
By Admin
ሀገራችን ብዙ ወሳኝ ፖለቲካዊ ክስተቶችን እያስተናገደች ትገኛለች። አንዳንዶች ልማዳዊው በሆነ አጭር ገላጭ አባባል “ኢትዮጵያ መስቀልያ መንገድ ላይ ነች ” ብለው ይጠቀልሉታል። ለእኔ ግን መራመጃ ጎዳናው በዝቶበት የጥርጣሬ አደባባይ ላይ ቆሞ የሚናውዝ ሀገርና ህዝብ አይታየኝም። ጎዳናው መስቀልያ ሳይሆን መንትያ ነው። የነፃነት ወይንም የባርነት! የሞት – የሽረት! እንደ አቶ አባይ ፀሀዬ “ቃል” ከሆነም፦ “ልክ የመግባት!” ወይንም “ልክ የማስገባት!”
በዚህች ውስን ፅሑፍ የሰሞኑን የሀገራችንን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ክንዋኔዎች በሙሉ መዳሰስ የማይታሰብ እንደሆነ ሁሉ፥ አንዱን የድርጊት ምዕራፍ ከሌላው ለይቶና አጉልቶ ማውጣትም እንዲሁ አስቸጋሪ ነው። ያም ቢሆን ግን ትኩረቴን የሳቡትን ሦስት አብይ ክስተቶች እንደሚከተለው ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ።
አቡነ በለዓም?
“በዚያን ጊዜ የሴፎር ልጅ ባላቅ የሞዓብ ንጉሥ ነበር። እሱም የቢዖርን ልጅ በለዓምን . . . እንዲህም ብለው እንዲነግሩት ላካቸው፦ ከግብፅ ወጥቶ የመጣ አንድ ሕዝብ አለ። ይኸው . . . ደግሞም መጥቶ አፍንጫዬ ሥር ሰፍሯል። እነሱ ከእኔ ይልቅ ኃያላን ስለሆኑ እባክህ መጥተህ ይህን ሕዝብ እርገምልኝ … ምክንያቱም አንተ የባረክኸው ሁሉ የተባረከ፣ የረገምከውም ሁሉ የተረገመ እንደሚሆን በሚገባ አውቃለሁ። ” ዘኁልቁ 22
በጎንደርና በባህር-ዳር አካባቢ የተነሳውን የእምቢተኝነት ትግል ተከትሎ ብፁዕ ወቅዱስ ሊቃነ ፓፓስ አቡነ ማትያስ የሰጡትን መግለጫ ስሰማ፥ ከባርነት (ከግብፅ) ምድር ወደ አርነት የሚተመውን የእስራኤልን ህዝብ እንዲረግምለት የሞዓብ ንጉሥ ባላቅ በወርቅና በብር የደለለው የእግዚአብሔር ሰው – በለዓም – ትዝ አለኝ።
በእርግጥ ቤተክርስቲያን ራሷን ከሀጢያት እንጂ ከፖለቲካ ነጥላ እስትንፋስ ይኖራታል የሚል አምነት የለኝም። መንግስት በሀይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም ብለን ስንልም ቤተክርስቲያን ከፖለቲካ ታጥባና ፀድታ፣ ፍፁም ርቃ መቆም አለባት ለማለት ሳይሆን፤ ቤተክርስቲያን የሚኖራት ፖለቲካዊ አቋም ፍትሀዊ እንጂ ርዕዮተ-አለማዊ፣ ህዝባዊ እንጂ ድርጅታዊ ፍላጎት ላይ የተመሰረት መሆን የለበትም ወይንም እንዲሆን መገደድ አይኖርባትም ለማለት ነው። አነሳሴ ስለ ፖለቲካ እና ቤተክርስቲያን ዝምድና ለመተረክ ስላልሆነ በአጭሩ፦ ፖለቲካ፣ ሀይማኖትና ህዝብ ሊነጣጠሉ የማይችሉ አብረው የተገመዱ መሆናቸውን ላስቀምጥና ወደ ዋናው የፅሁፌ መንፈስ ልመለስ። በዚህ ርዕስ ላይ ሰፋ ያለ ትንታኔ ማንበብ ከተፈለገም Politics Is Not Sin To Avoid Practicing በሚል የቀረበውን መጣጥፍ መቃኘት ምክሬ ይሆናል።
አቡኑ በንግግራቸው መሀል “የሀገር ንብረት ” ለማለት ፈለገው “የሀገር ልማት ” በሚለው የህወሀት መሪ ቃል ተደናቅፈው ለመውደቅ ሲንገዳገዱ ብሰማ፥ “እኔን!” ለማለት ርህራሄው ቢጎድለኝም “እርሶን!” ብዬ ግብረገቡን ተከትዬ እስከመጨረሻው በትዝብት አዳመጥኳቸው። እንደው ለመሆኑ፦ አቡኑ ዘጠኝ ወር ሙሉ የት ነበሩ? በኦሮምያ ክልል “የሀገር”ብቻ ሳይሆን የፈጣሪም ንብረት የሆነው ሰው በመንግስት ታጣቂዎች ያለርህራሄ ሲፈርስና ሲቆረስ (ሲገደልና አካለ ስንኩል ሲሆን) በዝምታ ማለፋቸው ሱባኤ ገብተው ነው? ነው ወይንስ ለእኛ ያልተሰጠ፣ ለእሳቸው ግን የተገለጠ ከብሉይ እና ከአዲስ በተጨማሪ ሌላ ህሩይ ኪዳን ይኖር ይሆን? የኦሮሞውና የአማራው ደም ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ፣ መልካም መዓዛ ያለው የአቤል መስዋዕት ነው የሚል?
