Post

“እናቶች ለዘላለም ይኑሩ!” … ጠቅላይ ሚንስትሩ

“እናቶች ለዘላለም ይኑሩ!” … ጠቅላይ ሚንስትሩ

By Admin

ከተኮሱብን እንተኩሳለን!ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው ይላል መፅሐፉ እኔ ደግሞ በግሌ የፖለቲካ ሁሉ መቅደም ማህበረሰብን ማክበር ነው እላለሁ። ለዜጋ ብሎም ለህብረተሰብ ክብር የሌለው የዜግነት ፓለቲከኛ፥ ቧልተኛ እንጂ ሌላ ምን ይባላል?

ጊዜው፦ ህወኃት በአፍጢሟ ልትደፋ እየተንገዳገደች የነበረችበት ወቅት ነበር … 2016። የአርበኞች ግንቦትሰባት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለህዝባዊ ስብሰባ ጀርመን ገብተው ወደ አዳራሹ እያመሩ ነው። የብሉይ ኪዳኑን ጎልያድ የሚዛመዱ በሚመስሉ ግዙፍ ጠባቂዎች ታጅበውከተሸከሙት የእጅ ቦርሳ ክብደት የተነሳ የግራ ትከሻቸው ሰምጦ ስመለከት፥ የአዘቦቱ ቀን ፋሲካ መስሎ ተሰማኝ። በተለይ ደግሞ ከመንገድ ዳር ቆመው ለሚቃወሙዋቸው የህወኃት ደጋፊዎች ኣውራ-ጣታቸውን እንደ ፈረንጅ ቄሮ (teenager) ዘቅዝቀው በኩራት ሲራምዱ … በቃ ፈጅተዋቸው ነው !አልኩ በውስጤ። ያ ከባድ የእጅ ቦርሣም ከተማርኩና ከቆሰሉ የህወኃት ወታደሮች ስም ዝርዝር ውጪ ሌላ ምንም ነገር ሊሆን አይችልም ብዬ ስላሰብኩ ቁጥራቸውን መገመት ጀመርኩ። ሃያ ሺህ … no no no … እንኳን አርበኛውሻቢያም በባድሜ ጦርነት ገድልኩ ያለችው የትየለሌ ነው … መብለጥ አለበት ብዬ ደምድሜ 60 ሺህ አደረስኩት።

ከመቼው ተቀመጥው ከመቼው ስም ዝርዝሩ ተነቦ እያልኩ ስቁነጠነጥ አርበኛው ገና ከአዳራሹ ሲገቡ ከእኔ ይበልጥ በደንብ የሚያውቃቸው ደጋፊ ፉጨቱን አቅልጦት ወዲህና ወዲያ እየዘለለ በዘፈን እንቅጩን ነገረኝ … መች ተዋጋና … አስቧል ገና !እያለ። በከሸፈው ግምቴ የተሰበረው ቅስሜ ውሎ አድሮ ቢጠግንም የእጅ ቦርሳው ክብደት ሚስጢር ግን አሁንም አልተገለጠልኝም። ምናልባት ደጋፊዎች ለሚከፍሉት መዋጮ የሚቆረጥ ደረሰኝ ይሆን? ይህን የደረሰው ብቻ ነው የሚያውቀው።

ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ፦ ዘወትር ለውጪያዊ አካል ግፊት የሚሰነዘር የመልስ ምት (reaction) ብቻ ሳይሆን፥ ከራስ ዓላማ ተነስቶ ወደ ራስ ግብ ወደብ የሚደረግ ጉዞም (action) ጭምር ነው። ፖለቲካ፦ እንዲህ ከተደረገ እንደዚያ አደርጋለሁ፣ ይህ ከተባለ ያን እላለሁ በሚል የድጊት ቃልኪዳን ብቻ ተወስኖ የታጠረ ሆኖ አይሰማኝም። የያኔው አርበኞች ግንቦትሰባት፥ የዘንድሮው ኢዜማ ሳይዋጋ ቤተመንግስት ገባ ብዬ ብርድም – ሙቀትም አይሰማኝም። ነገር ግን ከለውጡም በሉት ከተሃድሶው ማግስት ጀምሮ ህዝባችን ለሚደርስበት እስራት፣ ውክቢያ፣ ዕገታና ግድያ የአህያ ጆሮ ይስጠኝ ብሎ መቀመጡ ብቻ ሳይሆን፥ ከተኮሱብን እንተኩሳለን !ከመረጡን እንመረጣለን! አይነት ብልጣብልጥነት ከመተዛዘብ አልፎ ቀንና ቦታ ሲፈቅድ ምናምን እንዳያማዝዘን እሰጋለሁ።

