
By Admin
ሀገራችን ብዙ ለውጥ እያየች ነው። ለለውጥ ዘመን ነውጥ፣ ለሽግግር ወቅት ፖለቲካዊ ሙቀት ግን ኢትዮጵያ ኣዲስ አይደለችም። የንጉሱ ሥርዓት በወታደራዊው መንግስት ሲተካ፣ ወታደራዊው መንግስት በዘረኛው ማህበር ሲቀየር፣ የረሃብ ማህደር ተበርብሮ – የመቃብር ጉድጓድ ተቆፍሮ ህዝብ በዶክመንትሪ movie በሌላም በሌላም ሲቀሰቀስና ሲላቀስ አንብበናል፣ ሰምተናል፣ ጥቂቱንም ደግሞም አይተናል።
ይህን ስል ግን፦ የዘንድሮው ለውጥ ከያኔው የሚለይበት ምንም መስፈርት የለም እያልኩም አይደለም። የሚንስትሮቹ ም/ቤት የናዝሬት school ት/ቤት እስኪመስል ድረስ በሴቶች ሲሞላ ዓይኔ እየተመለከት – ቅርፃዊ ለውጥ የለም! ብዬ ለመካድ አልደፍርም። ባይሆን፥ አብዛኞች እንደሚረዱት ይህ የጠቅላይ ሚንስትሩ ወንድ-ነቀል (ሴት-ተኮር) እርምጃ፦ እናትና እህቶቻችን ቀድሞ የተነፈጉትን መብት ከማስከበርም አልፎ እኩልነታቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ብቻ የተወሰደ መልካም ጅማሬ ነው ብዬ አልገድበውም። ምክንያቱም፥ ከዚያም አልፎ በፆታ ክፍልፋይ የሴቶቻችንን የቁጥር ብዛት በሚገባ ያሰላ፣ በመጪው ሀገራዊ ምርጫ የሚኖራቸውን የድምፅ ብልጫም ግምት ውስጥ ያስገባ፤ ብልሃት የተሞላ ፖለቲካዊ move እንደሆነም ስለምገምት ነው። ያም ሆነ ይኸ ግን፥ የእናትና እህቶቻችን ሹመት በአብዛኛው ያስማማናል እንጂ አያስተማማንም። ትላንት ህወሃት “አፍ የሌለውን አፈ-ጉባኤ፣ አቅም የሌለውን አቅም -ግንባታ አድርጋችሁ ትሾማላችሁ “ ተብላ ብትወቀስ፥ የደን ዕፅዋት (Forestry) ምሁሩን፦ የጫካና የዱር ልምድ በስፋት ያካበቱ “አንቱ!” – ብላ አቶ ስራጅ ፉርጌሳን የመከላከያ ሚንስትርም አድርጋ ሾማብን ነብር’ኮ ። ስለዚህ የወይዘሮ አይሻ መሓመድ ሙሳን ሹመት “ይበል!” ብለን ወደ ዛሬው ትዝብቴ እልፍ እንበል።
ትላንት፦ ኣንድ ጋዜጠኛ የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ “በከባድ ሌብነትና በሰብዓዊ መብት ረገጣ ሰለምፈልጋቸው ቤት ንብረታቸው ይታገድልኝ ሲል ለኣዲስ አበባ ክፍለ-ከተሞች ከኣራት መቶ በላይ የግለሰቦችና የንግድ ድርጅቶችን ስም ዝርዝር አስተላለፈ “ ብሎ ያነበው ጀመረ። እኔም – ጎን ለጎን ሌላ ስራዬን እየሰራሁ ማዳመጤን ቀጠልኩ። መሓል ላይ ግን በድንገት “እማሆይ” ያለ መሰለኝና ጆሮዬን ስላላመንኩት ድምፁ ወደሚመጣበት አቅጣጫ ተመለከትኩ። መልሼም፦ ምናልባትም አንባቢው ጋዜጠኛ እኔኑ እራሴን “ሰማህ ወይ? ” ሲል የጠየቀኝም መሰለኝ። ራቅ ብዬ ከተቀመጥኩበት ቦታ ተነሳሁና፥ የዜናውን የድምፅ ፋይል ትንሽ ወደኋላ መልሼ ስደግመው ግን … አዎን … “እማሆይ” ነበሩ ክራራይሶን ትተው በኪራይ ሰብሳቢነት የተከሰሱት።
ምናልባት አሁን “ታዲያ ይሄ ምን ያስገርማል? ከአቡኑ ብብት የወጣ ማካሮቭም (Makarov) ተሳልመን ስመናል ” ትሉኝ ይሆናል። ለእኔ ግን ከማስገረምም አልፎ አሳስቦኛል። ምክንያቱም፦ ከእማሆይ በላይ ለአምላክ የቀረበ፣ ሀሳብና ፍላጎቱን የሚረዳ ማን ሊኖር ይችላል? እኛ በላይኛው መንግስት የሓብታምና የደሃ ሰፈር የለም፤ ሁሉም በኩል ያድራል ብለን ስንዘናጋ፥ እማሆይ ምን ምስጢር ተገልጦላቸው እንደሆነ ማን ያውቃል ቤት ንብረት የሚያከማቹት – የሚያሸሹት? ጎበዝ! ማሰቡ ይበጃል፤ ለክፉም ለደጉ ለላይኛውም ቤት ቅሪት መቋጠሩ ይጠቅማል።