በእርግጥ ቤተክርስቲያን (የፕሮቴስታንት ዕምነትንም ይጨምራል) የህይወት እንጀራ (ክርስቶስ) የሚሰበክባት ቤተ-መቅደስ ሳይሆን የስንዴ ሽልጦ የሚጋገርባት ዳቦ-ቤት ከሆነች ከራርማለች። ብፁዕ ወቅዱስ ሊቃነ ፓፓስ አቡነ ማትያስ አደባባይ ወጥተው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሲያስጠነቅቁን፡ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለአብዛኛው ኢትዮዽያዊ – የመንፈሳዊ ዕምነት መሪ ሳይሆን የህወሀት ርዕዮተ ዓለም አክራሪ ነው የመሰሉት። የቀድሞው አቡን (ነፍስ ይማር) የብረት መስቀል ታጥቀዋል ብለን እንዳልተሸበርን ይባስ ብለው የዘንድሮው ብረቱን ጥለው ከእንጨትም ሳይሆን ከሰው አጥንት የተሰራ መስቀል ይዘው አሳቀቁን።
ዛሬ ለአቡኑም ሆነ እሳቸውን ለመሳሰሉት ባለረጅም ቀሚስ “ፌደራሎች” ያለኝ አጭር መልዕክት: ኑ ተመለሱ! በዚህ ጽሑፍ ገላጭ ምስል ላይ እንደምትመለከቱት፦ ጀርባችሁን ለገዳዮች ሰጥታችሁ፣ ፊታችሁን ወደ ህዝብ አዙራችሁ የአምላክን መንጋ ከጥቃት ተከላከሉ ነው። መስቀልን እንደ ድርጅት አርማ እያወለበለቡ፡ የተጨቆነን ህዝብ “አረፈህ ተገዛ” ብሎ መገዘት መናፍቅነት እንጂ መንፈሳዊነት ሊሆን አይችልም። በመሰረቱ መስቀል የመፈታት፣ የአርነት፣ ነፃ የመውጣት መስዋዕትነት ምልክት እንጂ የመገዛት፣ የባርነት፣ የቀንበር ተምሳሌት አይደለም።
ከተኮሱብን እንተኩሳለን
የሰሞኑ የለውጥ ረመጥ በትጥቅ ትግሉ በተደራጁ የፖለቲካ ተቋሞች ቢታገዝ (ልብ በሉ ቢታገዝ እንጂ ቢፐወዝ አላልኩም) ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን ሳስብ፡ ከቅርብ ርቀት በሚሸት የነፃነት መዓዛ እሰክርና አፌን ምራቅ ይሞላዋል። በእርግጥ በዚህ ወሳኝ ወቅት ማን ምን ሊሰራ ይገባዋል? የሚለውን ከመተንበይና ከመተቸት ይልቅ ማን ምን እየሰራ ነው? የሚለውን መመልከትና ማገዝ የበለጠ ይመረጣል። ሆኖም ግን፦ ከጥቂት ቀናት በፊት የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልከቶ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር አርበኛ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሰጡት መግለጫ ላይ “ከተኮሱብን እንተኩሳለን ” የምትለዋ አባባል እኔን አተኩሳኛለች።
አርበኛው ፕሮፌሰር እንኳን እርሶ እዛው እሳቱ ዳር ያሉት እኔ እንኳ በብዙ ሺህ ማይልስ ርቄ ሰዎቹ እንደተኮሱ ሰማሁ፣ ተመለከትኩ። ከመተኮስም አልፈው በቁጥር ሳይሆን በስፍር እየገደሉ’ኮ ነው?
