
By Admin
ዛሬ ውስጤን የሚያናውጠው ማዕበል፡ ከጥቂት ግለሰቦች በስተቀር የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ አእምሮ እንደ ትንሽ ታንኳ እያናጋ፡ አንዴ ከራሱ ምናብ የሃሳብ ቋጥኝ ጋር፡ አንዴም ከአምላክ ምስጢራዊ ፈቃድ ዓለት ጋር እያጋጨው እንዳለ ይገባኛል። ታዲያ፥ ስሜት በቀላሉ ሰብረው በማያመልጡት የምሬት ሠራዊት ሲከበብ፣ ተስፋ በድቅድቅ የሞት ጭጋግ ውስጥ ሲደበቅ፣ ለነፍስና – ለስጋ፡ ለአእምሮና – ለእጅ፡ እንደ መፃፍ ያለ ከባድ ህመም የለም። ልብ ብርቱ በሆነ የሀዘን ጦር ሲቆፈር፡ ጉልበትን ሰብስቦ ሃሳብን አምጦ መውለድ አይደለም፡ እውነታንም ቁጭ ብሎ መታዘብ ይከብዳል። ያኔ፥ እፅፋለሁ ላለ ጣት፡ ብዕር እንደ ብረት ለሽክም ይከብዳል። ቢሆንም ግን፡ የቆሰለው አእምሮዪ በተደጋጋሚ አንድ ጥያቄ ይጠይቀኛልና፡ በዝምታ ከማስታምመው – ይኸው ተንፍሼ ልገላገለው ሞከርኩ።
የማከብርህ ኢትዮጵያዊ ወገኔ፥ ተፈጥሮ ሳትሰስት፡ ከዓለም ሁሉ አብልጣና አድልታ የሰጠችንን የዘፍጥረት እና የስልጣኔ ብኩርና፡ እንደ ኤሳው ለሆዳችን – ለምስር ወጥ – ሸጠን፡ እስከመቼ ነው እንደ ዝቃጭ እንደ አተላ፡ ህይወታችን ክብር፣ ሞታችን ዝክር የሚያጣው? እስከመቼ ነው ዘረኞች የዘሩልንን አዝመራ ስናጭድ – ስንውቃ ውለን፡ ሲመሽ ምርት ሳይሆን ምሬት ሰብስበን ወደ ቤታችን የምንገባው? እስከመቼ ነው ሰሜን ጫፍ ተቀምጠው፡ ከደቡብ ጫፍ የተወረወረ ጠጠር ሊስታቸው እስከሚሳነው ድረስ እየሰፉ እና እየሰቡ ያሉት የፖለቲካ መሪዎቻችን፡ ከአፍንጫችን በላይ ያንጠለጠሉልንን የነፃነት ካሮት ላንደርስበት-ላንበላው አህያ ሆነን ስንጋልብ እና ስን’ጋለብ ዘመን የሚያልፈው? እስከመቼስ ነው ምስኪኑ ወገናችን ደረቱ ላይ ተደግኖ የተተኮሰበት የመሳሪያ ጥይት እስኪስተው ድረስ በየሰከንዱ-በየደቂቃው በረሃብ እየከሳ እና እያነሰ፡ በየበራሃው በኖ ተኖ፣ በየባህሩ ዝሎ ሰጥሞ የሚያልቀው?
በወንድሞችህ የግፍ ሞት ልብህ የተሰበረው ኢትዮጵያዊ ወገኔ፥ የነፃነት ትግል እኮ ዓላማ እንጂ ባህል አይደለም። ተጀምሮ ማለቅ፤ መነሻ አምድ፣ መደምደሚያ ግብ ሊኖረው ይገባል። የባርነት ሰንሰለት አልበጠስ ብሎ ከከረረ፡ አልቋጭ ብሎ ከረዘመ፡ እንደ ወግ-ባህል ከዘመን ዘመን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ከተሻገረ፡ ቆም ብሎ ማስተዋል፤ መሪ ተመሪን መቃኘት ግድ ይላል።
ዛሬ በኣራቱም የዓለም ማዕዘናት ህዝባችን እየቆጠረ ላለው ፍዳና ሰቆቃ መነሻ ምክንያቱ ፖቲካዊ እንጂ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አንዳልሆነ ለመረዳት፡ ማንም የርዕዮተ ዓለም ፈላስፋ አሊያም የምጣኔ ሃብት ሊቅ መሆን አይጠበቅበትም። ፖለቲካዊ ችግር ደግሞ ከምንም በላይ ፖለቲካዊ መፍትሔን ይሻልና፡ ፖለቲካችን እንዴት እና ወዴት ነው? ዜጎቻችን ትላንት– ሳውድ ዓረቢያ፡ ዛሬ– የመን፣ ደቡብ ኣፍሪካና ሊቢያ ላይ እየተጋቱ ያሉትን መከራ ከምንጩ ለማድረቅ፣ ነገም ተመሳሳይ ጥፋት ካይሮ ላይ ከመከሰቱ በፊት ችግሩን ከችካሉ ለመንቀል ልምን ተሳነን? ጉድለታችን የመሪ? የተመሪ? ወይንስ አጠቃላይ የድርጀታዊ መዋቅር እንከን ነው የሚለውን መጠየቅ እና በአፋጣኝ መመለስ ወቅቱ ይመስለኛል። እርግጥ ነው ዛሬም