ነው ወይንስ ቀድሞ በስድስት ወራት ውስጥ ኣዲስ አበባ ለመግባት ኣምስት ኣምስት መቶ ዶላር እንደተዋጣው አሁንም ከቤተመንግስት ለማውጣት ኣምስት ኣምስት መቶ ዶላር ይከፈል? “መሰንበት ደግ ነው ይላል የሀገር ሰው። ማን ያውቃል ዶላር ከፍሎ ስይሆን በዱላ ኣምስት ኣምስት ቦታ ከፋፍሎ የሚያስወጣ ይመጣ ይሆናል።

እናቶች ለዘላለም ይኑሩ!” ጠቅላይ ሚንስትሩ

እንደ እኔ ያለ ምስኪን ወንድ፦ የፍቅር ጓደኛው አልለመን ብላ ጥላው ስትኮበልል ለጊዜውም ቢሆን የሚፅናናው ላድ በድባብ ትሒድ ብሎ ነው። ሴቶች ሁሉ አንድ ናቸው የሚል እምነት ባይኖረኝም፥ የብሒሉ ትርጓሜ ግን ሴት ብትሔድ ሌላ ሴት ትመጣለች ለማለት ይመስለኛል። የብልፅግናው መሪ እናቶች ለዘላለም ይኑሩ !ብለው ሲፎክሩ? ሴቶች ቢታገቱም እናቶች ነገ ሌላ ሴት ልጆች ይወልዳሉ ማለታቸው ይሆን? አጃኢብ ነው! ይላል ሐረሬው … .

አቆራራጩ ጠቅላይ ሚንስትር እንደ ቀድሞው ቆራጡ መሪ ኣንድ ሰው እስኪቀር ድረስ እዋጋለሁ !ብለው ሲሸልሉ ባልሰማም ኣንድ ሰው እስኪቀር ድረስ ምህዳሩን አስፋለሁ !ብለው የተነሱ ግን ይመስለኛል። እንዳውም ሁለት ላድርገው መሰለኝ እሳቸውና ቀንደኛ ደጋፊያቸው አቶ ጌታቸው አሰፋ ብቻ እስኪቀሩ። ከኣፈ-ቀላጤያቸው ከአቶ ነጋሶ ጥላሁንም በላይ ጥላከኢዜማም በላይ ሚዜ ሆኖ ጠቅላይ ሚንስትሩን እያገለገለ ያለ እንደ ቀድሞው የደህንነት ሹም ማን አለ? ከከብት ጋር ሜዳ ውለው ሜዳ የሚያድሩ ምስኪን እረኞች በግፈኞች ሜዳ ላይ እስከወዲያኛው ሲያሸልቡ አቶ ጌታቸው አሰፋ ይወነጀላሉ እሳቸው ነፃ ይወጣሉለአቅመሔዋን ያልደረሱ ልጃገረዶች በደምቢ ዶሎ ጫካ ለወራት ሲረሱ የቀድሞው ደህንነት ሹም ይረገማሉ የአሁኑ ጠቅላይ ሚንስትር እፎይ ብለው ደቡብኣፍሪካ የኔልሰን ማንዴላን የግዞት ደሴት Robben Island’ ይጐበኛሉታዲያ ከአቶ ጌታቸው አሰፋ በላይ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ማን ድጋፍ ሆናቸው? በነገራችን ላይ፦ የጠቅላይ ሚንስትሩ የደቡብኣፍሪካ ጉብኝት ለሁላቸንም ግልፅ ቢሆንም፥ የRobben Island ጉዞ ግን የእኔ ግምት መሆኑን እንዳትረሱ።

