
By Admin
አብዛኛው አንባቢ የዚህን ግጥም ውስጠ-ትርጉም ነጥሎ ለመምዘዝ ይሳነዋል የሚል ግምት ባይኖረኝም፤ ጥረቱን ለማቅለል ሲባል ብቻ፡ አትኩሮት ይገባዋል ያልኩትን ቃል እና ሐረግ በተለየ የፊደል ቀለም አስቀምጬዋለሁ። መልካም ንባብ።
***
ከሞት ከፍቶ ሳለ … የእናንተ ዜና-ህይወት
ኢማም፣ ቄሱ ታስረው … ባይደርሱም ለፍታት
ሰፈሩ ተሰፍሮ … ባይኖር ፍራሽ፣ ድንኳን
ለሀዘን ቁጭ ካላችሁ … ከስልጣን፣ ከዙፋን፤
ከልም ባትለበሱ … ክልል ጋርዳችሗል
በድን ገላችሁን … ወርቅ ገንዛችሗል፤
ነውር ነው ብንቀር … ለቅሶ ደረስናችሁ
ሞታችሁን በቁም … አምላክ ካ’በላችሁ
ከእዚህ በላይ በረከት … ምን ዓለም አላችሁ?
እኔም ጓደኞቼም … ነፍስ ይማር አልናችሁ።
ከጅራፍ ጥይቱ … ባይተርፍልን ገላ
የምንመታው ደረት … የሚቧጨር ስጋ
አርፋችሁም ባይሆን … ቀብረናችሁ ልናርፍ
ዜና-ዕፍረታችሁ … ጡሩንባ ሲለፈፍ፤
ባትማሰሉንም … አጥንት ተካፍላችሁ
አዛምዶናልና … ደማችን ከእጃችሁ፤
እርማችሁን አንበላም … ቤት ውለን ከጓዳ
የኣንድ-ለኣምስት ዕድር … ይይዘናል በዕዳ፤
እኔም ጓደኞቼም … በልማታዊ ቃል
አባይ! አቦይ! አቦይ! … ወይ’አኔ! ወያኔ! ወይ’አኔ! ብለናል።
ጠኔ ረሃቡ ከፍቶ … ባይኖር የሚቀመስ
የሚዘገን ንፍሮ … ከቤት ስንመለስ
ከጉድጓድም ባይሆን … ከመቃብሩ አፍ
ያ ሙት አካላችሁ … ከፎቅ፣ ከቪላው ሲያርፍ፤
ሰብአዊም ባትሆኑ … ሰዎች ናችሁና
ህይወት፣ አቅልም ባይሆን … ነፍስ አላችሁና
የቁም ሞታችሁን … ባንዘክረው ቀኑን
“ፀረ-ሞት!” ነው ብሎ … ይከሰናል ጽዮን፤
እኔም ጓደኞቼም … አጉል ወግ አስሮናል
አደባባይ ወጥተን … ነፍስ ይማር ብለናል።
የሚጠጣው ጠፍቶ … የሚላስ ጠብታ
ዓይነ-ውሃችን ደርቆ … ባይፈሰንም እንባ
ገባን “ካምፕ-ሎጆ” … መጣን ለቅሶ ልንደርስ
የሞተውስ አርፏል … ለቋሚው ነው ማልቀስ፤
ስናውቅ ካድሬነቱን … የሙፍቲ፣ የአቡኑን
ውስጡን-ለቄስ ብለን … ሰምተን ቡራኬውን
ውስጡን መስቀል አርገን … ተሳልመን ሽጉጡን
እኔም ጓደኞቼም … ነፍስ ይማር ብለናል
እፍኝ አፈር ዘግነን … አፍረን በትነናል።
(ተፃፈ – ለግንቦት ፳ የሃያ-ሶስተኛ ዓመት የሙት ዝክር።)