Post

አቅላይነትን ፈርተህ እንዳትቀል!

አቅላይነትን ፈርተህ እንዳትቀል!

By Admin

ጠቅላይ ሚንስትሩ የሙሴን በትር ጥለው የሳኦልን ጦር ጨብጠው አየሁ። ደግሞ ትንቢት ነው ብላችሁ የሌለኝን ፀጋ እንዳታሸክሙኝ ፤ በህልሜ እንጂ እኔ ትንቢተኛም ትዕቢተኛም አይደለሁም። ይኼኔ፥ ሶሻል ሚዲያው ተሽቀዳድሞ፥ እኔ እንኳን በሰዓታት እንቅልፍ ያላየሁትን “ሀይል የእግዚአብሔር ነው” ሲል ለጠቅላይ ሚንስትሩ ዛቻ መልስ የሰጠው እስክንድር ነጋን በሰከንድ የ-online ሽልብታ አልሞ፥ ‘የጨበጡትን ጦር ወርውረው እንደ ዳዊት ለጥቂት ሳቱት ‘ ይል ይሆናል። ቢልስ ምን አለበት? ጦራቸውን ባይወረውሩም የፖሊስ ኮማንደራቸውን ልከው የለ።

እኔ ግን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን፥ በህልሜም ባይሆን በእውኔ፦ “በህወሃት ዘመን እንኳ ጋዜጣዊ መግለጫ ተከልክሎ አያውቅም ” ሲል አዳምጬዋለሁ። ህወሃት ገደለ፥ ኦህዴድ አስገደለ፣ ህወሃት ባንክና ንብረት ዘረፈ፥ ኦህዴድ አዘረፈ፣ ህወሃት መሬት፣ ቤትና ኮንዶሚንየም ነጠቀ፥  ኦህዴድ አስነጠቀ  … አሁን ነው  “ አዲስ ንጉስ እንጂ … ለውጥ መቼ መጣ? ” ብሎ መዝፈን።

አንድ እምነት አለኝ፦ በልደት ቀን መዋቢያ የሚሆንን ውድ ክራቫት ከሰጠ መሰሪ ወዳጅ ይልቅ፥ መገነዣ የሚሆንን ልጥ አርሶ ያመጣ እውነተኛ ጠላት የከበረ ስጦታን አበርክቷል። ምክንያቱም የእውነት ዋጋ ከብርና ዕንቁ እጅግ ይልቃልና። 

ሰፊዋን ኣዲስ-አበባ በኣንድ የጐሳ ጅማት አጥብበው እየዘመዘሙ፣ ነዋሪዎቹዋንም በሁለት ወገን ከፋፍለው አንዱን እያሞላቀቁ ሌላውን  እያሸማቀቁ፥ ጠቅላይ ሚንስትሩም ሆኑ ከንቲባቸው አደባባይ ላይ ቆመው “ከተማዋ ሀገራዊ አልፎም ኣህጉራዊ ናት ” የሚል ግብዝ ስብከታቸው፣ ከፕላስቲክ እንደተቀረፀ የፍራፍሬ ክምር፥ የፎቶ ቤት ጠረፔዛ ከማድመቅ ባሻገር የየትኛውንም ተምልካች አንጀት አላውሶ፣ አምሮት ቀስቅሶ አፍን ጠብታ ምራቅ አይሞላም። ለወሬ ወሬማ በቀን ኣስራ-ሦስት ጊዜ አሳር ያበሉን መሪዎችስ “በቀን ሦስት ጊዜ ትበላላችሁ” ሲሉን አልነበረም?

ዶክተር ኣብይ አህመድ ቃልን ስጋ ማልበስ ቢሳናቸው እንኳ ተግባር ማላበስ ቢሞክሩ መልካም ነው። እንጠየፈው የሚሉት ዘረኝነት አረም ነው። ለይቶ በመንቀል እንጂ ሌላ አረም በመትከል አረምን ማጥፋት ደግሞ ከቶም አይቻልም። ምናልባት ይህቺ ፅሑፍ ከጆሮአቸው ብትደርስ፥ ጠቅላይ ሚንስትሩ ተሽቀዳድመው በኣዲሱ “አቅላይ” ብሔርተኝነት እንደሚፈርጁኝ አልጠራጠርም። ሀቁ ግን ይህ ነው፦ ኣንድ ህፃን ከመጠለያ አምባ አንስተው፣ “ሚልዮን” ብለው ሰይመው ወደ ቤተመንግስታቸው ስላገቡልን ምስጋና አቀርባለሁ እንጂ፥ ኣንድ ሚልዮን ህፃናት ከነወላጆቻቸው ከቤት ንብረታቸው እየተፈናቀሉ እነደ ጠጠር በየመንገዱ ሲበተኑ  እየተመለከትኩ ዝም ለማለት ሰብዓዊ ሞራልም ሆነ ኢትዮጵያዊ ግዴታዪ አይፈቅድልኝም።   

