Post

አሰብኩና . . .

አሰብኩና . . .

By Admin

ህወሀት አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ ሳይሆን አዲስ አበባ ከገባ ብዙም አልቆየ።  አንድ የኣንደኛና የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የነበረ የሰፈር ጓደኛዬ ከትምህርት ቤት ለተሰጠው የቤት ሥራ የሚሆን ኣንድ ስዕል እንድስልለት ለመነኝ። ምን አይነት ስዕል ነው የምትፈለገው ስል ጠየኩት። “የሆነው ይሁን ” አለ ግን ብቻ መምህሩ እንዳዘዙት የእርሱ የራሱ የእጅ ስራ ውጤትም መሆን እንዳለበት አስረዳኝ። እሺ ብዬ ቃል ገብቼለት ጠዋት እና ማታ እንዲጨቀጭቀኝ ስላለፈለኩ ቶሎ ልገላገለው አሰብኩና ተያይዘን ወደ ቤት ገባን።

በወቅቱ እጄ ላይ ከነበሩኝ በጣም ጥቂት የስዕል መነሻ ሀሳቦች መካከል ስናማርጥ፥ አንዱ ወረቀት ላይ አይኑ አረፈና ይህንን ይዤው ካልሄድኩ ሲል አመረረ። ያኔ ገና በነጥብ እና በቀጥታ መስመር መካከል ያለውን ዝምድና እንኳን በቅጡ ሳላስተውል፣ ጣቶቼ ልሙጥና ነፃ ጥምዞችን (smooth and open curves) ሳይማሩ “የማያፍር ደፋር!” ሰዓሊ ሆኜ የሞነጫጨርኩት የመጀመሪያዬ ካርቱን ነበር። ገና ለአቅመ-እስራት ያልደረስን ልጆች ብንሆንም ብዙም ነፃነት አልተሰማኝምና – ኣንድ እጅ በአንድ ቅጽበት መቀስና ሽጉጥ የመጨበጡን ምስጢር፣ የጋብቻ ቀለብቱን፣ የሰዓት (የዘመን) መቁጠሪያውን፣ የኮቱን እጀታ ጥበብና በአጠቃላይ የስዕሉን ይዘትና ትርጉም በማስረዳት መምህሩ ስዕሉን ባይወዱት ሊያስከትልብን የሚችለውን ችግር ላሳየው ሞከርኩ። ጓደኛዬ ግን ስጋቴን መመልከት ተስኖት እንዲያውም ያንን ስዕል ብከለክለው ጥሩ የሰፈረ ጓደኝነታችን አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል እርግጠኛ የሆንኩባትን ስጋት በበወፍራም ፊቱ ገፅ ላይ ባየኋት ያልተለመደች ኩርፊያ አቀበለኝ። በልጅነት እና በጅልነት መካከል የፊደላት-ቦታ እንጂ የሆሄያት ለውጥ የለምና አልከለከልኩቱም – ስዕሉን ይዞት ወደቤቱ ሄደ።

ከጥቂት ቀናት ቦሃላ በዚሁ ጓደኛዬ የመኖሪያ ቤት አካባቢ ሳልፍ ተገናኘንና ለሆነች አጭር ደቂቃ እንደሚፈለገኝ ነገሮኝ ወደ ቤታቸው እንድገባ ጋበዘኝ። የመማሪያ መፅሀፍትና ደብተሮቹ ከተደረደሩበት ጠረፔዛ ላይም አንድ ቦርሳ ነገር ሲፈትሽ ቆይቶ አንድ ወረቀት መዘዘና እየሳቀ ተጠገግቶ አሳየኝ። ያ ትምህርት ቤት ይዤው መሔድ አለብኝ – ከልሰጠኸኝ ብሎ ያኮረፈኝ የራሴው የካርቱን ስዕል መነሻ ሀሳብ ነበር። ለምን እንዳልወሰደውና ለመምህሩ አንዳላሳየው ስጠይቀው የሰጠኝ መልስ ግን የማላውቀውንና ያላሰተማረኝን የጓደኛዬን አስተማሪ ዛሬም ድረስ በመገረም እንዳስታወሰው አድርጐኛል። በእርግጥ ጓደኛዬ ስዕሉን እሱ ራሱ እንደሳለው አስመስሎ ለአስተማሪው አስረክቦት ነበር። ከሁለት ቀናት ቦሃላ አስተማሪው በተመደበላቸው የማሰተማሪያ ጊዜ (period) ወደ ጓደኛዬ ክፍል ሲመጡ ግን ወረቀቱን ይዘውት እንደተመለሱና የስዕሉን ሃሳብና መልዕክት እንደጠየቁት ነገረኝ። እርሱም “ስጠኝ-አልሰጥህም / ይገባኛል-አይገባህም ” በሚል ክርክር የተነሳ የተደራደርንባቸውን ሀሳቦች በሙሉ በሚገባ ከገለፀላቸው ቦሃላ፤ ለዛ የቤት-ስራ ከፍተኛውን ወጤት (mark) እንደስጡት፣ ነገር ግን ስዕሉን አርሞ የሚገባውን ትክክለኛ ዋጋ (mark) ሊሰጠው የሚችለው ብቸኛው መምህር ጊዜ (Time) ብቻ መሆኑን እንዳስረዱትና ስለዚህም ወረቀቱን በጥንቃቄ ሊጠብቀው እንደሚገባ መክረው መልሰው እንዳስረከቡት አጫወተኝ። እኔም “በል ስዕሌን መልስ – አምጣ ” ልለው ውስጤ ክፉኛ ተፈታተነኝ። ቦኋላ ግን በኣንድ ነገር ተስማማን። ኮፒ አድርጎ ሊሰጠኝ። እናም ይኸው ከብዙ አመታት ቦሃላ ያ ስዕል እጄ ገባ። እጅግ በጣም አመሰግናለሁ B!  

