Post

እኛ እና ነብር

እኛ እና ነብር

By Admin

በወኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? – ትንቢተ ኤርምያስ 1323   

ይህን ጥቅስ ብዙዎች ይዘፍኑታል፣ እንደ መልካም ቃልኪዳን ይሰብኩታል። ለእኔ የሚሰጠኝ ትርጉም ግን የተለየ ነው። የበረከት ሳይሆን የዕርግማን ቃል እየመሰለኝ መጥቷል። በዘር፣ በሀይማኖትና በቋንቋ የመዥጐርጐራችን ምስጢር የማይጠብ፣ የማይፈታ፣ በአጠቃላይ በፍፁም የማይዋሃድ ልዩነት እንደሆነ የሚያሳብቅ አባባል እንደሆነ አድርጌ መውሰድ ከጀመርኩኝ ቆይቻለሁ። ለምን ብባል፦ የቱንም ያህል ልዩነታችንን አርመን የጋራ በሆነው ምድራችን ላይ ተስማምተን እንደ አንድ ህዝብ ለመኖር ብንጥርም፥ ድንገት ደርሶ የረጋውን አማስሎ፣ የጠራውን አደፍርሶ ወደ ዜሮ የሚመልስን የእኔነት አሜኬላ መቼም አይጠፋም።

ምናልባት “ልመደው” ትሉኝ ይሆናል፤ ልለምደው ግን አልቻልኩም። በተለይም ድግሞ ይኸው የእኛ መዥጓርጐር ሀይልና ድፍረት የሰጣቸው የህወሃት ሰልፈኞች ዋሽንግተን ዲሲ ላይ “ወያኔነት ኢትዮዽያዊነት ነው” ብለው እምበር ተጋዳላይ ሲሉ ስሰማ፥ መከፋፈላችን ይበልጥ አበሸቀኝ። ያ የመፈክር ስንኝ እንደ ጥርኝ ሽታ ከረፋኝ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ለብሼው የኮራሁበት፣ ለዘመናት ለስልሶ ሲሞቀኝ የነበረው ኢትዮጵያዊነት ሻክሮ ሊኮሰኩሰኝም የፈለገ መሰለኝ።

ተምሮ ትልቅ የመሆን ተስፋዋን በጀርባ ቦርሳዋ አዝላ ከትምህርት ቤት የምትመለስ የሰባት ዓመት ህፃን ላይ ጥይት አዝንቦ – በደም አበስብሶ ከመንገድ ማስቀረት ነው ኢትዮዽያዊነት? ዘጠኝ ወር አርግዛና አምጣ የወለድችን  እናት – የመከራና የቅጠል ሸክም አጉብጦ ባቆሰለው ጀርባዋ አዝላ ለወግ ያበቃችውን ኣንድ ልጅ ገድሎ በበድኑ ላይ አስቀምጦ በዱላ መቀጥቀጥ ነው ኢትዮዽያዊነት? ከእቶን እሳት ማምለጫ ያጣ እስረኛ ላይ የተኩስ እሩምታ ከፍቶ – ደም እንደ ዘይት እያርከፈከፉ የሰው ስጋ መጥበስ ነው ኢትዮዽያዊነት? አርሶ የሚያበላን ሀገረኛ ገበሬ በጐረቤት ሀገር ሚሊሺያ ማስደብደብ ነው ኢትዮጵያዊነት? ከዳር እስከ ዳር ሀገር በሃዘን ልቡ ተሰብሮ አንገቱን ሲያቀረቅር – በወገን ደም ሰከሮ ከበሮ እየደለቁ መሽከርከር ነው ኢትዮዽያዊነት? መወየንና ወያኔነት ትርጉሙ ይኼ ነው –ወያኔነት ኢትዮዽያዊነት ነው የተባለው? “እነርሱ ምን ያድርጉ ከእኛ ሰው ሲታጣ” ነው ያለው ድምፃዊው … .

