Election Post

ተከለከለ አሉ የንጉስ ኣዳራሽ … የክት ያልለበሰ አይገባም በጭራሽ!

ተከለከለ አሉ የንጉስ ኣዳራሽ … የክት ያልለበሰ አይገባም በጭራሽ!

By Admin

ተከለከለ አሉ … የንጉስ ኣዳራሽ
የክት ያልለበሰ … አይገባም በጭራሽ

የክት ልብሱን’ማ የሃገሪቱን ኣንጡራ ሃብት እንክት አድርገው ከበሉት በላይ ማን አሳምሮ ሊለብሰው? ባይሆን በኮፒ ራይት ካልተጠየኩ- እኔው ራሴ አሻሽዬ  ብዘፍነውስ? ተከለከለ አሉ የንጉስ ኣዳራሽ … ተኩሶ ያልለበሰ አይገባም በጭራሽ !

ምርጫ እና ተቃዋሚ ድርጀቶችን በለመለከተ፡ ሰሞኑን የጦር ሰራዊቱ ልበል የጦር ኣራዊቱ አውራ ያሳዩት ንቀትና ዛቻ ሲገርመን፤ የፖሊስ ኣራዊቱ እርግጫ  ተከተለ። ይኼ ነገርርር … ብለን ገና የጀመርነውን ዓረፍተ-ነገር ሳንጨረስ፡ ምርጫ ቦርድ  ቀድሞን ደመደመው ፦ ምርጫ’ም መኢአድ’ም አንድነት’ም የሉም አለን። ለነገሩ ”ምን ተስፋ አይቆርጥም” ሆኖብን አንጂ፡ ሰዎቹ  ከ-እምበር ተጋዳላይ  ወደ እብሪተኛ ገዳይ  የተሻገሩበት የ97ቱ ምርጫ፡ አሳፋሪም አስተማሪም ምዕራፍ  ነበር።

ተቃዋሚ ድርጅቶች አድገው እና ረዝመው ከንጉሱ አዳራሽ በተጠጉ ቁጥር፡ መንግስት እንደ ሸገር መናፈሻ ጥድ በራሱ መልክ እና ቅርጽ አሳጥሮ ይከረክማቸዋል። ትላንት ቅንጅት፣ ዛሬ  ደግሞ አንድነት እና መኢአድ። ታዲያ ምን ተሻለ ጓበዝ? በክቱ ልብስ ካልሆነ፥ ያው ያዘቦቱን (የልምዱን) ተኩሶ መግባት እንጂ.

ፍቅርሽ አስጨንቆ … መላወስ አቃተኝ
ተደናበርኩለሽ … ጥይት እንደሳተኝ
ሳተና ነበርኩኝ … ተኳሽ በመውዘሬ
ለዘበናይ ብቻ … እጄን ሰጠሁ ዛሬ

እርግጥ ነው የሩቁንም ሆነ የቅርቡን ሰላማዊ ሰልፍ ስንታዘብ፡ ህዝባችን ከፍተኛ ጨዋነት ይታይበታል። ፖሊስ ከሰራዊት ምግባርና ተግባር ወጥቶ አራዊት ሆኖ ሲናከስና ሲራገጥ፡ ህዝቡ ዱላወን በትዕግስት ተቀብሎ፦ ደሙን አፍስሶ፣ አጥንቱን ስብሮ ወደ ቤቱ በወሳንሳ ይገባል። በወገናዊነቴ ስቃዩና መከራው ቆጭቶኝ ስሜታዊነት ቢፈታተነኝም፥ ትዕግስቱን ግን ከምስራቅ አውሮፓና ከሰሜን አፍሪካ ሰልፈኞች ጋር አወዳድሬ ”ለምን?” ብዬ አልጠይቅም። ወያኔ እንጂ ዘረኛው፡ ህዝቡ አይደለ’ማ። መንግስት እንጂ ለህዝቡ ፍቅር ያጣው፡ ህዝቡ ዛሬም ቢሆን በመቻቻል አብሮ የመኖር ባህሉን አልጣለውም። ጫካ ውሎ ጫካ አድሮ፡ አውሬ ሆኖ ለመናከስ፣ ያደገበትን የከተማ ስርዓትና ህብረተሰባዊ ገብረ-ገብ ለመፈረካከስ ህዝቡ ወያኔ ወይንም የዱር እንስሳ አይደለም። ያ ባይሆን ኑሮ’ማ ሳተናነቱና ተኳሽነቱ የዘር ነበር። የትላንቱ የአያት ቅድመ-አያቶቻችን እልህ ኣሻራ፡ በዚህ ትውልድ ደም ወስጥ ደብዛው ጠፍቷል የሚል ዜጋ የለም።