እውነትን ለሚገነዘብ አእምሮቤት ክብር ቤተሰብ መሆኑ አይጠፋውም። የሀገርም ኩራት ህዝብ ነው። አባት፣ እናት፣ ልጅ በየተራ እየረገፉ የጠቅላይ ሚንስትሩ ኢትዮጵያ አትፈርስም ተረት 100 ሚልዩን ህዝብ ማሻገር ቀርቶ ኣንድ ህፃን አባብሎ አያስተኛም። እኔን ጨምሮ የአብዛኛው ህዝብ እሮሮ በጠቅላይ ሚንስትሩ መጠን ያለፈ ቸልተኝነት በገፍ እየረገፉ ያሉትን ንፁሐን በመመልከት እንጂ ተገቢውን እርምጃ ወስደው በስኬት አልባነታቸው አይደለም። በብሔርተኞች ገጀራና በትር ኦና የሆነች ምድርን ለማን ልናወርስ ምንስ ለማትረፍ እንዳላየ ታውረን፣ እንዳልሰማ ደንቁረን እንለፍ? ለሞሶሎኒ  በስሙኒ ልንሸጣት?

የካደኝ ብአዴን ነው ህወኃት

የክፋት እምብርት ናት የምላት ህወኃት፦ ኢህአዴግን ያፈረሰው የካደኝ ብአዴን ነው ስትል ብሰማት፥ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋህ ሆና ታየችኝ። ለወጣበት ማህበረሰብ ያልታመነ ኣሳማ፥ ተሸውዳ ስታረባ መክረሟ በእርግጥ ያስገርማል። ብአዴን / ኣዴፓ ብኩርናውን በምስር ወጥ የለወጠ ኤሳው፣ ወንድሙን ያረደ ቃየል መሆኑን ለመመስከር መሲህ ከሰማይ መውረድ የለበትም። ከምስረታው እስከ ዛሬ ብልፅግናው ያለው ታሪኩን መመልከት ብቻ በቂ ነው።

እንደ እኔ እምነት፦ ለኣንድ መሪ የህዝብ መከራ በበዛበት ዘመን ስልጣን መጨበጥ ፈታኝ መሆኑ እርግጥ ቢሆንም፥ ከዚያ የበለጠ ትልቅ የታሪክ ስጦታም ፈፅሞ ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም፦ ታላቅ ስምን በኣንድ ግዑዝ የድንጋይ ስባሪ ላይ ሳይሆን በሚልዮኖች በሚቆጠሩ ህያዋን ልቦች ላይ ለዘላለም አትሞ ለማንቀላፋት መልካም አጋጣሚ ነውና። ኣዴፓ ግን ከዚህ ፈፅሞ የተለየ ነው። ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ፦ ለባርነቱ ሽፋን የሚሰጠን ምክንያት ለውጡ እንዳይቀለበስ የሚል ነው። ሲጀመር ለውጥ ካለ በቤተመንግስቱ ግብር ማብያ ደጃፍ ለተኮለኮሉት እንጂ በገጠር፣ በከተማው ለተበተነው ሰፊ የኣማራ ህዝብ የተለወጠው ምንድነው? ከጥይት ሞት ወደ ገጀራና ሜንጫ ዕልቂት?

አፈጣጠሩ እንጂ አኗኗሩ ከኣሳማ ያልተለየው ኣዴፓ ለውጡ እንዳይቀለበስ ብሎ ሲያለቅስ፥ ገፊ ምክንያቱ የህዝብ ነፃነት ሳይሆን ግለስባዊ ስግብግብነት ነው። የኣዴፓ ለውጥቢቀለበስ፥ ህወኃት ከሃዲ አሽከሯን ጥፍሩን ሳይሆን ጥርሱን ነቅላ በድዱ እንደምታሳኝከው ጠንቅቆ ያውቃል። ያ ቢሆን ደግሞ ከእውነተኛ የኣማራ ልጆች በላይ ደስተኛ የሚሆነው ማነው? በግሌ ግን፦ ምላሱንም ጭምር ከላንቃው በጥሳ፥ የሆዱንም ተድላ ጣዕም ብታሳጣው እመርጣለሁ። በወገኑ ደም የደመቀ፣ በዘሩ እንባ እንደ ክትፎ ጣባ የወዛ ከርሳም ቀርቶ፥ ለሀገር ክብር ሳር መስሎ የገረጣ አርበኛም አንገቱ በግፍ በገመድ ተቋጥሯል።