ዛሬ ትዳሩም ፈርሱዋል! ሙሽሪትም የጋብቻውን ቀለበት ሸጣ የዓባይን ቦንድ ገዝታበታለች! “ብሔር ብሔረሰቦችም ” ላይ የዳመነው የመከፋፈልና የዘረኝነት ደዌ አካፍቶ ብቻ ያባራ ይመስላል። እንሆ፦ በመምህር ጊዜ እርማት መሠረት እኔና ጓደኛዬ በኣንድ ስዕል ተወዳድረን በ Dgrade ተሰናብተናል። አዎ ክፉኛ ተመተናል! ያም ሆኖ ግን ፈተናውን አልፈን ደስ ብሎን ስቀናል!

እና ታዲያ ያንን የመጀመሪያዬን ካርቱን ሳይቦረሽ – ሳይቀባ ዛሬ ፖስት (post) ለማድረግ ስዘጋጅ፡ አንድ ትንሽ ነገርም አብሬ ማለት እንዳለብኝ አሰብኩና ስዕሉን መመልከት ጀመርኩ። ዓይኔ ብሌኑ ማግኔት የሆነ ይመስል አሁንም አሁንም ዝም ብሎ ወደ ብረት ቀለበቱ ይሳባል። መቼም ለምን የወርቅ ቀለበት እንዳላልኩ ይገባቹሀል። ታዲያ ምን ልበል ብዬ አሰብኩና . . .  

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ (ነፍስ ይማር) በአንድ ወቅት *ዩኒቨርስቲ ገብቶ ለዓመታት ከመማር ከኤርትራው ፕሬዚደንት ከአቶ ኢስያስ አፈወርቄ ጋር ለሰዓታት መቀመጥ ይሻላል ያሉትን (ቃል) አሰብኩና . . .

የህወሃት መንግስትና የስርዓቱ ደጋፊዎች እንዲህ ለረባ ላረባው፣ ከአደባባይ መድረክ ሽንፈታቸው እስከ ጓዳ አልጋ ስንፍናቸው ሻቢያንና የሻቢያውን መሪ ተጠያቂ በማድረግ ብክንክን ሲሉ ውለው ማደራቸውን አሰብኩና . . .

በአንድ ወቅት አቶ ኤልያስ ክፍሌ ኤርትራ ለኢትዮጵያ የነፃነት ተዋጊዎች ልታበረክት የምትችለውን የሎኬሽንና ሎጂስቲክ (location and logistics) ድጋፍ አስመልክቶ ላቀረበላቸው ጥያቄ ፕሬዚደንቱ *የወያኔን መንግስት ለማስወገድ የእኛ መንግስት ድጋፍ አያስፈለጋችሁም (እዛው) ሱሉልታ ጫፍ፣ እንጦጦ ተራራ ላይ ተደራጅታችሁ ዘረኛውን አገዛዝ ገፍትራችሁ እንጦረጦስ ልታወርዱት ትችላላችሁ ሲሉ የመለሱትን አሰብኩና . . .

ዛሬ ግፍና በደል የሰለቻቸው የደጅ-አዝማች ባልቻ ልጆች ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በማያያዝ ያስነሱት ሰላማዊ ተቃውሞ ስርዓቱን ከመሰረቱ እንዴት እንዳናጋው አሰብኩና  . . .

የእኚህ ሰው ተሰጥዖ መለኮታዊ በረከት ወይንስ ምድራዊ ዕውቀት? ስል ጠየኩ። በርግጥም ፕሬዚደንቱ ወያኔን እጃቸው መዳፍ ላይ እንደተቀረፀ ካርታ ጠንቅቀው ያውቋታል ማለት ነው? ብዬም አሰብኩና … አሰብኩና … ማሰቡ ሲሰለቸኝ ከላይ ያለችውን ከሁለት ኣስርት አማታት በፊት የተሳለችውን የመጀመሪያ ካርቱኔን ላደረሰኝ የሰፈር ጓደኛዬ በድጋሚ ምስጋናዬን አቅርቤ ሀሳቤንም ጽሁፌንም ደመደምኩ።

*ትክክለኛ የሀሳቡን ይዘት ሳይለቅ በፀሃፊው ቃላት የተገለፀ

Comments are closed.