የተጠርጣሪ ግለሰቦቹን ስም ዝርዝር ለ-አዳመጠው ወይንም ደግሞ ለ-አነበበው “… (ልጅ)፣ … (ልጅ) ፣ … (ልጅ) ” እያለ ከመስመር መስመር ሲሸጋገር – ሜቴክ መንደር እናቶች ልጆቻቸውን ወተት ሳይሆን ወርቅና ብር ማጥባት ጀመሩ ወይ? ያስብላል። በዚህ ብልሹነት ተነካክተው “… ወይዘሮ እንትና (ሚስት)፣ ወይዘሮ እከሊት (ሚስት)፣ ወይዘሮ … (የሚስት እናት)፣ አቶ … (የሚስት አባት)፣ … (የሚስት እህት) … ” ወዘተ እያለ ከዚህኛው የገፅ ጠርዝ ወደዚያኛው ገፅ ጠርዝ ሳይበጠስ የሚንጠለጠለው የትውልድ ሓረግ፥ ህወሃት- ወለዱ ዘረፋ ከሃገራዊው ግብረ-ገብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሀይማኖታዊው አስተምሮትም ጋር ምንኛ የተራራቀ አሳፋሪ ተግባር እንደነበር በግልፅ ያስረዳል።
የባሏ የናባልን አንገት ለመቁረጥ ከአፎቱ ከወጣው የንጉስ ዳዊት ሰይፍ በብልሃት የታደገችውን አቢጋልን አስታውሶ፥ መጽሐፉ “ሚስት ለባሏ ዘውድ ናት” ብሎ እንዳላስተማረ፥ ይኸው ዛሬ – “ሰርቀህ ካልመጣህ እንደወጣህ ቅር “ ብላ የምትራገም፣ የንጉስን ቁጣ ልታበርድ አይደለም የቀትርን ንዳድ እንኳ የማታስጥል፣ ዘውዱ ቀርቶ የሰሌን ኮፍያም መሆን የማትችል የትዳር አጋር ላይ ደረስን ማለት ነው? ይብላኝ ለኣዲስ ኪዳኑ ወንደላጤ እንጂ እኛስ በብሉይም በሉት በብሉቱዝ (bluetooth) … ብቻ በደና ዘመን አግብተን – ወልደን ከብደናል።
ለማጠቃለል ግን ኣንድ ነገር ልበል። እስርና የንብረት- እገዳ ለዘራፊና ገዳይ የፍርድ -መቅድም እንጂ የፍትህ- መደምደሚያ መሆን አይኖርበትም። ይኽ እርምጃ፦ የለውጥ ወቅት ሙቀት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር። የዛሬ የለውጥ ብርሃን የትላንትን የመርገምት ጨለማ የሚገልጥ ብቻ ሳይሆን፥ ተገቢና ተመጣጣኝ ፍርድንም በመስጠት የነገን ስጋት የሚገፍ ጮራ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። ያ መሆን ካልቻለ ግን ዛሬም ከትናንት፣ ነገም ከዛሬ አዙሪት ፈፅሞ ልንወጣ አንችልም። የሰውን አንገት እንደ ገብስ እሸት፣ ክቡሩን ገላ እንደ ማሳ ማሽላ በሜንጫ ለመቁረጥና ለማስቆረጥ ከመዛትም አልፈው በተግባር ያዘመቱብን፥ በማደግ ላይ ያሉ ትናንሽ ጅቦች ዛሬም እንደ አደቡ የቡራዩ ከተማ የቅርብ ጊዜ ምስክር ናት።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፥ ክርስቶስ እንኳ ፀዳ ባለ ፍቅርና ስብከት ሊያቆማት ያልቻለውን utopia፥ እሳቸው በምክርና ልመና እመሰርታለሁ ብለው ከታተሩ ትልቅ ስህተት፥ መጨረሻችንም ከባድ ዕለቂት ነው። የሀገርና የህዝብ ደህንነትን ከስርዓት አልበኞች መታደግ የሚቻለው በህግና በፍርድ አልያም በሀይልና ስልጣን እንጂ በልመናና ተማፅኖ እንዳልሆነ ተረድተው እያለቀ እና እየተፈናቀለ ላለው የዳርና የደቡብ ህዝባችን በቶሎ ሊደርሱለት ይገባል። መለኮትን የሚቀበል መለኮትን ከሚሰጠው እጅግ ያነሰ አይደለምን? ክርስቶስን የሰቀለ ዓለም እና ሰይጣን ክርስቶስን ለሚሰብክ ክርስቲያን ሊገዛ እንዴት ይቻለዋል? እምነትን የሰቀለ ይሁዳ ለአማኙስ እንዴት ይታመናል?