ኣዴፓ፦ ወክየዋለሁ ለሚለው የኣማራ ህዝብ ተቆርቋሪ ቢሆንማ ኑሮ፥ የክልሉ ዋና ከተማ ባህርዳር መሆኗን ዘንግቶ፥ ነፍሳቸውን ለማትረፍ ከኦሮምያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የተሰደዱ የደሴ ወልድያ ተማሪዎች ለአቤቱታ ለምን ባህርዳር ድረስ መጡ ?ብሎ አይከስም ነበር። አልፎም በኣንድ እናት ልጆች መካከል መለያየትን ለመፍጠር የባህርዳር ወጣት ቤተክርስቲያን በተጠለሉ የወሎ ተማሪዎች ላይ ዱላ መዘዘ ብሎ በአደባባይ በኩራት አያጓራም። ለህዝብ መብት መቆም፣ ክልልን መወከል በተግባርና ምግባር እንጂ በመድረክ ጩኽት አይገለፅም። ለመጮህ ለመጮህማ ላምም ሳር ግጣ ስትጠግብ መስክ ላይ እም – !ትላለች።

የብርቱካን ጭማቂ

በግሌ፦ ምርጫችን እንደ ሠርጋችን መልስም ያለው መስሎ ይታየኛል። አሸናፊውም ሆነ ተሸናፊው ለሌላ ሁለተኛ ዙር መጋበዙ አይቀሬ ነው። እድሜ ለሰጠው ፖለቲከኛ፦ ሀገር ለማዳን ከምርጫው በፊት ይቅደም ሲባል የነበረውን የሽግግር መንግስት ከምርጫው ቦኃላ በአካል ለመታደም፥ አልያም በሴራ ፖለቲካ ተጠልፎ ከብረት አጥር ጀርባ ሆኖ በቴሌቪዥን መስኮት ለመታዘብ ዕድል ይኖረዋል። ካልሆነም ላልተወሰነ ወራት ሀገር በመሳሪያ ታኮይቆማል ወይ እስከወዲያኛው በመሳሪያ ተቦርቡሮ ይወድቃል። በዚህም ተሄደ በዚያ ግን፦ ከሰፊው ምህዳራቸው ገበታ ማኝክ ከሚችሉት በላይ ለጐረሱት ጠቅላይ ሚንስትር፥ ሊጠጡት የተዘጋጁት የብርቱካን ጭማቂ እንደ ትንታ ነው።

ከድምፅ ቆጠራው ማግስት ጀምሮ ምርጫ ቦርድ ከሜንጫ ቦርድ የሚያደርጉት ፍልሚያ ቀልብ መሳጭ ባይሆንም ደም መጣጭ እንደሚሆን ግልፅ ነው። አቶ ጃዋር መሐመድ በምርጫ ባይሳካ በሜንጫ ልክ አስገባችኃለሁ ያሉንን እንዳትረሱ። በነገራችን ላይ፦ ዶ/ር መራራ ጉዲና ማንኛውም ዜጋ መጥፎ ስነምግባር ከሌለው የድርጅታችን አባል መሆን ይችላል ሲሉ ብሰማ፥ ሰውየውን ለቤተመንግስት ስልጣን ሳይሆን ለመንግስተሰማይ ዳኝነት እንደተመኘኋቸው መግለፅ እወዳለሁ። ምን ያድርጋል ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀራል እንጂ፤ ለሰው ልጅ አንገት ሜንጫ የመመኘት አረመኔያዊ ምግባር በመልካም ስነምግባር ከታለፈ … adios ኩነኔ! በፍርድ ቀን፦ እኔም ሉሲፈርም እጃችንን ኪሳችን ውስጥ ከትተን እያፏጨን ገነት ነበርን!

