ስትወጣና ስትገባ፡ ከንጋት እስከ መሽት እሷን ጥበቃ አንድ ቦታ እንደ ጅብራ መገተሬን የታዘበ የውይይት ታክሲ ወያላ እንኳን ሳይቀር፦ “ለገሃር፣ ሳሪስ፣ ፎንቃ ደመቀ፥ የሞላ – በራሪ” እያለ ስሜን የደንበኞቹ መሳፈሪያ እና መውረጃ ምልክት እስኪያደርገው ድረስ፡ ድንዝዝ ድንግዝ ያልኩላትን የሰፈሬን ቆንጆ፤ ያቺን የምታውቋትን፣ ስለምን እና ስታላምኑኝ የነበረችውን ውዴን፤ በስፈር ጉልቤ ባስፈራራ፣ በሃገር ሽማግሌ ባስማልድ ባስጠይቅ፡ ለያዥ ለገራዥም በሉት ለገላጋይ (ሴት አይገረዝም እና) ያስቸገረችውን አመልማሎ፡ በአረጋዉያን ኢትዮዽያውያኖቹ ሽምግልና ሳይሆን፡ በእነዛ አፋቸው እኔን ቀርቶ እሷንም በቅጡ በማይገባት ሰላቶ መሳይ አሜሪካውያን ሸንጋይነት ያለፈው ቅዳሜ ድል ባለ ሰርግ አግብቻት አረፍኩላችሁ።
ታዲያ “እንኳን ደስ አለህ!” ለምትሉኝ ሁሉ መልሴ በአምላካችሁ ሳይሆን በዲቪያችሁ ነው። እስቲ እናንተንም ፀሎታችሁን ሰምቶ፡ የጠላችሁን አስወደዶ የሚድረው የአራዳው ጊዮርጊስ ሳይሆን የዋሽንግተኑ ዲቪ አለሁ ይበላችሁ፤ እናንተስ ብትሆኑ እንደኔው መናጢ አይደላችሁ ምን አላችሁ?
ያ ጣልያን አያት ቅድመ-አያቶቼን ፈጅቶ እንደው በጅምላ በነጭ ላይ ቂም አስያዘኝ እንጂ፡ አንድ አንዴስ ነጭ እውነትም ነጭ ነው። ያቺን ጠብራራ የጠብራራ ልጅ አገባለሁ ብዪ፤ ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ፡ ገሚሱ ከኣልጋ ሲወርዱ ደጅ ከምታስረግጠው ኣንድ ክፍል ቤቱ ደባል አስገብቶ፣ ከፊሉም የብር ጥርሱን ሸጦ በተጠራቀመው ኣንድ መቶ ሃምሳ ብር ጥሎሽ ልጣል፣ ሰርጌ ላግባ ብል አሻፈረኝ ያለችው ባለ ጨካኝ ልቧ እመቤት፤ ዛሬ “ዲቪ ደረሰዉ” ሲባል ብትሰማ፡ እንደ ህንድ ሙሽራ ጥሎሽ ጥላ ያገባችኝ እሷው ሆናላችሗለች፦ድፍን ኣስር ሺህ የኢትዮዽያ ብር ከዛ የሠርጌ ቀን ከተዋብኩበት እና ምቀኛ አይሉት ሞገደኛ አይጥ ደረቱ ላይ ቦጭቆት በሮ፡ ኮከብ አይመስል ኒሻን ነው አልል፣ ወይ ቀዳዳው አላነሰ ጥይት ነው ብዪ ከሰው ፊት አልኩራራበት፤ አንደው ለሰበብ አስባብ በቸገረኝ ጥቁር ወፍራም ኮት ኪሴ ውስጥ ከትታ።
ተመስገን! እንዲህ ነው እንጂ እፎይ ማለት፤ የሚወዷትን ሴት ብቻ ስይሆን የሚያፈቅሩትንም ብር በአንድ ቀን ሲዳሩ። “አይ ሞኙ” ነው ያላችሁት? “ነገ ልትፈነግልህ“? በስመ-ዲቪ፥ ወ-ዋይት ሃውስ፥ ወ-ዋሽንግተን በሉ እናንተ፡ ምነው ጎበዝ ይህን ትመኙልኛላችሁ? አቤት አቤት አሉ አያቴ፤ ይህንንስ የክሊንተን ጆሮ አይስማው። ደግሞስ ቢሰማው፥ እኔ ወንድማችሁ ደመቀ እንደሆነ የነቀምት ነቄ ነኝ። ይህን ባህር አቋርጠን፣ ውቅያኖስ ከተሻገርን ቦሃላ እንፋታለን ወይ እኮበልላለሁ የሚል ሃሳብ እንደሚኖራት ቀድሜ ነው ያለምኩት። ለዚህ አይደል ወንድም ይሁን ሴት፣ ወንድ-አፍራሽም ይባል ሴት-ፈራሽ፣ ብቻ ፍሬዪን ቋጥረሽ፣ ዘጠነኛው ወር ገብቶ አናቱን በከፊል፣ በጨረፍታ ካላየሁ በስተቀር አልነቃነቅም ብዪ ዘራፍ ያልኩት። አለበለዚያማ እንዴት ተደርጎ? ይሄ ፕሮሰስ የሚባለውን ነገር ንክችም አላደርገው።
እንደው ለምናልባቱ ሸውዳኝ እንኳ፡ እነዚያ የተባረኩ አሜሪካኖቹ ሃገር ገብተን የፍቺን ጥያቄ አነሳለሁ ብትል፡ የወሰደን አውሮፕላን መልሶ እዚሁ የተሰደድኩበት ከተማ፣ እምዮ ሸገር ይመልሰናል እንጂ እኔ ደመቀ፡ በክሊንተን ምያለሁ፦ በፍጹም አንላቀቅም።
በጊዜው ለንግስት እሌኒ የተፃፈ።