ውስጡን እንፈትሽው ከተባለም፥ የዩክሬንና የካይሮ አብዮተኛ እንደ ረሃብተኛ በአዉሮፓና አሜሪካ፡ አልፎም በሀይማኖትና በወገንተኝነት በተደራጁ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት እየታገዘ፦ ከብስኩት እስከ ወተት፣ ከውስጥ-ልብስ እስከ ብርድ-ልብስ በሬሽን እየታደለው ጌታዋን እንደተማመነችው በግ ላት ውጪ አደረ እንጂ፥ እንደኛዎቹ ደፋር ወንዶች፡ አንድ ሃገሩን አፍቅሮ አንድ ራሱን ሆኖ መች ተሰለፈ? መቼ ተቀጣቀጠ? ባይሆን፦ ሰልፉ እና ተቃውሞው የተፈለገውን ትኩሳት እንዲያሳይ ”ዲያስፖራው ምን ሰራ? ምን አገዘ?” የሚለውን ጥያቄ ማንሳት አግባብ ነው። ከመደብደብ፡ ይደባደብ ካልን፦ ለደሙ ማድረቂያ፣ ለቁስሉን ማጠቢያ፣ ለራሱ እና ለቤተሰቡ መደገፊያ፣ ጉልበት ሞራል የሚሆነው ምን ረብ ያለው ስራ ተሰራ? ፖለቲካችን- የአፄ ምኒልክ አብራክ ፡የአቦይ ስብሃት በረከት፡ የሌንጮ ለታ ብላቴና እያለ ከራሳችን አልፎ ግቢ ውስጥ ኣንድ ሆኖ የሚኖረውን ህዝብ እንዲበታተን ከመመረዝ ወጪ ምን ወዝ ኣለው? ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው።

በፍቅር ማነቂያው … ዶሮ እንዳይል በከንቱ ኧሪ አንቺን ወዶ
ክራሩን ሰት ሰሚ … ብቅ በይ ቆሜያለሁ ከበርሽ ማዶ

እስቲ ዘር፣ ድርጅት ሳይከፋፍል፡ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይል፡ በአደባባይ በዱላና በሰደፍ የሚቆስለውን ሰልፈኛ የሚያሳክም የሚያግዝ አንድ የጋራ ጥሪት (fund) ይኑረን? እስቲ የወገን ድካም እና ኧሪታ ከንቱ እንዳይሆን ከጎኑ ሆነን ትግሉን እናክርረው? በሰለፉ እና በእምቢተኝነቱ ሂደት የሚደሙትን፣ የሚቆስሉትን፣ ኣልፎም ከስራና ከትምህርት ገበታቸው ላይ የሚታገዱትን የሚበዥ ኣንድ ኣካል ሲቋቋም፣  ወገናዊነቱና የትግል አጋርነቱ በተግባር ሲረጋገጥ፡ ያኔ የተፈለገውን ትኩሳት በአደባባይ ማየት ይቻላል። ለዚህም በጎ ተግባር፡ ራሳችንንም ሆነ እኛን የመሰሉትን ለማሳመን፣ አምነንም ግዴታችንን ለመወጣት አቅም እና ጉልበት እንዳለን ለአፈታ አልጠራጠርም

አፈር ጭቃው ሲቆፈር፣ በማጥ በድጡ ህዝብ ሲያልቅ ዳር ቆመን ስንታዘብ ውልን፤ ደልድዩ ተሰርቶ ሲያልቅ’ና ሲመረቅ፥ መቀስ ይዞ ሪቫን ለመቁረጥ፣ አበባ ታቅፎ ከፊት ለመራመድ መሽቀዳደም፡ ያስተዛዝባል። ዛሬ ህዝባችን መሻገሪያው እንጂ የጠፋው አሻጋሪው አይደለም። ስልጣኔ እና ዕውቀት ወረርሽኝ ሆነው፡ በትንፋሽ’ና በንክኪ እንደማይተላለፉ የመጣነው አየነው፡ የቀሩትም አደመጡት። ውጭ ሃገር መኖሩ፡ ከፈረንጅ ጋር ውሎ ማደሩ፡ ሀገርቤት ያለውን ፖለቲካና ፖለቲከኛ አስንቆ እኔ ድልድይ ሆኜ አሻግርሃለሁ ለማለት ድፍረት አይሆንም። ይልቅስ ብቅ ብሎ ተቀላቅሎ፡ ትግሉን ጎን ለጎን –በብረት እና በብልሃት– ማስኬዱ ይበጃል።

አይወጣም ደረጃ … ቢፎክር ሴቼንቶ
እንደ እኔ ካልሄደ … በፍቅር ተገፍቶ
መድፈሪያሽ ወርቅ ነው … ብርም አይገዛሽ
ልብ የሌለው ሀብል … ግድም አይሰጥሽ

ወያኔ ተፎካካሪ ድርጅት ስለሌ እንጂ ስልጣኔን በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ ብሎ ሰለፎከረ፣ ይወጣል፣ ይሄዳል ብሎ ማሰቡ ዘበት ነው። ሰባ የጦር ጄነራል፣ ሺህ መቶ-አለቃ (ቼንቶ) – በፍቅርም ይሁን በፀብ፣ በአጥንትም ይሁን በብረት ካልተገፋ በስተቀር እንዴት ይነቃነቃል? ዛሬማ ብሩንም ወርቁንም ይዘውታል፤ ምን ያስደነግጣቸዋል? ከኪሳቸው ተርፎ- ህዝቡ የባለቤትነት ጥያቄ ቢያነሳ እንኳ በሚል ስጋት፡ “የዲያስፖራው የጋራ ሃብት ነው” ብለው ሊያታልሉት፡ ህዝብ ዘርፈው፣ ቅዬ ንደው እራሳቸው ለሚገነቡት ፋብሪካ ተለጣፊ ባለሃብት የሚሆን ውሻና ድመት ከባህር-ማዶ ማፈላለግ ጀምረዋል። ምናለ – ህዝቡም ደደብ፣ አዲስም ደደቢት አንዳይደሉ ቢገባችው? ለነገሩማ ንቀት ይዟቸው እንጂ ልዩነታችንንስ ተረድተወታል።

እስቲ ላለመናቅ ትግላችን ሀሞት ይኑረው፤ የምር ሆኖ ይምረር። እንደዛ ጥርሱን እንደ በቆሎ እሸት ፈለፍሎ አንደበላው ሆዳም ቀልደኞች አንሁን። እነሱም ግድ ያላሉን፦ ከማወራትና ሀ-ብሎ አፍን ከመክፈት ውጪ ልብ የላቸውም ብለው ነውያለውን አለ፣ የሌለውን ደግሞ የለም እንበል። በባዶ መኮፈስ፣ ገብስ ሳይሆን ወረቀት እየበላ የሚዘለውን ፈረስ መጋለብ አስናቀን እንጂ ወንዝም አላሻገረን። ታላላቆቻችን በኣዲስ ዘመን በሳተላይት ያደሉን ኣዲስ የትግል ስልትም ቢሆን፡ አንደ ታናናሾቻችን የእንቁጣጣሽ ንድፍ- በወረቀትና በቀለም አሽብርቆ ቀረ። የወሬ ሳይሆን የስራ፣ የተግባር ዓመት ነው የተባለለትም 2007፡ ይኸው ፀጥ ረጭ እንዳለ የስነ-ምግባር ዓመት መስሏል፤ ፀባይ የምንገዛበት። ጆሮዬ የቱንም ያህል ቢረዝም፡ በእግሮቼ ኣውራ ጣት ቆሜ ብንጠራራም፡ ከገመትኩት አካባቢና ድንበር 7000 ማይልስ ርቆ ዲሲ ላይ ጠቢቡ ሳይሆን ጠባቡ ሰለሞን ከተኮሳት ጥይት በስተቀር፡ የሰማሁት ኮሽታ፣ ያየሁት ብልጭታ የለም። እኛ ሳንተኩስ ቀኑ ተተኩሶ ዓመቱ ተጋመሰ። ነው ወይስ- ዘመኑ ሰልጥኖ፣ መሳሪያውም ዘምኖ – ታንክ እና ክላሹም አንደሽጉጡ ሳይለንሰር (silencer) ተገጠመለት? 

ጓበዝ፥ ብዙ ከማውራት ትንሽም ብትሆን የአቅምን መስራት ይበጃል – ያስከብራል። የመሀሉ ጦር ደፍሮ ለጨበጣው ሲቁነጠነጥ፡ እኛ “አቅም አለን” ካልን- ዳር ሆነን ለቀናት ቢያንስ ለሰዓታት የተኩስ ሽፋን መስጠት ይሳነናል? አለበለዚያ፦ መድረኩ ስለቀረበ ብቻ ሀ፡ብሎ አፍን መክፈቱ ሌላ ትርጉም እስካልተሰጠው ድረስ ለጠላት ማዛጋት ለወዳጅ ማዘናጋት ነው። አሁን ይበቃል። እውነትን ተናግሮ ህዝብን ወደ ኣንድ አቅጣጫ መመለሱ፡ ሀይልን አጠናክሮ ትግልን ያጎለብታል፣ ድልን ያቀርባል። ልብ ሳይኖረኝ አፌን ከፍቼ ሀ-ብል፡ ማን ግድ ሊለኝ?

ይውጣ ይወጣ … እግሬ ይዛል በእርምጃው
ከሷ አይብስም … ሰባ ደረጃው

የዛሬ ፅሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት፡ የአንድነት ሃይሎች በድፍረት የቆረጡለትን- ተመልሶ አደባባይ የመውጣት ወሳኔ ላደንቅ እወዳለሁ። እርግጥ ነው የተከፈለውና የሚከፈለው መስዋዕትነት ከባድ ነው። ሆኖም ግን፡ ለእናት ሃገር ሺ ጊዜ ቢሰለፉላት፣ እግር ቢዝል – ቢደክምላት ያንስባታል እንጂ አይበዛባትም። የሶስት ሺህ ዘመን ማንነትን፣ የአብሮነት ፍቅርንና አንድነትን ለመጠበቅ ሲባል፦ ሰባ አይደለም ሰባ ጊዜ ሰባ-ሰባት ደረጃ ይወጣል፤ ሰባ አይደለም ሰባ ጊዜ ሰባ-ሰባት መሰናክል ይዘለላል።

መጣሁ ከኮሪያ ይዤልሽ ሰዓት … ይቀጥላል

የዘፈኑ ስንኝ ትርጉም ሙሉ በሙሉ የዚህ ፅሁፍ ፀሀፊ እንጂ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከግጥሙ ደራሲም ሆነ ከዘፋኙ ፍቺ ጋር መስተሳስር የለውም።

Comments are closed.