ቢሆን፡ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጀቶች ከብሉይ ኪዳን የመማፀኛ ግንብ በተለየ መልኩ መዋቀርና ተቀዳሚ ዓላማቸው ተገዳዩን ማትረፍ እንጂ ገዳዩን ማቀፍ መሆን የለበትም ብዪ አምናለሁ። ዘራፊው ዘርፎ፣ ገዳዩም ገድሎ እጁ ሲዝል እና ሲደከም፡ ሀጢያቱን ለማስተሰረይ፣ ከህዝብ ለመታረቅ ዘሎ የሚቀላቀለው እና የሚያንቀላፋበት ጎራ – እንደ እኔ ግለሰባዊ እምነት- ወህኒ-ቤት እንጂ አንድነት፣ መድረክ፣ ሸንጎ ወይንም ግንቦት ሰባት መሆን ያለበት አይመስለኝም።
ላለፉት በርካታ አመታት እንደታዘብነው ግን፦ ሀገር እንደ ቡሄ ሙልሙል ገምሶ፣ ህዝብ እንደ አክርማ ቀጭቶ፣ ዘርፎ እና አዘርፎ የበቃው ባለስልጣን መሽሽጊያው አንድም ቤተ-መቅደስ ኣለበለዚያም የተቃዋሚው ድርጅት ነው። ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፡ ወንጀለኞች ሰይጣናዊ ባህሪያቸውን በሃይማኖታዊ ጠበል አርጥበው፣ በተቃዋሚ ፎጣ አድርቀው በአዲስ ካባ ብቅ ሲሉ እንደ ቅዱስ መላዕክት የሚሰገድላቸው የአይሁዳውያኑ የመማፀኛ ቅጥር መሆናቸው እስካላበቃ ድረስ፡ የነፃነት ኣላማችን ዕውን የሚሆነው፣ የመከራችን ቋጠሮ በዘላቂነት የሚፈታው – በዕድል እንጂ በትግል እንዳልሆነ መጠርጠር የለብንም።
ከረሃብ ወደ ስድብና ውርደት ተመሳሌነት ያሻገሩህ ኢትዮጵያዊ ወገኔ፥ ጽሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት ዛሬም እንደ ትላንቱ የማሰምርበት እውነት ቢኖር፦ ህዝባችን ከእንሰሳ ባነሰ ክብር በየመንገዱ ተቀጥቅጦ ሲገደል ዝም ብሎ ከማየት የከፋ የወገን በደል የለምና፡ እንደ ዜጋ የሚጠበቅብንን ሁሉ በማድረግ የተረፉትን ለመታደግ፣ የረገፉትንም ቤተሰቦች ለማፅናናት ዛሬ! አሁን! ቃል ብቻ ሳይሆን ከትግሉም መሃል መግባት ይኖርብናል።
መፈራረሳችን፣ ስድባችን፣ መዋረድና መታረዳችን ዓላማቸው ብቻ ሳይሆን አለማቸውም ለሆነው ጎጠኞች፡ የሃዘን ሲቃችን ብሔራዊም ባይሆን ጎሳዊ መዝሙራቸው ነው። የድረሱልን ለቅሶና ጩኸታችን፡ “አከርካሪውን ሰበርነው – ጥርሱን አወለቅነው“ ብለው ለተሳለቁብን ዘረኞች፡ የዓላማቸውን መሳካት የሚያበስር ደወል፣ የግባቸውን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ ቃጭል ከመሆን ባሻገር ፋይዳ እንደሌለው ተረድተን፤ ራሰን፣ ወገንን እና ሃገርን የማዳን ዘመቻውን ከራሳችን በራሳችን መጀመር ብልህነት ነው። የዓባይን ውሃ ለኣባዮቹ ትተን፡ የወገናችንን፣ የአዛውንት እናትና አባቶቻችንን የኣይን ፍሳሽ- ዕንባ – ለመገደብ፡ የትግል ቦንድ (ውህደት) መፍጠሩ ከመቼውም በላይ አስፈላጊ የሆነበት ወቅት ላይ ደርሰናልና ወንድ – ሴት፣ እስላም – ክርስቲያን ሳንል በተግባር በስነ-ምግባር እንተባበር።
ኤግል-ዊንግስ-ሶሳይቲ በደቡብ ኣፍሪካ፣ በየመን፡ አንዲሁም በሊቢያ ህይወታቸው ለጠፋው ዜጎቻችን የተሰማንን ከፈተኛ ሃዘን ስንገልፅ፡ ለቤተሰቦቻቸውም አምላካዊ መፅናናትን እየተመኘን ነው። ችግሩ ከመሠረቱ አልተወገደምና፤ በኣሁኑ ወቅትም በአደጋ ወስጥ ላሉት ወንድሞችና እህቶቻችን፡ ከበረከታችን ሳንሰስት በጉልበት፣ በዕውቀትና በገንዘብ የምንችለውን ሁሉ ከማደረግ ባሻገር ትግሉ ለመከራው ዘለቄታዊ መፍትሔ እስኪያመጣ ድረስ፡ የአምላክ ሰፊ መዳፍ የመጠለያ ድንኳን እንዲሆናቸሁ ምኞትና ፀሎታችን ነው።