Post

በበግ በረት በግ ገባ

በበግ በረት በግ ገባ

By Admin

አዴፓ June 29 / 2019 አስቸኳይ ስብሰባ አድርጌ አስተላለፍኩ ያላቸውን ስድስት የአቋም  ነጥቦች አነበብኩ። አንብቤም፦  ተግጦ በሚጣልላቸው  አጥንት  መንጋጋቸው ከትከሻቸው የሰፋ የአዴፓ ባለስልጣናት  “አቋም”  የሚይዙት  ገዢዎቻቸውን  በሚነካ  ጉዳይ ላይ ብቻ ነው ወይንስ ኣማራ-ነክ ስብዕናንም ይጨምራል ስል ጠየኩ። እንደዛ ከሆነ ታዲያ … ምነው Herman Cohen  ከብሔርተኞቹ ጋር አብረው ‘ኣማራ’ ብለው በጅምላው የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የተዛባ አመለካከት እንዲኖረው ዘመቻ ሲከፍቱ “አቋም” ለመያዝ አቅም አነሳቸው? ሲሆን ሲሆን “አጋር ነን”  የሚሉትን መንግስት አስገድደው (አስምሬበታለሁ) አሊያም  በጥገኛ ድርጅታቸው ደረጃ እንኳ ኣንድ  መስመር  ፅፈው  ግለሰቡን  መገሰጽ  ለምን ተሳናቸው?

ጠቅላይ ሚንስትሩ፦ ኣማራው ስልጣን ፈልጎ እንዳልተገደለና እንዳልተፈናቀለ፥ ዛሬም የምናየው ሀዘን ላይ እንዳልደረሰ ቢያውቁም፤  እኔም፦ እሳቸው ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌን (ነፍስ ይማር) ለመኮነን ሰባት ገፅ ልቦለድ  ለመፃፍ ግዜ እንዳላቸው ብገነዘብም፥  ቢያንስ  በ tweet  ደረጃ እንኳ የቀደሞውን ሽንጋይ ሽማግሌ እንዴት አላረሟቸውም ስል አልወቅስም። ስለማያደርጉት።  

እውነቱ ግን፦  ኣማራው በእሳቸው ወደ ስልጣን መምጣት አቅሉን አጥቶ ፈንጥዞ ነበር እንጂ አቂሞ ነፍጥ አልጨበጠም። ሰባተኛው  ንጉስ፥  ኣሥራ-ሦስተኛው ደቀመዝሙር ካልሆኑ በስተቀር፦ በብረትት ለበስ የጦር ተሽከርካሪዎችና  ታጣቂዎች  ከታጠረው መኖሪያ ቤታቸው ውጭ ያለስጋት ዘና፣ ፈታ የሚሉበት  ብቸኛው መስተዳድር የኣማራው ክልል እንደነበር ይክዳሉ የሚል ግምት የለኝም። ከጥቂት ጊዜያት በፊት  የተመለከትኩት የምስል መረጃ ትዕይንቱን ሙሉ ለሙሉ ቀርፆ ግምቴን ወደ ፅኑ እምነት ባያሻግርልኝም፥ በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የክልል መስተዳድር ስንብት የእራት ግብዣ ላይ በድንገት የተከሰቱት ጠቅላይ ሚንስትር ንግግር ለማድረግ ከጠረፔዛቸው ተነስተው ወደ “መድረኩ” ሲያቀኑ ግን የታዘብኩት ይህንን ነው: በፅልመት፣ ደጅም እንኳ ቢሆን በኣማራው መካከል  መቆም ስጋታቸው እንዳልነበርና ጀርባቸውን የሚመለከት ጠባቂ እንደማያስፈልጋቸው። ለዚህ ግምቴ መነሻ ደግሞ ከታች የተቀመጠው የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃ ነው።  ከደቂቃ 23:45 እስከ ደቂቃ 24:20   