ደግሞስ መወቀስ ካለበት በ”አቅላይነት” የሚወቀሰው ማንው? የኢትዮጵያ ህዝብ? ኣዲስ-አበባውያን ወይንስ ጠቅላይ ሚንስትሩ እራሳቸው?

ሚልዮኖች ሲፈናቀሉ፣ ስብዓዊ ፍጡራን እንደ ቄራ እንሰሳ በጅምላ በካራ ሲታረዱ – አልፎም ሲሰቀሉ፣ በሁለት እግሩ የሚራመድ ኣውሬ ካልሆነ በስተቀር የሰው ልጅ ይፈፅመዋል ተብሎ የማይታሰብ፣ በእውኑ አለም ለመከወን ቀርቶ በድርሰቱም ምናብ ለመተውን እጅግ የሚዘገንን ግፍ ተመልክተን “ንጉስ ሆይ ይስሙን!” ስንል፥ የከተማና የገጠር ልጅ ወግ ተርከው፣ በዝንጀሮ ተረት መስለው “ኮሽ ባለ ቁጥር አትደንግጡ” ሲሉ ስጋታችንን ያቀሉታል። ጌድዮ ወርደው፦ ሴት ልጅ ተደፍራ፣ አስክሬኗ መሬት ለመሬት ተጐትቶ ያም ሳይበቃ ዛፍ ላይ ተስቅላ ተገኘች የሚል በእንባ የወረዛ ሰቆቃ ሲሰሙ “ለ-facebook likeለ-NGO ፍጆታ የዋለ አቤቱታ” አድርገው ያጣጥሉታል። ታዲያ አቅላዩ ማነው? የህዝቡስ ብሶትና ስቆቃ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ከ-“ኮሽታ” ያለፈ ስጋት፣ concern የሚሆነው ምን ደረጃ ላይ ሲደረስ፣ መቼና የት፣ ምን አይነት ግፍ ሲፈፀም ነው?

እንደ ራዕያቸው ሁሉ የዶክተሩ “አቅላይነት ” ድንበር ተሻጋሪም ነው። ትላንት ልንዋሃድ ዕቅድ ይዘናል ይሉዋትን ጐረቤት ሶማሌ፥ ዛሬ “በኣንድ ጣሪያ ስር ቁጭ ብላ ለመወያየት አይቻላትም” ብለው ማህበራዊ ትውፊቷን ያረክሱታል። ሲያሻቸውም ባህር አቋርጠው፦ ኣንድ-አንድ ባለፀጋ ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን የሚያስጠብቁት ለጉልበተኞች በቢልዮን የሚቆጠር ጉቦ በመክፈል ነው፤ አልያ ግን፥ ብሔራዊ ደህንነታቸውን ለመከላከል አቅመ ቢስ ናቸው የሚል ትርጓሜ በሚሰጥ ወግ ሳውዲን እና መሰልሎቹዋን ያቀሏቸዋል። እዚህ ላይ … ነገርን ነገር ያነሳዋልና … እያንዳንዱ ሀገር በየሃገራቱ የሚደረጉ መንግስታዊ መግለጫዎችንና ቃለመጠይቆችን በግልፅም ይሁን በስውር እያስቀዳ አስተርጉሞ በመረጃነት የሚያቀርብ የደህንነት ቢሮ እንዳለው፥ እንኳን የኢንሳ ሹም ለነበሩት ለእሳቸው ለእኔም አይጠፋኝም። ታዲያ ይኸን “አቅላይ” ንግግራቸውን አለመግረዛቸው ለምን ይሆን? ሰምተው ቢያኮርፉም ለምኜ አግባባቸዋለሁ ብለው ነው?

