አትለቅልቂው” ሲል ያማረረም ከሆነ … “ቀረብህ እንጂ አልቀረብኝም” ብላ ቤዛዋን ፍለጋ ፊቷን ወደ መላዕክትና ፃድቃን በማዞር “ገብርኤል!” ፣ “ህፃኑ ጨርቆስ!” የምትለዋንም ባለመዘንጋት ነው። ወንድ ከሆነም … እንደ አያ ፋኖ አይነቱ  “ዘራፍ!” ሲል፥ እንደ አቶ ደመቀ መኮንን የመሰለውም “ዘርፌ!” የሚል ይመስለኛል።

ይህ ልማድ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራትም ጭምር በስፋት ይስተዋላል። በኣንድ ወቅት ለኣጭር ጊዜያት ሱዳን ውስጥ ከከረመ ግለሰብ ጋር ስለሀገር ጉዳይ ስንወያይ ያጫወተኝም እውነት ይህን ያስረዳል። በቆይታው የተመለከተውን ሲመሰክር፦ “ዛሬም ድረስ  ሱዳኖች  ከየት ኣቅጣጫ እንደሆነ የማያውቁት ከፍተኛ ድምፅ በድንገት ሲያስደነግጣቸውመንግስቱ መጣ!ይላሉ” ሲል አጫውቶኛል። ለምን? ብዬ ስጠይቅም፦ “ክቡር መንግስቱ ኃይለማርያም የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት በነበሩበት ወቅት ሱዳኖች በስደት ሀገራቸው ውስጥ የተጠለሉ ኢትዮጵያውያንን ማንገላታት ሲዳዳቸው … ፕሬዘደንቱስደተኞቹ እኔን ቢጠሉም ኢትዮጵያ እና እኔ ግን አልጠላናቸውምበማለት ለማስጠንቀቂያ በሚሆን መልኩ ተዋጊ ጄቶቻቸውን  በሱዳን አየር ክልል ውስጥ እያንባረቁ ያመላልሷቸው ስለነበር ነው” ሲል መልሶልኛል።

ይኼ ታዲያ ያኔ … ከትላንት ወዲያ ነው። በውቅቱ የነበሩት መሪዎችም ሆኑ የሠራዊቱ አባላት በዜግነት ክብርና በሀገር ፍቅር ሰልጥነው በተመረቁበት ደጉ የደርጉ ዘመን። እንደ ትላንቱ … ወንድ ልጇ በፅንፈኞች ካራ ታርዶ፣ ሴት ልጇ በሳውዲ አረቢያ እስር ቤትና በቤሩት አውራ ጎዳና ለሰባት ተደፍራ ጩኸቷን ለማሰማት ሀገሯ አደባባይ፣ መንድሯ ጎዳና ላይ የወጣች እናት በህወሃት ኣጋዚ ቆመጥ ሳትቀጠቀጥ በፊት። እንደ ዛሬው አረመኔው የኦህዴድ አመራርና ሠራዊት ገጠር ተጎዞ በሳር ጎጆቸው የተጠለሉትን ኣዛውንትና ህፃናት ድሮን እያመላለሰ ሳያከስላቸው ማለት ነው።

እውነት ለመናገር፦ እነዚህን የውጭ ሀገራት ጥቅም አስከባሪ ቅጥረኛ መሪዎችንና ቢበሉ ቢበሉ የሚሞላ ሆድ የሌላቸውን ጅረት-አንጀት ባለሥልጣናት በዱላም ይሁን በደብተራ ትምህርት መታደግ ይቻላል ብዬ በፍፁም አላስብም። ሆኖም ግን ከፍተኛ ጥረት ከተደረገ ከተራ ሠራዊቱ መካከል ቢያንስ ጥቂቱን እንኳ … ከግለሰብ በፊት ህዝብን፣ ከቤተ-መንግስት በፊት ሀገርን አብልጦ እንዲያይ ወደ ወል ማንነት ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህም እነዚህን ጥቂት የመከላከያ አባላት ነፃ የሚያወጣ አዲስ መከላከያ መገንባት ግድ ሳይል አይቀርም።

ይህስ ባይሆን … የኣማራ ገበሬ በየቀኑ እንደ ቆሎ እየዘገነ የሚማርከውን መከላከያ የሚከላከል ሌላ መከላከያ አያስፈፍግም ብላችሁ ነው? ለኢትዮጵያ ህዝብም ቢሆን “ከመከላከያ ጎን እቆማለሁ” ብሎ መከላከያው ሸሽቶ በሮጠ ቁጥር ከጎኑ ለመቆም ተከትሎ ሲሮጥ ልቡ ፈንድቶ ከማለቁ በፊት ለመከላከያው ሌላ መከላከያ መገንባት እጅግ አስፈላጊ ነው። አዎ! መከላከያውን የሚከላከል ሌላ መከላከያ ይገንባ! ዛሬም ባይሆን ከጥቂት ቀናት በፊት በተከበረው “የመከላከያ ቀን” … መሪ ቃል (መፈክር) መሆን የሚገባው ይህ ነበር: መከላከያን የሚከላከል መከላከያ እንገነባለን!  

Comments are closed.