Post

ብልፅግና … እፉዬ-ገላ

ብልፅግና … እፉዬ-ገላ

By Admin

በደም የተፃፈ አኩሪ ታሪክ ሲያነብ የነበረ ህዝብ፥ ጊዜ ሳይሆን መሪ ጥሎት በለሀጭየተፃፈ አሳፋሪ ተረት ለማድመጥ በቃ። ከጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ እና ከኣማራ ክልል መስተዳደር የወጣውን ወቅታዊና ልዩ መግለጫ ሳደምጥ፥ ይኼ ብልፅግናያሉት መንግስት እፉዬገላ መስሎ ታየኝ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ዱቄትካሉት ህወሃት ያልተሻለ፣ ንፋስ ወዲህ ወዲያ የሚበታትነው … ገለባ።

ልፍስፍስ መሪ እራሱን ብቻ ሳይሆን ሀገርም ያልፈሰፍሳል። በኣንድ መዳፍ የሚዘገን መረን፥ መቶ ሚልዮን ህዝብን እንዲህ ሲያምስ መመልከት እንደ ዜጋ አንገት የሚያስደፋ ትልቅ ውርደት ነው። የጠቅላይ ሚንስትሩ ከልክ ያለፈ ራስ ወዳድነትና ልወደድባይነት፦ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ንፁሐን ዜጎች አላስፈላጊ የህይወት መስዋዕትነት እንዲከፍሉ ከማድረግም ባሻገር፥ በየኣህጉሩ የምንኖረው ኢትዮዽያውያንን አንገት አስደፍቷል።

አብዛኞቻችን … ኢትዮዽያ እንደ ሀገር እየደረሰባት ያለውን የውጭ ጫና ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ የተቃውሞ ጩኽት ላለመሆን እያየን እንዳላየ፣ እየሰማን እንዳልሰማ የምናልፈው አስተዳደራዊ እድፍና ጉድፍ እንደመዋቢያ ታቱና ንቅሳት ቆጥረን የተቀበልነው መስሏቸው ይሆን እንዴ?

ገና ከጅምሩም ቢሆን፦ ህወሃት አፈር-ልሶ ሳይሆን ሊጥ-ተጥቶ ተነስቶ እንዲህ እየተወራጨ ኣማራ ክልል እንዲገባ ጉልበት የሆነው … የአንካሳው ተኩስ አቁም ስሌት ወፍራም ምክንያት ምን እንደሆነ በሚገባ እንረዳለን። ደግመው ደጋግመው እንደሚያደነቁሩን፦ የክልሉ አርሶ አደር የእርሻ ወቅትወይንም ደግሞ ኣማራውን ጤና ያሳጣው ጥሞናም አይደለም። አቶ ሬድዋን ሁሴን ጭምር ሳይደብቁ በደማቁ የተነፈሱት ሐቅ በጊዜው የሚያንቀውን ያንቃል።

እስከዚያው ድረስ ግን፦ የዱቄት እርሾ እንደ አብሾ አሳብዶት፥ ህወሃትና ትርፍራፊዎቹ ትላንት ደሴ ላይ የገደሉትን ዜጎች ጨምሮ በየቀኑ ያፈሰሱትና የሚያፈሱት የኣማራ ደም፥ ነገ ለሌላ የበቀል አዙሪት የሚያዘጋጀን የዞረ ድምር ከመሆን ባሻገር ለየትኛውም በደል ማስተሰረያ መስዋዕት፣ ለማንኛውም ዕርቀሰላም ማሟሻ አብሽ የመሆን አቅም የለውም። ጦሩን የማዘዝ ስልጣን ያላቸው ጠቅላይ ሚንስትር ይህን በደንብ ሊያውቁት ይገባል። ዛሬ ህወሃት ላይ የሚያሳዩት ቸልተኝነት፥ ነገ ኣማራው እንዲከፍሉት የሚጠይቃቸው ብድር ነው። በወሎና ደሴ አደራድረው ህወሃት ተነጠኩ ብሎ የሚያላዝነውን ወልቃይትን መልሰው አይደለም፥ በልጅነት የቦረቁባትን በሻሻንም ጭምር መርቀው ቢሰጡዋቸው፥ ከእንግዲህ ኣውሬዎቹን በፍፁም አያለምዷቸውም። ህወሃትና ጀሌዎቹ ከጠቅላይ ሚንስትሩ እጅ ብቻ ሳይሆን፥ ጠቅላይ ሚንስትሩም ከህወሃትና ጀሌዎቹ ልብ ከወጡ ድፍን መንፈቅ ሞልቷል። ይልቅስ … እጃቸው ላይ የቀረውን ጥቂት … እጅግ በጣም ጥቂት መክሊት በአግባቡ ቢጠቀሙበት ያተርፋሉ። በሁሉም አካል ልወደድ ባይነታቸው አመራራቸውን ብቻ ሳይሆን ያልፈሰፈሰው፥ በማለዳ አብረዋቸው የቆሙትን ወዳጆቻውን ጭምር አሳጥቷቸዋል፤ ነገም ያሳጣቸዋል። ከኤርትራ ጋር ያላቸው መልካም ትስስርም ቢሆን ካልቆርጡ የሚቆረጥ፥ በተግባር ተልዕኮ እንጂ በአምልኮ ተክሊል የታሰረ ቃልኪዳን አይደለም።

በመጨረሻም ላነሳው የምፈልገውና እንደሁልጊዜው ዛሬም ሳስበው እጅግ የሚያሳፍረኝ የአሳማው ብአዴን መደንደን ነው። ጎበዝ … ይኼ ራስ ወዳድነትና ህዝብን ለግል ስብዕና ግንባታ ጭዳ የማድረግ አሳፋሪ በሽታ፥ እንደ ሚኒስትር እና ሚንስትር ዴታ ሹመት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የሚሰጥ / የሚታደል ስራይ ይሆን እንዴ? ህወሃት፦ ኣንዴ በባቡሩ ሐዲድ … ኣንዴ በአውራ ጎዳናው ላይ እንዲህ ያለከልካይ ስትጋልብ ስመለከት፥ እውነትም እነ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ አቶ ደመቀ መኮንን፣ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እና አቶ ተመስገን ጥሩነህ ስንዝር መሬት እንኳ ያልወሰዱ ጥሩ አገልጋይ ናቸው አልኩ። ለካ … ኣንድ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ ነበር የኣማራን መሬት ሁሉ ጠቅልሎ ይዞ የነበረው? ነፍስህን ይማረው አቦ! 

Comments are closed.