Post

“መፈንቅለ መንግስቱም” ተሳክቷል!

“መፈንቅለ መንግስቱም” ተሳክቷል!

By Admin

ትላንትና፥ ቀድሞ ከምመለከታቸው ሁለት ሀገራዊ የዜና ድረ-ገፆች  ውጪ  እርሜን  ወጣ ብል፥ አንድ አርዕስተ-ዜና ተመለከትኩ –  “ጠቅላይ ሚንስትሩ ፓርላማውን  በእንባ  አራጩት”  ይላል። ዓይን መሳቢያ – ብልጭልጭ  የአልባሌ ዜና ልጣጭ  (መጠቅለያ) መሆኑ አልጠፋኝም። ያም ቢሆን ግን  “ባህር-ዳር  ላይ ደም ያራጩት ጠቅላይ ሚንስትር ሳምንት ሳይሞላቸው ከምኔው ፓርላማውን  እንባ  ለማራጨት  ደረሱ?”  ብዬ  ከማሰብም  ባሻገር፣ ሌላ  ትኩስ  ዜና  አልነበረምና  ያንን  ተንቀሳቃሽ  ምስል ከፈትኩ። የተመለከትኩት ግን እንደተባለው እንባ ሲያራጩ ሳይሆን፥ ለታዘዛቸው አገልጋይ  ክንፍ ሰክተው፣  “እምቢኝ!” ላላቸው ደግሞ ቀንድ  ተክለው ኣንዱን መልአክ ሌላውን ጭራቅ አድርገው  ሲስሉ ነበር። ጠቅላይ ሚንስትሩ፦  በገዳይና   በተገዳይ  መካከል ገደል ፈጥረው ይኼን በገነት ያንን ደግሞ በሲዖል ለማኖር ሲጥሩ፥ በሁለት  ወንድማማቾች መካከል  ልዩነትን ዘርቶ፣ አለመስማማት አብቅሎ፣ እልቂትን ያሳጨደ ግብዝ  ባለሥልጣን  ርስቱ የት እንደሆነ ግን ሳይናገሩ አልፈዋል።    

እዚህ ጋር ያለኝን ጽኑ እምነት ማስቀመጥ ግድ ይለኛል። ዶ/ር  አምባቸው መኮንንም  ሆኑ ብርጋዴር  ጄነራል  አሳምነው ጽጌ፣ ጄነራል  ፃእረ መኮንንም  ሆኑ ጄነራል ገዛኢ አበራ፣ እንዲሁም ሌሎቹም ለእኔ  እኩል  ኢትዮጵያዊ  ናቸውና በህልፈታቸው የሚሰማኝ ቁጭትም ሆነ ሀዘን አንድ ነው። እንደ ግለሰብ፦  እንኳን  የወገን  የጠላትም  ሞት ከማይስደስታቸው  ብዙሃን  መካከል ኣንዱ  ነኝ። የቱም አይነት ትርጓሜ ሊሰጠው ቢችልም፥  ደስታዬ  – ለነፃነቴ  መስዋዕት በሆኑት ሰማዕታት  እንጂ   በግፍ  በዘመቱብኝ ወራሪዎች ሞት አይደለም።  ኩራቴ –  የህይወት  ዋጋ  በከፈሉልን  ኢትዮጵያውያኖች  ጽናት እንጂ  ዋጋ  ባስከፈሉን  ጣልያኖች  እልቂት  አይደለም።

ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ አጠቃላይ የፓርላማ ዲስኩር ስመለስ፥ ከሸፈ የተባለው “መፈንቅለ መንግስት” ተሳክቶ አስተውያለሁ። በአደባባይ “ፍቅር ያሸንፋል!” ብለው የሚሰብኩት አቡነ-ሚንስትር፥ በጓዳቸው ለሀይልና ጉልበት እንደሚሰግዱ፣ ለእብሪት እንደሚንበረከኩ፣ ለትዕቢትም  እንደሚሰዉ  በግልፅ ተመልክቻለሁ። ሁሉንም ለማስደሰት ከንቱ የደከሙት ግለሰብ፥ በስተመጨረሻ፦  የሰው  ልጅ  ሁለት  የአፍንጫ  ቀዳዳ  ቢኖረውም  አንዱን  እንጂ  መልካምና መጥፎ  ሽታን ሁለቱንም  እኩል  ማሽተት እንደማይቻለው ተረድተዋል። ስለዚህም  የሀይል  ሚዛኑ  ወደ  አጋደለው  ህወሃት  ተስበዋል።  

በገዛ  አስተዳዳሪው  “ከሀገር ለመገንጠል ያስባል” ተብሎ  የተከሰሰውን  ፈርተው፥  “በክልል  ለመከለል” ይጠይቃል በሚባለው ላይ ዝተዋል። በአንደበታቸው  “ኢትዮጵያን ለማፍረስ የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እንዴት ፈረሰች ብሎ ምሁራንን ቀጥሮ  ይዶልታል” ያሉንን የሀገር ደላላ ነፃነት አውርሰው፥ “ኢትዮጵያ እንዴት ትሰንብት” በሚለው ሀገር ወዳድ ላይ ጥይትና እስር ተናዘዋል። ለግለሰቦች የስልጣን ውክልና ጎራ ይዘው የሚከራከሩት መሪ፥ ለህዝቦች መድሎ-አልባ ህገመንግስታዊ ውክልና በቆሙ ወጣቶች ላይ ጎራዴ ለመምዘዝ እንደማይመለሱ  በእርግጠኝነት ተናግረዋል። አዎን፦ ብሔርተኞችና  ህወሀት  አሸንፈዋል!  “መፈንቅለ መንግስቱም” ተሳክቷል!

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ህወሃት ቢሳቡም፥  ህወሃት ግን የዞረ “ድምሩን”  ለማወራረድ የቤተመንግስት ወይራ ችግኞች አድገው ጫካ እስከሚሆኑ ለመጠበቅ  ትዕግስት ያላት አይመስለኝም። ወደ ላይ ሳይሆን ወደ ታች ቀድማ መሸፈቷ  አይቀሬ ነው።  ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደዱም ጠሉ ትግራይ፣ አማራና ሲዳማ ከእጃቸው አምልጠዋል፤  ከጥቂት ጊዜም ቦኋላ ሱማሌ፣ ቤንሻንጉልና  አፋር ሳይወድ በግድ ይከተላል። በተለይም ኣማራ – የአዲስ አበባ ሚንስትሮችህ  ወንዶች ናቸው ብለህ ከአመንክ  በጊዜ ብትገርዛቸው ያዋጣሃል። 

Comments are closed.