ወደ ምርጫችን ስመለስ ትላንትና ኣንድ ግለሰብ በመፍታት ህዝብ ! ያለላት ግልሰብ ነገ ሀገር ፈታ ህዝብ ! እንደሚል የሚጠራጠር ካለ የዲዳ ጓደኛውን ብቻ ሳይሆን የራሱንም እውነታ ሳይገነዘብ “I see እንዳለው ዓይነስውር መሆን ነው። ፈረንጅ ሲተርት “I see, said the BLIND man, to the DEAF ይላል።

ጉልበትና ብልሀታቸው ውስን ሆኖ ሳለ ከሚገባው በላይ እጅግ በመታበይ ሀገር ለማፍረስ አፋፍ የደረሱት ጠቅላይ ሚንስትር፥ ከወይዘሮ ብርቱካን ሚድቅሳ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የሚኖራቸው ስልት ሁለት ነው። ኣንድ፦ በባህላዊው (በተለምዶዋዊው) የምርጫ ህክምና ትንታቸውን አስታግሰው በነጠላም ይሁን በቡድን መንግስት በመመስረት ህግን በሀይል ማስከበር፤ አልያም፦ ሀገርን ብቻ ሳይሆን ክልልንም ጭምር “ብልፅግና ” በሚባል ብል አስበልቶ እስከወዲያኛው በመንደር መፈርፈር።

እርግጥ ነው ትንታቸውን በባህላዊው የምርጫ ህክምና (ድምፅ ሰረቃ) ለማስታገስ መሞከር ከቅርቡ የሰላም ኖብል ተሽላሚነታቸው ጋር አይዋሃድም፥ እንደ ሀገር እንቀጥላለን ከተባለ ግን ዘመናዊው የምርጫ ህክምና ለትንታቸው ፈውስ ሊሆን ከቶ አይችልም። ምክንያቱም፦ አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ መራጭ ተመራጩን የሚመዝንበት ዓይን በአደገኛ የዘርና የሐይማኖት ልዩነት ጨረር ከመንሸዋረሩም በላይ፥ በድቅድቅ የጥላቻ ጨለማ ታውሯል። አይዲዮሎጂ፣ ዴሞክራሲና ዲስፒሊን እንደያኔው ኣማራና ክርስቲያን እጅና እግራቸው ታስሮ አርሲ አርባጉጉ ገደል ተወርውረዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደሚሰብኩን አሁን እየተጓዝንበት ያለነው ጎዳና መዳረሻ ብልፅግና ሳይሆን ብቀላ ነው።

የኢንጅነር ታከለ ኡማ – አበባ

በኣንድ ወቅት የከተማችን ምክትል መስተዳድር ጀባያሉንን “metaphor በእርሳቸው አቀራረብ አዋዝቼ ልውጠው ባኝከው ባኝከው አልደቅልህ ብሎኝ ይኸው እስከዛሬ እንደታገልን አለን። ኢንጅነሩ እንዲህ ነበር ያሉት

ከአንድ ሰው ጋር ያወራነውን share ላድርጋችሁ … ቤት ውስጥ የበቀለ ችግኝ እንዲደርቅ እንዲለመልም ማድረጉም የባለቤቱ ጉዳይ ነው። ምን ማለት ነው በሌላ መልኩ … ቤት ውስጥ ያለው ችግኝ ፀሐይ እንዲያገኝ ትንሽ መስኮት መክፈት አለበት … መጋረጃዎቹንም … ውሃ ደግሞ ማጠጣት አለበት እንዲደርቅ ከተፈለገ ደግሞ መዝጋትበሩን ዘግተህ ፣ መጋረጃውን ዘግተህ ፣ ውሃ እንዳይጠጣ አድርገህ መከልከል ነው በቃ simple ነው ። …  
 

አሁን ትዝ አለህ አያሌው ሞኙ ሰው አማኙ?

