ጥቅምት የወጋውን … ግንቦት ላይ ቢነቅለው
ለሊት የማሰውን … አድሮ ቢሸፍነው
ስሙ ቢቀያየር … መልክ፣ ልኩን ላንስተው
እሱው እራሱ፦ ይኼው!
ተመርዞ ላይድን … በስብሶ አናቱ
ቀኝ እጁ ከግራው … ምን ነው ልዩነቱ
ከርሞ የሚያኮራሽ … ተስፋ፣ ጤንነቱ
ኢምንት ደህንነቱ?
ጠኔ ጠፋ ችግር … ሰላም ነው የሚልሽ
ሲያባብልሽ አንጂ … አቁስሎ ሲልስሽ
የልጅ ውርጃ … ያ ዲቃላሽ
ጥምል፣ የካብ ስር ላሽ!
ክህደት ነበረ … ለእናትነት ምስሽ?
በያ ተጠየቂኝ … እስቲ እውነታ ካለሽ
አሁን ነው ወይያኔ … የሚሆን ከለላሽ
ገፎ የሚያራቁት … ሸማውን ከገላሽ
ሽፋንሽን ከላይሽ?
በዳር፣ በገጠሩ… ጥፋትን ሲያባዝት
እጁ ሲያወጣ ቅርስ … ሳንጃው ሲያወርድ ቅሪት
እግዞዞዞ! አንዳላልሽ … ጆሮሽ ቀፎት
ስብሀት ለሞት!
ግንባርሽ ባቋረው … የድካም ላብ ውሃ
ማሳ ሲያሸት ከርሞ … በሱዳን፣ ሊቢያ
ከእዛ ቅጥር … ያኔ፥ ወዲያ
የዘር ትቢያ!
ስናውቅ ማንነቱን … ሳይርቅ ትላንትና
ዛሬ ቢያዜም ደርሶ … በይሁዳ ቃና
ሊያሳየን ታምራት … ሰላም፣ ብልፅግና
የቀበሮ ባህታ፤
እንዴት ”በጄ” አልሽዉ … የአስቆርቱን ድቁና?
በያ መልሺልኝ … ይታወቅ ምክንያቱ
ከጀግና ተዋልደሽ … በዝቶ ዘር፣ ማንዘሩ
ኣንድ ልጅ የጠፋው … ሲባል “አኳኩሉ”
”ነግቷል!” ለማለቱ?
ይልቅስ እናት-ዓለም …
”፩ እና ፩” ብሎ … ሀገር በዘር ሲመነዝር
ማዶ ያሉት ቀርቦ … መሃሉ ሳይሆን ዳር
ዘራፍ! ለዘራፊ … ይሻላል ብትነቂ
“አኳኩሉ” ሲባል … “ነግቷልን” ብታወቂ፤
ቀልድ ፌዝ ካልሆነ … ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ
የልጆች ጨዋታ፤
ጨክኖ መቅበር ነው … ከፍኖ ስጋጃ
ዳግም ላይረገዝ … ተመልሶ ውርጃ።
1984 ዓ. ም.