
By Admin
መዳብ ፣ ቃጫ ሆኖ … አእምሮ ፦የራስ ፈርጥ
ገበያ ዋለና … ህሊና እንደ ሸቀጥ
የራሳችን ሳንባ … በሰው ትንፋሽ ሲሮጥ
ጡዋዋዋዋዋ! ብሎ ፈንድቶ … ሳናየው ሲለጠጥ
ከልብ ጋር ተካሶ … ከአእምሮ መፋረድ
በወርቅ ሽቦ ሳይሆን … በእምነት ክር ፣ ገመድ
አንገትን አስግሮ … ሃቅን ማሰተናገድ
ከስሎ ቡንንንንን! አለና … ሳይሞቀን ሲናደድ
አንደበትን መዳር … ከእውነት አዋዶ
አርጅቶና አፍጅቶ … የጥንቱ ሃይ፨ሎጋ፨ሆ
እልምምምምም! ብሎ ጠፈቶ … እንደ ወ ፏ ዶዶ
እንደ ዳይኖሰረስ … ሊቅ በሊቅ ተዋግዶ
በራስ ጎጆ ውሎ … ማደር በራስ ቀፎ
ከእኛው ወደብ መድረስ … በእኛው ታንኳ ቀዝፎ
ጎጂ ባህል ሆኖ … ተወግዞ ፣ ተነቅፎ
ድርግም ግም ምምምም! አለና … እንደ ቀልድ ተፋዝዞ
ይኸው ! ይኸው ድር አደራ
እኛነትን መግፋት … ግዜኛውን አቅፎ
አልቀረም ቦግግግግግ! አለ
ከሺን ማደባዘዝ … ሰቢን አጧጡፎ።
ሃሰትን መታገል … የራስ ስሜት ገልጦ
ሃቅን ለብሶ መጥቆር … እንደ ቆዳ ለምጦ
የአእምሮ እርሳስ … በሳንጃ ተቀርፆ
ፍፁም ተናቀና … የሰው ቀጭን አንገት
ክብር ሆኖ ሲሮጥ … ለአውሬ ዳልጋ ኩልኩልት
ማተቡ ተውጦ … ስጋው ሲደራረት
እንደ ዲገላ አውሬ … እንደ ሸለምጥማጥ
በእኛው ጥርስ ተነክሶ … የራስ ደም ሲመጠጥ
“ተዉ!” ባይ ጠፋና … ወግ እያየ ሲጦር
እየሞቱ መኖር
ይኸው! ይኸው ዛሬም አየን … ስልጣን አፍ ለጉሞ
ተጭነን ስንጋልብ … በቀነኛው በቅሎ
የሰው እበጥ ስናፈርጥ … የራስ ቆዳ ቆስሎ።
የራስ አቅምን ንቆ … ለጡንቸኛው ርዶ
ከጥቁሩ መጣቆር … ከነጩ ተናጥቶ
ለመክረሚያ ቤሳ … ስብዕናን ሽጦ
ከአንዳጁ እፍፍፍፍፍ! ማለት … ከአጥፊው አጥፍቶ
ከሰኪው ማሳካት … ከገንጣይ ገንጥሎ
ግዜን ተጠልሎ
ተው! ተው አንጂ ዜጋው … ምንኛ ነው ይሄ
ከአውራጁ ሆሆሆሆሆ! ማለት … እንደ ጨቅላው ቡሄ?
ትርፉ ትዝብት እንጂ … ረብ ላይኖረው ሲሳይ
ሃገር ወገን ላይጠቅም … አዋሽ ሆኖ አባይ
በልከራርም ጃኖ … በእንምሰል ካባ
ማን ለማን ተጫጭቶ … ማን ከማን ሲዳራ
በሞቴ ንገረኝ … የቱ ትዳር ረባ
ከወጪው ተፋቶ … ከገቢው ሲጋባ?
ከሃሰት ተጣምቆ … እውነት መገነዙን
አብሮ አደግ ሳይሸኝ … ከባዳ መለሱን
ለሰው በረት ውበት … የራስ ጓዳን ፍቆ
አስመስሎ ማደር … ዘመነኛን አቅፎ
ጡንቸኛን ተላጥፎ
ይቅርብን እንተወው … እንኑር በራስ ቀፎ
ለምን ያሳርረን … “ልደር” ማለት ጦፎ
ግን …ግን እንደው ምስጢሩ
ምንድነው መረቁ
በራስ አካል መዳፍ … እራስን መስረቁ
ጀማሪን ማጃመር … ከዕላቂው ሳያልቁ?
ፈፅሞ አይፈታም … የእኛስ ቅኔ ስንቁ
ከጨለማው መጭለም … ደምቀው ከደማቁ
ሰሙስ ጆሮ ይቀፋል … “እንኑር” ነው ወርቁ?
*እንደ ያኔው ሁሉ፤ ዛሬም በምደርሳቸው ጽሁፎች ወስጥ የአንድ አንድ ቃላቶቼን ስውር ትርጉም ማግኘት እንደሚቸገሩ የሚነግሩኝ ጓደግኛቼ ቁጥር ብዙ ነው። ይህን ለማቃለል ሲባልም አንባቢ የተለየ አትኩሮት እንዲያደርግ የምፈልግበትን ቃላት እና ሃረግ በተለየ ቅርፅ (italicized font) አስቀምጬዋለሁ። ለምሳሌ፦ አእምሮ = አንጎል = coiled brain tissue ፤ ራስ = ጭንቅላት = head ፤ ሊቅ በሊቅ = ምሁር በምሁር.
1983 ዓ.ም.