
By Admin
መቼም ለጠላትም ይሁን ለወዳጅ ብቻ ከጦር ሜዳ አካባቢ ድንገት ሽው የሚል የወሬ ነፋስ እንደ ትልቅ ወጀብ ልብን ያናውጣል። እኔም በጉጉት ከምጠብቀው ከሰሜኑ የጦር ቀጠና ደንገት ዱብ ያለውን የአቶ ኤፍሬም ማዴቦን “ከዊኣ እስከ ኦምሀጅር“ የሚለውን ጽሁፍ ስመለከት፡ ልቤ በደስታ እየዘለለ ፦ ትርጉሙ በቅጡ ባይገባኝም የሐረር ጓደኞቼን ቃላት ተበድሬ “አብሽር ተባሽር“ አልኩ፡ የሁለቱን እጆቼን መዳፍ እርስ በርስ እያፋተኩ። ለወትሮው ለሰዓታት ሳይቆረቁረኝ፣ ሳይሰፋ-ሳይጠብኝ የምቀመጥበት ወንበር አልመች ያለኝ ይመስል መቁነጥነጥ ጀመርኩ። ወዲያውም፥ ሰው እስቲ ለወሬ እንዲህ ይቸኩላል ብዪ እራሴን ታዘብኩና፤ የጓጓሁለትን ጵሁፍ ማንበቤን ቀጠልኩ።
ኣንደኛውን ምዕራፍ አልፌ ወደ ሁለተኛው፡ ሁለተኛውን ጨርሼ ሶስተኛው ላይ ስደርስ፡ ፀሀፊው “ለሁለት ቀን ከግማሽ የተጠራቀመ እንቅልፍ ይዞኝ ጭልጥ አለ ሲሉ“ ቀና መሰለኝ አእምሮዪ ተሰናበተኝ። በእንቅልፍም ባይሆን በሃሳብ እርሱም ይዞኝ እልም አለና፦ የኤርትራን (የሻቢያን) የትግል አጋዥነት አልፎም የትጥቅ ትግሉን አስፈላጊነት አስመልክቶ ዲያስፖራው በየ ሶሻል-ሚዲያው የሚያደርገውን እንካሰላንቲያ ማሰላሰል ጀመርኩ …
ከሁሉ በፊት ግን “ዲያስፖራው ቢጮህ ባይጮህ ምን ለውጥ ያመጣል? ትግሉ እንደው ያለው ሃገር ወስጥ ነው“ ለሚሉት ግለሰቦች ጥቂት መልዕክት አለኝ። ካልተወሻሸን በስተቀር፥ ዛሬ’ኮ የወያኔ አለቆች ስጋት፦ ለትግል ጦር ሜዳ መግባት ሳይሆን ለስብሰባ አውሮፓና አሜሪካ መጓዝ ሆኗል። እግር በእግር እየተከታተለ የሸመኑትን የውርደት ካባ የሚያለብሳቸው “የዲሲ ግብረ-ሀይል“ አንዱ ማሰረጃዪ ነው። የወያኔን ፋሽስት እንደ ሰሜን ኮርያ መንግስት ከዓለም ተገልሎ፣ በራሱ ግዛት ተወስኖ፣ “የግቢ አንበሳ፤ የውጭ ሬሳ“ ሆኖ እንዲኖር ያስገደደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማዕቀብ ሳይሆን የዲያስፖራው መረብ ነው። ስለዚህም ሲባል ከድንበሩ ባሻገር ያለው ሀይል የራሱን ሚና አስመልክቶ ለሚጫወተው ትግል ተገቢው ዕውቅናና ክብር ሊሰጠው ይገባል።
የሀገራችንን ተጨባጭ ፖለቲካዊ ቀውስ በተመለከተ አፋጣኝ መፍትሔ ለማምጣት፡ የሰላማዊው እና የትጥቅ ትግሉ አስፈላጊንት፡ በአንድ የጦር ሜዳ ላይ ለሚመዘገብ ድል የምድር ጦሩ እና የአየር ሀይሉ ከሚኖራቸው ተደጋጋፊነት ተለይቶ የሚታይ አይደለም። እያንዳንዳቸው በጥምረትም ሆነ በተናጥል ለጋራ ድል የሚጫወቱት ወሳኝ ሚና አላቸው። ከዚህም ባሻገር፡ እንደ እኔ የግል ዕምነት፡ ባርነት እና አርነትን የሚያመሳስላቸውና ኣንድ የሚያደርጋቸው ብቸኛ ባህሪ ቢኖር ሁለቱም የሚፀነሱበት ማህፀን የጠመንጃ አፈ-ሙዝ መሆኑ ብቻ ነው።
