Post

ብሶት የገደለው መንግስት

ብሶት የገደለው መንግስት

By Admin

“… የህዝብ ብሶት የወለደው ጀግናው … .” ከዛሬ ሃያ ሰባት  ዓመት በፊት  ኣንድ ማለዳ በኢትዮዽያ  ብሔራዊ  ራዲዮ  ጣቢያ  በድንገት ከተሰራጨ  መልዕክት የተመዘዘ  ሐረግ  ነው። አዎ … ያኔ … ህወሃት  አዲስ  አበባ  ስትገባ።  አይ  “ጀግናው” …  ድንቄም!  አሉ  ወይዘሮ  ብርቄ፥   ገድገድ  ቢሉ  በኣንድ  ጠርሙስ አረቄ።

አንኳኩተው በፈቃድ  የተከፈተላቸውን  የደርጉን  በር  “በሀይል ሰብረን  – በርግደነው  ነው የገባነው ”  ብልው “ጀግናው ” እንዳላሉን፥  ይኸው  ዘንድሮም  እንደ   ኣምና በፍረሃት ተውጠው፣ በጦር  መሣሪያ  ታጥረው  የነፃነት  ቀናቸውን ሊያከብሩት ነው።  ከዚህ  በላይ  ሞት  ወዴት፥  ከዚህ  የከፋ  ወርደት  እንዴት  ይኖራል? እፍረት ሆኖባቸው  ቀድመው ካልሻሩት  በቀር፥ ምድር ከተፈጠረች ጀምሮ፡ በስጋት  ሰቀቀን  የፊጥኝ  ተወጥሮ፣  አንዴም  ሳይሆን  በተከታታይ  ሁለቴ  በአስቸኳይ  ጊዜ  አዋጅ  በጨለመች ጀንበር  ስር  የድል ቀንን  ያከበረ “ዴሞክራሲያዊ” መንግስት  ከህወሃት  በቀር  ማን አለ? ያውም “መቶ ፐርሰንት  መርጦኛል ”  ብላ  በፎከረችበት  ህዝብ  እየታመሰች!

ህወሃትን ብሶት ገደላት እንጂ  አልወለዳትም።  እርግጥ ነው፦ የኢትዮዽያ ህዝብ ብሶት የህወሃትን  ትግል ጉድፈቻ  ወስዶ፣  አሳድጎ  (ሀይልና  ጉልበት ሆኖ)፣  ለወግ-ማዕረግ  አልፎም  ለዘር ዘውግ  አብቅቷታል እንጂ ህወሃትን  ከደምና አጥንት የፀነሳት ቂም – የወለዳትም ክፋት ነው። በኣንድ ወቅት  የቀድሞው አብዮታዊ  መሪያችን ፕሬዝደንት  መንግስቱ  ኃይለማርያም  ከተናገሩት እውነታ ውስጥ ጥቂቱን  ስቆነጥር እንዲህ  ነበር፦

እንደ ህብረተሰቡ፣  እንደ  አካባቢው  ሁኔታ፣ እንደ  ለምነቱ፣  እንደ  ግንዛቤው፣  እንደ  አመራሩ  የተለያየ  ችግርና  ቅሬታ ውስጥ  እንዳለን  ግልፅ  ነው።  ግን  ወያኔዎችን  ያስነሳቸው የአምራቾች የህብረት ሥራ ማህበር  በማቋቋማችን  ነው  ወይ?  ኣንድ single የአምራቾች  የህብረት ሥራ  ማህበር  አለ  ወይ  ትግሬ  ውስጥ?አንድ  መንደር  በመንደር  ተሰባሰቡ ብለናል ወይ? ለኣስራ አምስት አመት  አንድ  ገበሬ  ኣንድ  ሳንቲም  ቀረጥ  ወይንም  ደግሞ  ግብር ጠይቀናል  ወይ?  ወይንም ደግሞ አንድ single  የሀገር  ውስጥ  ገበያ  ሰራተኛ  ሄዶ  ሲያበቃ ኣንድ ቁና  እህል ከትግራይ  ሸምቷል ወይ?  ይኼ  ነው  ወይ አሁን  የቅራኔ ምክንያት ሆኖ ሲያበቃ የወረሩን?በ 1930 ዓመተ ምህረት  በዚህ  ምክንያት ነው  የተወጋነው  ወይ?  ነው? አብዮታዊ ሰራዊታችን ከህዝብ  እንዳልተወለደና የህዝብ  ወገን  እንዳልሆነ  ሁሉ፣  ይኼንን  ገበሬ  እየሞተ  ባለ መሬት  እንዳላደረገ  ሁሉ፣ እየለመነ   ብስኩትና  ዱቄት  እንደማያድል  ሁሉSource Audio:

 

 

