Post

ብልፅግና እንደ ዴዝዴሞና

ብልፅግና እንደ ዴዝዴሞና

By Admin

ፅሑፌን፦ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ነፍስ ይማር ብዬ መጀመር አግባብ ነው። ለቤተሰቡና ወላጆቹ፣ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን እመኛለሁ።

ወንድ ልጅ ላመነበት እውነት ቢገልም ቢገደልም ጀግና ነው! አሳፈሪውና የፈሪ ምግባር ግን ማስገደል ነው።

ትንሽ ከራርመን፦ በመዲናችን አዲስ አበባ የወዳጅ አዝማድ፥ በአጠቃላይ የነዋሪዎቿ ህልፈተህይወት በድንገት ሲሰማ፥ ለከተሜው ተለምዷዋዊ ጥያቄ የሚሆነው ታሞ ነበር ? ሳይሆን ማን ገደለው ? እንደሚሆን እርግጥ ነው። ለዛም ነበር ባለፈው ጥቅምት Adios Addis, Kudos Los Cabos! ስል የፃፍኩት። አዲስአበባ መንግስት ሳይሆን መሳሪያ የሚያስተዳድራት ህግአልባ ከተማ እየሆነች ለመምጣቷ የሚጠራጠር ካለ የሰሞኑ ግድያና እስር በቂ ምስክር ነው። ነጋድራስ ንጉሱ ያሰፉትን ምህዳር መቆጣጠር ተስኗቸው፥ በዚህም ሆነ በዚያኛው ወገን፥ ለሁከትም ይሁን ለበቀል፥ ሊገደሉ ይችላሉ ብለው የሰጉትን ፖለቲከኛ እና አክቲቪስት በሙሉ ሰበብ ፈልገው ሰብስበው፥ በአንድ ደጃፍ ኣንድ መቶ ሰራዊት አቁመው በእስር ማስጠበቃቸው፥ መንግስታቸው የዜጎችን በነፃነት የመንቀሳቀስና የመኖር ዋስትና ለማረጋገጥ አቅመ-ቢስ መሆኑን ያመላክታል። 

ይኽ ገና ጅማሬ ነው። እያደባ ዜጎችን ሲነጥቅ የምናየው የሰሜኑ ተኩላ ብቻ ሳይሆን፥ ከራሱዋ ከብልፅግና ጐሬ የሚወጣውም አውሬ የትየሌለ ነው። በእኔ እምነት፦ የኣራት ኪሎውን መንግስት ክፉኛ ነክሶ የሚያቆስለው የተሸረፈው የህወሃት ጥርስ ሳይሆን፥ ከድዱ በታች ተሰውሮ እያደገ ያለው የራሱ የብልፅግና መንጋጋ ነው። በሴራ ሰራይ የተበከለው ፖለቲካ፥ የታዋቂውን ተውኔት ባለሟል፥ የWilliam Shakespeare ድርሰት እየመሰለ መጥቷል ኦቴሎን። እያጎን ፈልፍሎ ማውጣት የእናንተ ስራ ቢሆንም፥ ብልፅግናን ግን ዴዝዴሞናብያታለሁ።

ነጋድራስ ንጉሱ እንደሆነ ነገም ተመልሰው እዛው ናቸው። ዛሬም እንደትላንቱ ኮሽ ባለ ቁጥር አትደንግጡ ! እንደሚሉን አልጠራጠርም። አዎና! ለእርሳቸው የአስተዳደር ብቃት መመዘኛው፦ ምዕራባውያን ከግል ጥቅማቸው አንፃር የሚለግሱዋቸው ውዳሴና ጭብጨባ እንጂ በከንቱ የሚፈሰው የህዝባቸው ደምና እንባ አይደለም። ለዚህም ነበር በኣንድ ወቅት፣ በኣንድ መድረክ ላይ መምራት እንደምንችልማ ይኸው ዓለም መሰከረበማለት የውጪውን fiesta cocktail እርሳቸው ጠጥተው እኛን በባዶ ያሰከሩን። ያ ባይሆንማ፥ የህዝቡ ጩኽት ቢገዳቸው፥ ሰላም አጣን ብሎ አቤት! ላለው ዜጋ እኔ ሰላም አስጠባቂ የሰፈር ሚልሽያ አይደለሁም ብለው አይወርፉትም። ግን … ግን … ነጋድራስ ንጉሱ ታች ኦሮምያ ክልል ወርደው፥ አርሶአደር ማሳ ውስጥ ውለው ገብስ ሲያጭዱ – ገበሬ“፣ በየመንገዱ የተተከለውን አበባና ችግኝ ውሃ ሲያጠጡስ – አትክልተኛነበሩ? የማይመለስ አቅላይ ጥያቄ ማብዛት ትርፉ ድካም ነውና ወደ ሌላው የጽሑፌ ጭብጥ ልመለስ።