የመዲናዋ መከራ ገና ነው። ከንቲባውም ሆኑ አባሜንጫ ህልማቸው ሸገርን በጉድፈቻ መከለል አልያም ውሃና አየር ከልክሎ አፍኖ መግደል ነው። እዚህ ላይ፦ የኢንጅነሩን ቃል በእኔ የግንዛቤ ፍቺ ብቻ አሳጥሮ ከማጠርና አልፎም conspiratorial ከሚመስል የትርጉም ማዛባት ለመዳን፥ የንግግራቸውን ሙሉ ይዘት የሚገልፅ የምስል አድራሻ (link) ማስቀመጥ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። ምናልባትም እሳቸው በተጠቀሙበት የአገላለፅ መንፈስ ምሳሌያቸውን አድቅቆ ለመዋጥ የሚያስችል ጠንካራ መንጋጋ፣ የዋህ አንጀት ያለው አንባቢ ካለም ላለማሳሳት ይህን ማድረጉ ጠቃሚ ይሆናል። ማንንም፦ የከንቲባውን ሳይሆን የዚህን ፅሑፍ ትርጓሜ ዋጥ ብዬ ለማስገደድ እንደማልሞክር ሁሉ፥ ማንም ደግሞ የእኔን ጥርጣሬ በእሳቸው metaphor ሊያስለውጠኝ እንደማይችል ግልፅ ሊሆን ይገባል። ግን ከንቲባው የጠቀሷቸው እኚያ ኣንድ ሰው ማን ናቸው? ምንጭ ቪዲዮ ደቂቃ 4:55  

ሸገርም ይሁን ሐረር፣ ናዝሬትም ይሁን ጨርጨር የትም መንደር የከተምክ የዋህ፦ መከራህ እንደ ደራሽ ጎርፍ ድንገት ሳይደፍቅህ ለራስህ እወቅ። ኢትዮጵያን ከሌላው የእጁ ሥራ ለይቶ ለፈጣሪ የቀረበ ልዩ ስሪት በማድረግ አምላክ ይታደገናል አይነት ስብከት ከፈሪሳውያን ያልተለየ ግብዝነት ነው። ከእርድና ከግፍ ግድያ የሚያተርፍህ በእጅህ የምትጨብጠው ሰይፍ እንጂ በጓዳህ ግድግዳ የሰቀለከው ሰይፍ የታጠቀ ምስል እንዳይመስልህ። ትዕዛዛቱ ኣስር ናቸው! ራስህን ከአረመኔያዊ የሜንጫ እርድ አትከላከል የሚል ኣስራአንደኛ ፅህፈት በፅላቱ ላይ የለም።

ደግሜ እነግርሃለሁ፦ ደካማውን በፍቅር፣ ሀያል ነኝ ባዩን ደግሞ በሀይል ማቆም አለማዊ ብቻ ሳይሆን መለኮታዊም ተግባር ነው። አምላክ እንደ ልቤ የሚሆንልኝ የእሰይን ልጅ አገኘሁ ሲል የተናገረውስ ስለማን ነው? የንጉስ ዳዊት እጅ በገናን ብቻ ሳይሆን ገና ለጋ ሳለች ወንጭፍ ስትበረታም የተሳለ ሰይፍ ትመዝ እንደነበር እንዴት ረሳህ? አንተ በከንቱ የሐይማኖት እስራት የተዘናጋህ፦ ካራ ስሎ የመጣ አራጅ ስጋህን ሲበልት የሀይማኖትህ ማደሪያ ነፍስህንም እንደሚያሳጣህ ስለምን ዘነጋህ? መታዘዝ መስዋዕት ከማቅረብ ቢበልጥም፥ አንዳንዴም እምቢ !ብሎ ክፉውን አጥፍቶ መጥፋት ከሰማዕትነት በእጅጉ ይልቃል። ብረትን የሚስለው ብቻ ሳይሆን የሚያዶለዱመውም ብረት ነው! ብረት ደግሞ በሸገርም ሆነ በየመዲናው የጓሮ አበባ ነው።

Comments are closed.