Post

ብሔርተኛ-ኣዳሪ

ብሔርተኛ-ኣዳሪ

By Admin

እንደ ኢትዮዽየዊ ባህላችን አንዳንድ የኣማርኛ ቃላቶች ለምላስ ብቻ ሳይሆን የሚመሩት ለጣትም እጅግ ይሻክራሉ፤ መናገር ብቻ ሳይሆን መፃፍም የሚከብድበት ወቅት አለ። በተለይ የኣደባባይ ንግግር ወይም ንባብ ላይ ለማዋል … የግብረገብ ጥያቄ ይነሳል። ያም ቢሆን ግን … ኣንዳንዴ … አስቀያሚን እውነታ ለመግለፅ እነዚህን “አስቀያሚ” ቃላት መፃፍም ሆነ መናገር አስገዳጅ ይሆናል።

ሰው አድናቆትና ክብር የሚገባው ተፈጥሮውን ሳይሆን የፈጠረውን ሸጦ መጠቀም ሲችል ነው የሚል ፅኑ ዕምነት አለኝ። ስለዚህም፦ ከሰባ ዳሌ እና ባት – የከሳ ዕውቀት … ከትልቅ ጭን – ትንሽ ጭንቅላት አብዝቶ ይስበኛል።

ተፈጥሮ የአምላክ ችሮታ ነው … የእግዜር ነፃ ስጦታ! እናም … የሰው ልጅ መፍጠር ወይንም ማሰብ ተስኖት በአካሉ ላይ የተገለጠውን የአምላክን ጥበብ በመሸጥ ብርም ይሁን ክብር – አድናቆትም ይሁን አምሮትን ለማግኝት ከሞከረ …  የመከነ ፍጡር ነው! ቢላሽ እና ርካሽ!  ለዚህም ምሳሌዬ፦ የተፈጠረላቸውን ገላ … ተምረው እንደተሸለሙት ዲግሪና ዲፕሎማ በየሶሻል ሚድያው ላይ በፍሬም በፍሬም እየለጠፉ … “እዩን – ግዙን” … የሚሉት ገላ-ኣዳሪዎች ናቸው።

እንደ እውነቱ ከሆነ፦ መቀመጫዋን ወደ ካሜራ ኣይን አዙራ የተነሳችውን ፎቶና ቪዲዮ በየ ድህረ-ገፁ ላይ በመለጠፍ ገላዋን ለግምት  በምታቀርብ ገላ-ኣዳሪ ሴት እና ጎዳናም ይሁን ጓዳዋ በር ላይ በምትቆም ሴተኛ-አዳሪ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? በእኔ እምነት … በዲጂታል ገላ-አዳሪዋ እና በደጇ ሴተኛ-አዳሪ መካከል የሚኖረው መሰረታዊ ልዩነት በተግባር ሳይሆን በአገልግሎት ክፍያ አተገባበር ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው። የዛች በVisa ወይም በVipps .. የዚህች ደግሞ  በጥሬ ብር ወይም በCash ስለሚፈፀም። በኣጠቃላይ … እውነታውን መዋጥ ቢከብድም … ትንሽና ትልቅ ሳይለይ አብዛኛው ማህበረሰባችን ማህበራዊውን ሚዲያ የሚጠቀምበት እንደ መማማሪያ ሳይሆን እንደ ቤርጎ – ማደሪያ – ነው።  

እራሴን ግልፅ ላድርግ፦  በየጎዳናው ላይ የምንመለከታቸው ሴተኛ-አዳሪዎች በሙሉ ይህን መልካም ያልሆነ ተግባር ለመፈፀም በቂ የሆነ ምክንያት የሌላቸው ነውረኞ ናቸው ብዬ አላምንም። እንዳንዴ … አንዳንዶቹ ተገደው የሚገቡበት የህይወት ፈተና … እንኳን ስጋቸውን ነፍሳቸውንም ቢሆን ለሽያጭ ቢያቀርቡ የሚያስገምታቸው መስሎ አይሰማኝም። በቅብ ግብረገብ ይህን እውነት መካድ እና መፍረድ … ጨዋነት ሳይሆን ግብዝነት ይሆናል።

ወደ ርዕሴ መንፈስ ስመለስ፦ እንደ አጠቃላይ ባህላዊና እምነታዊ እሳቤያችን … በተፈጥሮ የተሰጣትን የኣምላክ ችሮታ (ፆታ) ለንግድ የምታቀርብ እንስት … ሴተኛ-አዳሪ … ተብላ ከተወገዘች፤ ፈጣሪ የወሰነውን ተፈጥሮዋዊ ብሔሩን የሚቸረችር ዘረኛም … መኮነን፣ ማህበረሰባዊ  ክብርና ማዕረግ መነፈግ ይኖርበታል። ሴትነቷን የምትሸጥ “ሴተኛ-አዳሪ” ከተባለች …  ዘሩን እየመነዘረ ብሔሩን ተሸክሞ የሚያዞር ጀብሎም ትክክለኛ መጠሪያ ስሙ “ፖለቲከኛ”  ሳይሆን “ብሔርተኛ-ኣዳሪ” …  “አክቲቪስት” ሳይሆን “ዘረኛ-ኣዳሪ” መሆን ይገባዋል ባይ ነኝ።  

Comments are closed.