ከጠቅላይ ሚንስትሩ “አቅላይ ” ንግግሮች ሁሉ የተስማማሁበትና እውነት ነው! ስል ያመንኩበት ግን የእኛዎቹ ሶማሌዎች፦ “ስልጣን አንሶናል፥ ክፍፍሉ ፍትሀዊ ይሁን ” ሲሉ ለጠየቁት ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ነው። “አስተውሉ ... ” አሉ  ጠቅላይ ሚንስትሩ፦ “የቀድሞ ስልጣናችሁ ከትራንስፖርት ሚንስትርነት ዘሎ አያውቅም … የትራንስፖርት ሚንስትር መሆን ደግሞ … “ ብለው ሳይጨርሱት ለወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ተሸማቅቄ ጆሮዪን ደፈንኩት። ቦኃላ ግን ወይዘሮዋ ብአዴን መሆናቸውን ስረዳ፥ እኔ ምን ቤት ሆኜ፣ ጆሮዬን ደፍኜ የጠቅላይ ሚንስትሩ “አቅላይ ” ንፅፅር አመለጠኝ ስል እጅግ ቆጨኝ። አዎና! ብአዴን ሆዱ ብቻ ሳይሆን ትከሻውም ሰፊ፣ ቆዳውም ወፍራም ነው። ውርደት አይሰማው፣ ንቀት አይገባው። እንደ-እኔ እንደ-እኔ … ከራስ ውርደት አልፎ የወገን መናቅ ሳይቆረቁረው ለዘመናት የሚሸከም ትከሻ፥ የእንጨት ቀንበር አይከብደውምና፥ የኣማራ አርሶ አደር ለብአዴን ልሒቃን ውክልና ስጥቶ በመንግስት ቢሮ ከሚያስቀምጣቸው እንደ በሬ ጠምዶ ቢያርስባቸው፥ በእጥፍ አምሮቶ፣ ነግዶና  አትርፎ ይከብራል፣ ይከበራል ብዪ አስባለሁ። ያኔ ደግሞ በሂደት ክልሉ ብቻ ሳይሆን ሀገርም ይለወጣል።

ብአዴን፦ “የታሪክና የቦታ ሽሚያ ውስጥ አልገባም ” ሲል ስውር ግላዊ ስግብግብነቱን በህዝባዊ ስልት ለመተርጎም ከመንተባተብ፥ ከመንግስት ባንክ እስከ ግለሰብ bar፣ ከኣዲስ-አበባ መስተዳደድር እስከ ሚንስትሮች ምክር ቤት ያለውን እብድ የሚያደርግ መድሎ ለመቃወም ፊደል ቢቆጥር ይሻለዋል። ከ-40 በ-60 የኮንዶሚንየም መስኮት ባላነሰ መነፅር አይናቸውን ጋርደው፥ በመዘጋጃም ይሁን በመፀዳጃ ቤት በምክትልነት ሳይሆን በ-ም-ል-ክ-ት-ነ-ት የተዘፈዘፉት ተወካዮች፥ ስፍራቸውን በፍቃደኝነት በመልቀቅ ለህዝባቸው ያላቸውን ተቆርቋሪንት በግዜ ማሳየቱ ይበጃቸዋል።

ጽሑፌን ሳጠቃልል ግን፥ ኣዲሰ-አበቤ ሆይ፦ “አቅላይነትን” ፈርተህ እንዳትቀል  “ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ! ” እልሃለሁ። አልያ ግን አሞሌ ነው ተብሎ መጣል ብቻ ሳይሆን፥ ኮብል stone ነው ተብሎም በመሐንዲሶቹ መረገጥም ይመጣል። በዚህም ሳይበቃህ፥ ዛሬ የለገዳዲ ትቦ ጠበቀ – ላላ እያሉ በፓርቲ conspiracy ከንፈርህን በውሃ ጥም እያደረቁት ይሉት አንደራሴዎች፥ ነገ በካራ ጉሮሮህን ሊሰነጥቁት እንደማይመለሱ አጥብቀህ ልትረዳ ይገባል። ወንድ ልጅ ሲሸና አብሮ ያልሸና አንድም ሰላቢ ነው ወይንም ስልብ ነው! እነ እንደ-ልቡ ሲሸኑ ቆሞ መታዘብ፥ አንድም ስልብነት አልያም ሰላቢነት ነው። ተሰለቦ “ስልብ” ከመሆን ደግሞ ሰልቦ “ሰላቢ” መባል እጅግ ይሻላል።

Comments are closed.