ትላንት፦ “ምነው የግንቦት 7 ታጋዮች ውጊያውን ከአዳፍኔ ወደ ጐራዴ፣ ከጥይት ወደ ቀስት ለውጠውት Robin Hood ሆኑ እንዴ? ድምፅ ጠፋ“ ብለን ለለውጥና ለውጤት የቸኮልን ሰዎች፡ ዛሬ አመራሮቹ አስመራ ገቡ የሚለውን ወሬ ስንሰማ “እሰይ ፀሎቴ ሰመረ … እሰይ ፀሎቴ ሰመረ፥ ለ … ነግሬው ነበረ“ ብሎ ሊያዘመረን እንጂ ሊያላቅሰን አይገባም። ኤርትራ መውረድ ወያኔን ማውረድ ሆኖ ባያስፈነጥዝም፡ ኣንድ- ያውም ትልቅ- እርምጃ ነውና ሊታገዝ ይገባዋል። እርግጥ ነው በትግሉ አካሄድ ሁላችንም ጥርጣሬ አለን። የእኔ ስጋት ከግንቦት 7 ጀርባ የምመለከታት ኤርትራ ሳትሆን ከኤርትራ ኋላ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሊያተራምስን የሚተራመሰው የዓረብ መንጋ ነው። ነገር ግን ይህ ትግል ኢትዮዽያውያን ነን ለምንል ዜጎች ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው። ይህ ወቅት የህዝባችን መከራና ስቃይ ለሚሰማን ባለ-አደራዎች ታሪክ የምናስታውስበት ሳይሆን ታሪክ የምንሰራበት ወሳኝ ሰዓት ነው። የኢኮኖሚ ጠበብቶቹ: bygones are bygones, to take account of them in current decision is to court disaster ይላሉ። ያለፈው አልፏል፤ በዛሬው ውሳኔ ላይ ያለፈውን ማስታወስ ቀውስን አንደመጋበዝ ነው – ነው ነገሩ።
ካለኝ የጊዜ ስስት አኳያ፡ በአጭሩ በኤርትራ በኩል የሚደረገውን ትግል አክርረው የሚነቅፉትን ሰዎች ኑ ተመለሱ የወያኔ መንግስት አስቀድሞ በታትኖታልና የሰሜኑ ትግል የሚበትነው ሃገርና ህዝብ የለም ስል፤ ዛሬም ከግንቦት 7 በላይ የአንድዪ ሰማይ ካልሆነ ነፍስ እና ህይወት የለም ለሚሉት ደጋፊዎችም ቃል አለኝ። ከሻቢያ ዕገዛ የሚተርፈን መዝዘ እና አበሳ ነው ያለውን ሁሉ “ወያኔ! ባንዳ!” እያልን ከመፈረጃችን በፊት እስቲ የየራሳችንን ቦታ እንወቅ። ፖለቲካችን እንደ ግብረ-ሰዶማውያኑ ሰንደቅ ስድስት ቀለም ይዞ አልጠራ፣ አንድ አልሆን ያለው፥ ታቦት ለምኖ-ተሸክሞ አሊያም ታቦት ሸጦ ከሃገር የወጣው ሁሉ አውራ ፖለቲከኛ ሆኖ ነው።
ፅሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት ግን ወደ በረሃ ለወረዱት የግንቦት 7 መሪዎች ላሳዩት ጅምር መስዋዕትነት አክብሮቴን ሳልነፍግ፥ አንድ ነገር ማለት እወዳለሁ። በተፈጥሮ ህግጋት እየሳሳ ያለው የሻቢያ ቁንጮ ሳይመለጥ፣ ሳያመልጥ ከወንዙ ባሻገር ወደተመለከታችኋት ምድር በጊዜ “ግፋ በለው!” ማለቱ ይበጃል። አቶ አርከበ ዕቁባይ በሚቀጥሉት ኣስር ዓመታት ውስጥ ኢትዮዽያ የአሰብን ወደብ ተጠቃሚ ትሆናለች ብለው ሲናዘዙ፡ ውስጥ ለውስጥ ከጋሜ (ከትናንሾቹ) የሻቢያ መሪዎች ጋር እየተጣጣሉት ያል ገና ያልተበላ ፖለቲካዊ ዕቁብ እንዳለ አመላካች ይመስለኛል።
አለበለዚያ ግን፦ አውራው ተሰውሮ፡ እኛም ሳንሻገር፡ እነሱም ከጀሌው ተጃልሰው “ከዊኣ እስከ ኦምሃጀር“ በሚል መቅድም የተከፈተው ገድለ-ግንቦት ከ-starbucks coffee እስከ ቡና ፍረወይኒ በሚል መድብል እንዳይደመደም።