አዎ … ይሔ ግን ያኔ ነው። ዛሬ የማይመለስ ታሪክ ሆኗል። ከሰሞኑ ክህደት ቦኋላ፥ በእኔና በእሳቸው ዕድሜ ቀርቶ አባቱን በተነጠቀው የላስታ ህፃን ዘመንም የማይመለስ ታሪክ። ለፖለቲካ ትርፍ ካልተካካድን በስተቀር፥  እኔን የሩቁን ሰው ቢጠራጠሩ እንኳ “በግል ጉዳይ ወደ አሜሪካ  በረዋል” ተብሎ፥ እሳቸው ግን  “ለስራ ጉዳይ”  ሲሉ ለመዋሸት ባህር ዳር ድረስ የበረሩትን ምክትላቸውም ማለቴ ምልክታቸውን ቢጠይቋቸው ቁና ቁና እየተነፈሱ ያስረዷቸዋል። የጦር መሳሪያ እንደ ጥርስ መፋቂያ የሚንቀውን ህዝብ፥ በሚያከብረው፣ አጎንብሶ በሚስመው መስቀል ታጥረው ነው ያለፉት። ጭንቅላታቸው አንሶ፣ ህግ ስርዓቱ አልፈቅድ ብሎ እንጂ ፅላት ተሸክመው፣ በወርቀ ዘቦ ተሸፍነው ተጣድፈው እንደመጡ ተጣድፈው ቢወጡ ምንኛ እንደወደዱ ይነግሯቸዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ የወታደር ዩኒፎርም ለብሰው የታዘቡት፣ የሪፑብሊኩ ጦር በጥይት የበታተነው ክቡር የሰው ልጅ ገላ እንጂ ያንን የሸክላ ጀበና አይደለማ።

ቅዳሜ ዕለት ማታ ጠቅላይ ሚንስትሩ “መፈንቅ- መንግስት” በሚል ርዕስ የተረኩልንን አጭር መድብል ሳዳምጥ፥ ከፍተኛ ስጋት የነበራቸው ጦር ሰራዊቱ ላይ እንደነበር ለመረዳት አላስቸገረኝም። ለዓላማህና ለሀገርህ ታዛዥ ሁን! ብለው ሲማፀኑም አዛዡ ላይ ኣንድ አደጋ እንደደረሰ አመላካች ነበር። እምቢ ካልክ ግን ጎረቤት ሀገርም ጦር አለ – የሚል በሚመስል ቅኔ ያቀረቡትን ምስጋና ደግሞ  ዛሬም አዴፓ በመግለጫው ላይ በዝርዝር ደግሞታል። የእነሱን ፖለቲካ እኔም ልጫወተውና፦ እንደው … ሀገሬው ባይረጋጋስ አዴፓ ኣማራን ከካርቱምና አስመራ ጦር ቀጥሮ ሊያስቀጠቅጠው ነበር? “ግሩም ነው!”  ይላሉ አቶ ገረመው ሲገርማቸው። ቅጥረኛው  አዴፓ  ቀጣሪ  ለመሆን መመኘቱም  ኣንድ “ለውጥ” (reform) ነው

ከዚህ በተረፈ፦ አዲሱን የኤታማዦር ሹመት ተመልክቼ “በበግ በረት በግ ገባ”  ብያለሁ፤ አሳርዶ  ሊታረድ። ግን  ጠቅላይ ሚንስትሩ ምክትል ኤታማዦር ሹሙን ወደፊት ከማምጣት ይልቅ  “አዲስ” ፊት ለምን አስፈለጋቸው? ከ”ዘረኝነት”  ሂስ  ለማምለጥ?  ወይንስ ጄነራል ብርሃኑ ጁላ ‘ይህ የሚፋጅ የወቅቱ ፖለቲካ በማንኪያ ይቅረብልኝ አሉ?’

እኔ እስኪገባኝ ድረስ፦ አብዛኛው  የኢትዮጵያ ህዝብ (አብዛኛው ላይ አስምሬበታለሁ) ‘የኦሮሞ  ተወላጆች  ሹመት በዛ፥  የትግሬው አንሰ’፣ ‘የኣማራው ተወላጅ የሃላፊነት ድርሻ ሰፋ፥  የሶማሌው ጠበበ’፣  የሲዳማ፣ የጉራጌም፣ የሐረሪውም ወዘተ ብሎ ብሶት የሚያሰማው፥  ከባለስጣኖቹ  ቆጠራ  ተነስቶ  ሳይሆን በአገልግሎት አሰጣጡ መድሎ ተማሮ ነው። አለበለዚያማ ከፒያሳ ተነስቶ “ቦሌ” ብሎ የተሳፈረ መንገደኛ ከቦታው ደርሶ  ቢወርድ  – ‘የወላይታ ሹፌር በዛ’ ብሎ ለምን ይጮሃል? ከጮኸህም ታሟል። ባለስልጣን  እኮ  ለመደበኛ ሀገሬው አግልግሎት የሚሰጥ ግለሰብ እንጂ ኪሱ የሚገባ ገንዘብ አይደለም። አነስ፣ ጨመረ ብሎ ቆጥሮ ለምን ያማርራል?

Video link: Amhara Mass Media Agency.

Comments are closed.