
By Admin
የህወሃት ትግል ከጥንስሱም ቢሆን ትርጉም አልባ እርጉም ነበር። ጭካኔ እንጂ ጫካ ያገባቸው፥ በደልና ግፍ አልነበረም ወደ በረሃ የገፋቸው። አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ እንዳለው፤ “ወንበዴ” ነበሩና ወደ ውንብድና ተመልሰው ይኸው ዛሬ ሞት እና ሞርታር በየበረሃው እየማረካቸው ነው።
ትላንት … የአዛውንቱ የአቶ ስብሃት ነጋ እጅ፥ ማጌጫ ሳይሆን መቀጫ ቀለበት አጥልቆ ስመለከት … በሀይልና ሀብቱ ሲኩራራ ሰባት ዘመን እንደ ከብት ሳር የበላው የባቢሎን ንጉስ ናቡከደነፆር ትውስ አለኝ። እርግጥ ነው፦ ይህን ታሪክ ያነበብኩበት መፅሐፍ ሌላም ቃል አስታውሶኛል። “ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥ በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ፥ እግዚአብሔር ያንን አይቶ በዓይኑ ክፉ እንዳይሆን፥ ቍጣውንም ከእርሱ እንዳይመልስ ” ይላል (መጽሐፈ ምሳሌ 24 : 17)። የእኔ ምርጫም ሆነ ደስታ ደግሞ፦ በእነዚህ ሰውና ሰላም ጠል ፍጥረቶች ላይ የነደደችው የእግዚአብሔር ቁጣ እንዳትበርድ ነውና፤ ጮቤውን አርግቤ … ወደ ዛሬ አጭር ፅሑፌ ጭብጥ ልመለስ።
ከጥቂት ኣመታት በፊት (2015) … የሚሰማንን መናገር (verbal-ize your thought) ከሚለው መርሓችን በተጨማሪ፥ የሚሰማንን መሳል (cartoon-ize your thought) በሚል ሐሳብ፥ ለኣንድ ሳምንት በየቀኑ ኣንድ ኣንድ የካርቱን ምስሎችን በማህበራዊ ድህረ – ገፃችን ላይ እናስቀምጥ እንደነበር አስታውሳለሁ ። ከነዚያም ምስሎች መካከል፦ “ስብሀት ዶሚኖ-‘ፌክት (Sebehat domino effect)” የሚል ርዕስ የሰጠነው … ይህ … የዛሬ ፅሑፌ feature image ኣንዱ ነው።
ያኔም ቢሆን ፦ አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ በህወሃት የስልጣን ማማ ላይ እንደ Barbapapa የሰቡት ጉንቱ ባለስልጣናት ዳሌ፥ ለቢሮና bar እንጂ ለፍትህ ወንበር እንደማይሰፋ የመላው ኢትዮጵያዊ እምነት ነበር። ከዕለታት በኣንዷ ቀን፦ እነዚህ ወንጀለኞች ከህዝብ ፍርድ እንደማያመልጡ እኔ በቀለም ብስለውም፥ እያንዳንዱ ዜጋ በአእምሮው እርሳስ የነደፈው … የሚጠበቅ … ብርቅ የማይሆን ሐቅ ነበር። እጅግ የሚያሳዘነው ግን፦ ትላንት በጣም ጥቂት ከሆኑት የትግራይ ተወላጅ ምሁራኖች በስተቀር አብዛኞቹ ዝምታን በመምረጣቸው፥ ዛሬ ወንጀለኞቹ በውድቀታቸው ከቅዬና መንደራቸው የገፉዋቸውን ምስኪን ህፃናትና አዛውንት እናቶችን መመለከቱ ነው። አዎን … ከባለስልጣናቱ የእጅ አንጓ ቀጥኖ፥ በስመ ትግራዋይ ካቴና እንደ ቀበቶና መቀነት በወገቡ የጠለቀለትን ምስኪን መመልከት በእርግጥም ያሳዝናል።
በጥቂት ራስ ወዳድ ነገደ–ባንዳዎች እብሪት፥ እንደ ሀገር ያጣነው የዜጎች ህይወት ቀላል ባይሆንም፥ ክልሉ ከሚያጋጥመውና አይቀሬ ከሆነው አጠቃላይ ማህበራዊ ቀውስ በቶሎ እንዲያገግም፥ ዛሬም ከትግራይ ምሁራንና ወጣቶች ብዙ ይጠበቃል። ትላንት የእነ አቶ አምዶም ገብረሥላሴን ብሶት ለማፈን አዳራሹን በፊታውራሪነት በጭብጨባ ሲያውኩ የነበሩ እጆች፥ ዛሬ የብረት ካቴና አስሮ አደብ አስይዟቸዋል የሚል እምነት አለኝ። የትግራይ ህዝብ ምሬቱንም ሆነ ምርቃቱን ለመተንፈስ ከትላንት በተሻለ ከዘረኝነት የፀዳ ክልላዊም ሆነ ብሔራዊ መድረክ እንዲኖረው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በጋራ መታገል ይኖርበታል። ግራ ቀኙን እያስተዋልን፣ የኋላውን አስታውሰን የፊቱን እየተነበይን በጥንቃቄ መጓዝ ግድ ይላል። ሽግግሩ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን።