
By Admin
የቀን ተረኛው ነፍስ … ሲዋከብ አርፍዶ
ወዲህ ሲል ፡ ወዲያ ሲል … ግሎ ላቡን ማግዶ
ጀንበር በጨረቃ … በፅልመት ተሳዶ
አውሬ፣ ጂኒ ሲነግስ … ደጅ ቀፎ፣ ደጅ ከብዶ
በድካም ሲባጎ … እንቅልፍ ተቀስታ
የብርሃን ፍጡር … ቆስሎ በሽልብታ
ምድር እረጭ ብላ … ሰማይ ኮከብ ለብሶ
ዥጉርጉር ወገኛው … አፈር ህዝብ ተማስሎ
በእፎይታ ድባብ … ድፍርስ አይኑን ከድኖ
ማልዶ እስኪነቃ … ዳግም ለህይወት ፍልሚያ
ሲያስታምም ትክተቱን … በትራስ ላይ ኩርፊያ
ላየው ተአምር ሲያሰኝ … ሯጭ፣ ተወንጫፊ ስጋ
በአንሶላ ላይ ሰክኖ … ተዘርሮ በአልጋ፤
ለካስ …
በማሾ፣ በሻማው … በአዳም ጥበብ ር’ቀት
በአምፑል፣ በፋኖሱ … በሰው ሳይንስ ምጥቀት
ንግሰት መከልከሉ … ግርማ መቀማቱ
ቆሽቱን አሳርሮት … ሲከስል ኖሮ አንጀቱ
ያረገዘውን ቂም … ሊሸከም ተስኖት
ምሽት ሲያምጥ እሳት … ሊገላገል ወልዶት፦
ሳትዳረስ ንጋት ምደሪቱን ሊያፈካት … በእግዞይታ ወ’ይኔ
ሲተፋው እሳቱን ሊያነፍረው ጥሬውን … ግሞ ለብሶ ወኔ
ጢሽ!ም በስሎ በፍም … እስኪሰማ ዷ! ድው! ግምምም!
ነበልባል ለብልቦት የጥይት ኡኡታ … እስኪቀልጥ፣ እስኪግም
በ “እንዲህ ነበር ያኔም ” … ፍጡር ተጃጀሎ
ንቃት፣ ጥንቃቄ … በወቅት ሸማ ታ’ጅሎ
ተማግዶ ቤት፣ አጥሩ … አረር ሲፈናጠር
እግር አልባው እሳት … እንደ ንስር ሲበር
ነገር ካበቃለት … ጀምሮ መጠርጠር
ንቃትን ጨርፎ … ገሚስ እሱነቱ በሰመመን ታብቶ
ድንብር ግትር ሲል … በደመ-ነፍስ ሩጫ ፍጡር ዋሻ ሽቶ
ስንት ጉድ አሳየን … ልንስቅ፣ ልናለቅስ
የበቅሎው ቤት እሳት … የግንቦቱ ድግስ፤
የሽብር ጥቁር ከል … ብሩህ አእምሮን ጋርዳ
ፆታ፣ ርህራሄ … ጠፍተው በየተራ
ታይቷን ነጥቆ ከሚስት … ድንጉጥ አባወራ
አስገብቶት ቀኙን … ሲጠበው ለግራ
ሲገፍ የውስጥ ልብስ … አቤት! የጭንቅ ሥራ …
ባርኔጣ ስትጎትት … መነፅር ላይጠቅማት
እንደ ስካርቭ ጠምጥማው … የባሏን ክራቫት
እንዳልተዋቀረው … አጥንት እንደሌላት
እግሯ አልቆም ብሎ … እማወራ ጨንቋት
ስትሳብ በምድር … እንሽላሊት አርጓት …
አቤት! አቤት! አሉ … አያቴ አቤት! አቤት!
በጣር፣ በአውጪኝ ነፍስ … ሲውተረተር ፍጥረት
ታሪከኛው ግንቦት … ስንቱን አየንበት፤
በእሳቱ ኮማንዶ … በአረሩ ፋኖ
እግሩ ሙዚቀኛ … አይኑ የእውር ሆኖ
በረንዳ ላይ ቆሞ … እንዳይሮጥ ዕርቃኑን
የሃያው ጎረምሳ … ሲያማርር እድገቱን
ሲመኝ ጨቅላነቱን…
እራፊ “ሆት፡ፓንት”ዋን … ብቻ እንደታጠቀች
ከወገብዋ በላይ … እንደተፈጠረች
ጉች፣ ጉች አንዳለች
ብቅ ስትል ቢያያት … እጆችዋን አጣምራ
አካሏን ልትደብቅ … እህት-ዓለም አፍራ፦
ሳይዘፍኑ ደናሹን … ገላውን አርቆ
ዘሎ ወደ እህቱ … ወገቧን ተጣብቆ
ከሰጠችው ታጥቆ … ሊጠፋ፣ ሊመንን
በእናት፣ በአባታቸው … በኣርባ-አራቱ ታቦት ሲገዝት፣ ሲለምን
እሷም ልትራራለት … ልትሆነው ያቺን ቀን
አሻፈረኝ ብላ … ፍጹም ብትለመን
በኣስር ጣቷ ስትስብ … ስትገፋ ወደ ላይ
እሱም ሲተናነቅ … ቁልቁሉን ከእጇ ላይ
በርትቶ ጎትቶ ቢያደርሰው ከምድር … ሞት የሞቱን ስቦ
ትግሉ አንዳይማረር ሊሸመግል ሊዳኝ … ይመስል አስቦ
ፍንዳታው ቢያቀልጠው … አርገፍጋፊ ድምፁን በብርሃን አጅቦ፦
እርሱም ሳይታጠቅ … እርሷም እዛው ጥላው
ለአንዳቸውም ሳይሆን … መከረኛ ቁምጣው
እርቃኑን ሲከንፍ … ጭንቀት አስደንብራው
በዋይታ እያጀበች … እህቱም ከኋላው
ከተረፉም ከእሳት … ስጋችው ሊታኘክ፣ የሰው አይን ሊበላው
ቀድሟት ከደጅ ወጣ … አልቀረም የፈራው፤
ፍጡር መተንፈሱ … ህልወናው ልሞ
ህመምተኛ ድኖ … ጤነኛም ሰው ታሞ
ሴተ-ላጤ ቅርሷን … አባወራም ሚስቱን እንደ ጉድፍ ጥሎ
ነፍስ እየመዘነች … ከሜዳ ሲበተን፣ ሲፈስ እንደ ቆሎ
እንደ “እሳት-አደጋ” … አባ-ዲና፣ መርማሪ
ከጭንቅ መንደር ውሎ … የደላው ሰርሳሪ
በአንድ ጀንበር አጥቦ … የደንባሬን ጉያ
ሳይመርጥ የጠመመ … የዛገ ማጥለያ
ተሸክሞ ሲሮጥ … አሸክሞ አህያ …
ታሪከኛው ግንቦት
ሰንቱን አየንበት!
ተራፊ ሲያለምህ … ትርፈቱን አድንቆ
ወፈፍ ያደረገው … በላንቃህ ነበልባል፣ በሽብር ሸብርኮ
ዛሬ ሲያስታውህ … የብርክ፣ ምጡን ግግር ከእላዩ ፈቅፍቆ
ስንቱ ይፈግ ይሆን … የታሪክ ድራማ ድርሰትህን አድንቆ?
ስንቱስ አቄመብህ … ሊያስብህ በእንባ ታድሎት ሰቆቃ
እሳትህ አላምጣ … ፍርግርግ ምሰሶ፣ ማገሩን አድቅቃ
ያስጠላችው ሸራ … ጣሪያ ቆርቆሮውን፣ የአፈር ምርጉን ነጥቃ?
በወቅቱ፥ መታሰቢያነቱ ለበቅሎ ቤት ጉዳተኞች የተሰጠ።
(*የአፈር ምርግ = ስጋ = የሰው አካል)
1983 ዓ.ም.