“ብሶት” ነው የወለደን አሉ። ታዲያ ያ ብሶት ምን እና  የት ነበረ?  ደግሞስ “ብሶት” አብዮት ነች ወይንስ የድመት ዲገላ ልጇን የምትበላ? በርግጥ  ዛሬ  ላይ  ሆነን  ህወሀትን  የገደላትን  ብሶት ለመጠቆም  የማልጨርሰውን  ሐቅ  አልቆጥርም።  ግን  ብቻ በግርድፉ፦ ግድያው፣ እስራቱ፣ ዘረፋውና  የማን  አለብኝነት ዝልፊያው፣ ስደቱ፣ ፓለቲካዊ  ኢኮኖሚያዊና  ማህበራዊ  ቀውሱ ሁሉ ተዳምረው  የወለዱት  ግብዳ ብሶት ህወሃትን  ላታንሰራራ  ዘርሯታል!  እንደምትፎክረው አፈር  ልሳ  አይደለም ዳግም  የ70 ቢሊዮን  ብር  ስኳር  ብትቅምም  በፍፁም አትነሳም!

ወደዚህ  ፅሁፍ  ሁለተኛ  ዋና  መንፈስ  ስመለስ፦  እንደ  አምናው ዘንድሮም፡  እኛ  እና  የእኛ  የሆኑት፣  እኛንም  የመሰሉት  ሁሉ ግንቦት ሃያን  ጥቁር  ለብሰን፣  ፌስቡክ  እና  ድህረ ገፆቻችንንም አጨልመን  ልንውል  ወስነናል።  ይህ ቀን፦  ወንድ  ሴት ወጣት አዛውንት  ሳይለይ  በመላው  ኢትዮዽያውያን  አንገት  የጭቆና  ሰንሰለት  የጠለቀበት፣ በታሪካችን  ከሰማነው፣ ከአነበብነውና ከኖርነው የትኛውም  ክፉ  ቀን  ሁሉ  አብልጦ  የከፋ  ብሔራዊ  የሀዘን  ዕለት  ነው። ግንቦት  ሃያ፦ ወጣቶች ተስፋ  ስለቋጠርን የምንዘምርበት  ሳይሆን  ስደት፣ እስራትና  ሞት አትርፈን ከመሐከላችን የጎደሉትን በሀዘን  የምንዘክርበት፣ እናቶች  በእልልታ  ሳይሆን  መበለቶች  በዋይታ የሚያስቡት የሰቀቀን ቀን  ነው።   

በቅርብ ከእስር የተለቀቁት  አቶ  በቀለ ገርባ  የተናገሩትን ቃል ተመርኩዘን የግንቦት ሃያ 1983 ዓመተ-ምህረትን  በረከት ስንመለከት፦ ከእስር-ቤት  ውጪ  በነፃነት  ከሚራመዱት  ይልቅ፥ በእግር-ቶርች  ተጠርንፈው  በየወህኒ  ቤቱ  ተኮራምተው የተቀመጡት ንፁሃን  ዜጎች ይበዛሉ።  በማረሚያ  ቤት  ከተዘጋባቸው  ጥፋተኞች  ጋር  ሲወዳደሩ፥  በአወራ-ጎዳናው  ላይ በኩራት  የሚንሽራሸሩት ወንጀለኞች  በእጥፍ  ይልቃሉ፤  ታዲያ  ይህንን  ቀን  የሚያከብረው  ማነው? ግንቦት ሃያ፦  የፍትህ ጎህ  የቀደደበት ሳይሆን ፍትህ እራሱ  20  ቦታ የተቀዳደደበት ዕለት ነው!

እርግጥ  ነው፥  እንኳን  የሦስት ሴት  ልጆች  አባት  ለሆኑት  ለኣዲሱ  ጠቅላይ  ሚንስትር  ዶ/ር  አብይ  አህመድ  ይቅርና፥  ገና ላልወለድነውም  ቢሆን  የአቶ አንዳርጋቸው  ፅጌ  ሴት  ልጆች እንባና ናፍቆት አንጀት  ይሰረስራል። ታድያ ህወሃት  በግንቦት  ሃያ  ዋዜማ ወይንም  ማግስት  ከግፍ  እስር  ፈታ፥  ሊነጋ  አይደለም  ሊፈግ  የማይችለውን   የ 27 ዓመት ፅልመት  እገፋለሁ  ብላ  አስባ ይሆን እንዴ እኝህን አባት እስከ  አሁን  አልሰጥም  ያለችን? ድንቄም! ነው ያሉት ወይዘሮ  ብርቄ?

ምስጋና፦ በውዴታም  ባይሆን  በግዴታ  ይህን  አድማችንን  ለማሳካት  የኢትዮዽያ  መብራት  ሀይል  ኮርፖሬሽን ከተሞቻችንንም  በማጨለም  ልማዳዊ  ድጋፉን  እንደማይነፍገን  በመተማመን ነው።  

Comments are closed.