እዚህ ላይ ብዙ ለማለት የሚያስችሉ ሀሳቦች ቢኖሩኝም ወቅቱ ሰላለሆነና ከእኛ ይልቅ ጠላትን የሚያንፅ፣ ከጠላት ይልቅ እኛን የሚያፈርስ መስሎ ስለታየኝ በይደር ማስቀመጡ አይከፋም። ብቻ ግን ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ . . . እንደሚሉት፤ እኔም ለወያኔ ያልሆነ ብረት . . . ብዬ ልለፎት። የትግራይ ምሁራንና ህዝብን በተመለከት ያቀረቡት ጥሪ ግን የእኔም ጩኸት መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ። በአጠቃላይ ሲታይ የዚህ ወንድም ማህበረሰብ ዝምታ እንደ ፈርዖን ቸልታ ምክንያታዊ ሳይሆን መለኮታዊ እየመስለ መጥቷል። እጅግ ሊታሰብበትም ይገባል እላለሁ።
የኔልሰን ማንደላ “የዕርቅ እርምጃ”
አንድአንዶች፦ ይህ መንግስት የአካሄድ መስተካክል ቢያደርግ አሁንም ቅራኔን መፍታትና በጋራ መቆም ይቻላል ብለው ያምናሉ። ለእኔ እስከሚገባኝ ድረስ ግን፡ የህወሀት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ባህሪ የቲዎሪ (theory) ነፀብራቅ ሳይሆን የዘር ስሪት ነው። በሌላ አነጋገር ህወሀት የጐሳ ስብስብ እንጂ የሚታደስ ወይንም የሚቀየር የአመለካከት ቅርፅና መጠን (context) ያለው መርህ የሚያራምድ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም። ዘርና ዘረኝነትን የመቀየርና የማስቀየር ሂደት ደግሞ እንኳን ለማሌሊት ሎሌዎች ለጄኔትክስ ኢንጂነሪንግ ጠበብቶችም ቢሆን እንዲህ በቀላሉ የሚደፈር ሳይንስ አይመስለኝም። ለዚህ ነው ይህን ዘረኛ መንግስት ከማክሰም ወጪ ማከም አይቻልም የሚል ጠንካራ እምነት የያዝኩት።
እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች – ዓለም የእርቅና የመቻቻል ፖለቲካ በኩር አድርጎ በክብር የሚያወድሳቸውን ኔልሰን ማንደላን (RIP) በመጥቀስ፡ እኛም ዛሬ በእርሳቸው ጎዳና እንድንድህ ሊመከሩን ሲዳዱ ይታያሉ። የኔልሰን ማንደላ “የዕርቅ እርምጃ” የግዴታ እንጂ የውዴታ አልነበረም። ደቡብ-አፍሪካ ከነበረችበት ማህበራዊ በተለይም ኢኮኖሚያዊ ይዘት አንፃር ያንን ህብረተስብ ለጊዜው ለማሳደርም ሆነ ለማስተዳደር፡ የምርት መገልገያውን ብቻ ሳይሆን ስለተ ምርቱንም ጭምር የተቆጣጠሩት የነጮቹ አስተዋፆ የሚለምኑት እንጂ የሚገፉት አልሆነም። ለዚህም ነበር በአንድ የእራት ግብዣ ላይ ኔልሰን ማንዴላ ለታዳሚ እንግዶቻቸው “ዘወትር የነበረኝ ጭንቀትና ቅዥት አንድ ቀን ከእንቅልፌ ስነቃ ዴ-ክለርክ ሀገር ለቆ ወጥቷል የሚል ዜና እሰማለሁ እያልኩ ነበር ” ሲሉ የተናገሩት።
ምንም እንኳን ይህ ስርዓት የኢኮኖሚውን አጠቃላይ አውታር (financial, material, and knowledge base) በመቆጣጠር፡ በአዝጋሚ ማህበራዊ ለውጥ ሊያደርሰን ያሰበው ዕጣ-ፈንታ ከያኔዋ ፕሪቶሪያ የተለየ ባይሆንም፤ ዛሬ ላይ ሆነን ግን የህወሀት ኢህአዴግ መወገድ ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትል ሆኖ ለድርድርና ዕርቅ የሚያስገድድ ደረጃ ላይ አልደረስንም። ስለዚህ፦ የኔልሰን ማንደላ ጠባብ ጎዳና ሀገርን ከጥፋት ሳይሆን ወንጀለኛን ከፍርድ የሚታደግ እኩይ ሀሳብ ነው።
በሚቀጥለው ፅሁፍ የህብረታችንን ዓመታዊ ሀገራዊና አለማቀፋዊ ተምሳሌቶች (Eaglewingss 2015/16 National and International Wings Winners) ይዘን እስከምንገናኝ መልካም እንሰንብት።