ሰሞኑን ፊንፊኔን አስመልክቶ ከሰማኋቸው ወጐች በሳቅ ያፈነኝ የወይዘሮ አዳነች አበቤ ቀልድ ነው። ጠቅላይ ዐቃቤ ህጓ፦ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ህልፈት አሳቦ፥ ዱላ ጨብጦ ከደንጋይ ሀውልት እስከ የሰው ልጅ አጥንት እየነደለ ሰባብሮ፣ ሀዘን በችርቻሮና በጅምላ እያከፋፈለ አዲስ አበባ የገባውን አስለቃሽ – “ለሀዘን የወጣ አልቃሽ ብለው ሲራሩለት፤ በአንፃሩ ደግሞ እራሱን ከኦሪት ፍርድ ለመከላከል የተሰባሰበን የኣዲስአበባ ወጣት – “ሁከት ፈጣሪ፣ ሽብርተኛ ብለው ለቅጣት ወንጅለውታል። ወገግ ያለ ወገንተኝነት ይልሀል ይኼ ነው! ለእነ አቶ ጁዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባ እስር ድምቀት ሲባል በደቦ ታስረው የተደበደቡትን የኣማራ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞችን እሮሮ ስሰማ ግን፥ የዓባይ ውሃ ባላንጣችን ግብፅ ትውስ ብላኝ፥ ሳቄን አቆምኩና፦ አቤቱ አድምጠን! በዘመነ ኦህዴድ አሳር መከራችን በእስርና ድብደባ ብቻ ይለፍልን !ስል ፀሎቴን ለአምላክ አደረስኩ።

ይኼኔ ፦ ከዚህ በላይ ምን ሊመጣ ?ብላችሁ ይሆናል። ከ 3100 እስከ 2900 ከክርስቶስ ልደት በፊት በነበሩት ዘመናት፥ የግብፅ ነገስታት (ፈርኦኖች) እና መኳንቶቻቸው ሲሞቱ፥ ባሪያዎችም ሟች ጌቶቻቸው ወደዚያኛው ዓለም የሚያደርጉትን ጉዞ እንዲያጅቡና ከሞት ወዲያ በሚኖራቸውም ሁለተኛ ህይወት እንዲያገለግሉዋቸው ታስቦ ይታረዱ፣ አንዳንዴም ከጌቶቻቸው አስክሬን አጠገብ እስከህያው ነፍሳቸው ይቀበሩ ነበር። ይህንንስ መሳይ ክፉ ዕጣ ፈንታ እንዳይሰማ – “የሰይጣንን ብቻ ሳይሆን የተረኞቻችንንም ጆሮ ይድፈነውየሚያስብል ነው።

ለዛሬ እዚህ ላይ ይብቃኝ ምናልባት ግን፦ ሰባተኛውን ንጉስ ለምን ነጋድራስ አደረካቸው ?ብሎ የሚጠይቅ አንባቢ ሊኖር ይችላል። በእርግጥም ለምን ነጋዴ እንዳደረኳቸው ለማስረዳት በእርሳቸውና በባለስልጣኖቻቸው ፈቃድ ከእንስሳ ባነሰ ክብር ታግተው ያሉትን ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያኖችን ምስክርነት ከተጭባጭ የድምፅ መረጃ ጋር ይዤ – “ነጋድራስ ንጉሱበሚል ሌላ ፅሑፍ እመለሳለሁ። ለአሁኑ ግን ህዝቡን በገንዘብ የሚለውጥ ነጋዴ ከአልጋ ቁራኛ እስከ wheelchair ህመምተኛ ለየትኛውም ሳይራራ የዜጋውን ነፍስ በጠገራ የሚደራደር ሀገር አቋራጭ ሲራራከነጋድራስ ሌላ ምን የክብር ማዕረግ ይኖረዋል? ነጋድራሱ ቢያደምጡኝ ኣንድ ሐቅ ልነግራቸው እወዳለሁ የሰውን ልጅ መፃፊያ እጅ እንጂ ማሰቢያ አእምሮ ማሰርም ሆነ ማሳሰር ፈፅሞ አይቻልም። እውነቱ ይህ ነው፦ እጅ በካቴና ብረት ሲታሰር አእምሮ በንስር ክንፍ ይበራል! ፍፁም ድፍረት በተሞላበት ሀይል በነፃነት ይከንፋል። ይሰማል?

Comments are closed.