የእኛ የስልጣን ዋንጫ – የግለኝነት ጽዋ እስኪሞላ የስንት ንፁሀን ደም መፍሰስ አለበት? ስንት አዛውንት እናቶችና አባቶች በእንባ ወደ መቃብር መወረድ አለባቸው? አምባ ለይተን እርስ በእርስ መካሰሱን ትተን ወደ አንድነት እስክንመጣ ስንቶች በዜግነታችን ላይ ይቀልዱበት? በአደባባይ በኢትዮጵያዊነታችን ላይ ይዛበቱበት?

የሰሞኑ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “ጎሠኛነት በባዶ ሜዳ” ጽሑፍ ሀቀኛውን ከሐሰተኛው፣ እውነተኛውን ከአስመሳዩ ልዩነት ሳያደርግ ስደተኛውን በጅምላ በአንድ ስልቻ አጅሎ የወቀጠ ክሪቲክ (critique) ነው ብዬ ባምንም፥ እውነታ የለውም ብዬ ግን ለመካድ አልሞክርም።

ፕሮፌሰሩ፦ ኢትዮጵያዊነት ሲሰበክ ጠበል እንደዘነበበት ክፉ መንፈስ የሚንዘፈዘፍ የብሔር ብሔረሰቦች ልክፍት የተጠናወተው መንግስት ለሃያ ኣምስት ዓመታት በከተመባት መዲና እየኖሩ፣ የዘር ሸረሪት አድርቶበት በጐሳ ድር ከላይ አስተዳደር አንስቶ እስከ ታች የመፀዳጃ ቤት ገንዘብ ተቀባይ ድረስ በአንድ ብሔር በተተበተበ አየር-መንገድ እየበረሩ፣ ወደ እዛች ምድር ከዘርና ከዘረኝነት ውጪ አንዳችም የፖለቲካ ሸቀጥ ያለ ከፍተኛ ቀረጥ እንደማይወጣና እንደማይገባ እያስተዋሉ – “ለምን ስደተኛው አማራና ኦሮሞ ብቻ ብሎ ቆመ” ብለው መቆጣታቸው አልገባኝም። እንዳውም ቁጣ የሚያስነሳው፥ የእኔም የዛሬ ጽሁፍ ዋና መንፈስ፦ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ ሌላም ሌላም እያሉ ትልቁን ጠላት – ቀንዳሙን ኣውሬ በመናቅ በዘር በድርጅት ተከፋፍሎ እርስ በእርስ መነካከስ ነው። 

ያም ሆኖ ግን የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ምሬት መነሻ አልባ ነው ብዬ አልደመድምም። የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ-ፈንታ አስመልክቶ ሰቆቃው ዋቆ ከለንደን ያዩልንን (የዋጁልንን) የሚያሳቅቅ ራዕይ ያዳመጠ ሀገረኛ፥ ለተቃውሞ ጽሑፍ ብዕር ቢያነሳ አይደለም ለሰልፍ ሰይፍ ቢመዝ አይከሰስም። እሳቸው “ስደተኛ” ብለው በአንድ ያከበቡትን ዲያስፖራ፥ እኛ “አስመሳይ” “ሆድ-አደር” “ዋልጌ” እና “ይሉኝታ ቢስ” ብለን በሰንጠረዥ ብናጥረው ግን፥ ጽሑፉ የአብዛኛው ስደተኛ ፖለቲካዊ ባህሪ መለያ (ፕሮፋይል) እንደሆነ በሚገባ ያስተማምነናል። የኮምፒዩተሩን ማይክራፎን እንደ ክላሽ፣ ካሜራውን ደግሞ እንደ ጦር ሜዳ ባይናኩላር ነጋ ጠባ እየወለወለ በየሶሻል ሚዲያው ቦታ ቦታ ይዞ የሚታኮሰውን “አርበኛ” ነኝ ባይ ቧልተኛ በትክክል ገልፀውበታል።

ፕሮፌሰሩ ባይሰደዱም ስደተኛ አስርገው መሐላችን ያስገቡ እስኪመስለኝ ድረስ፥ የአጠቃላይ ዲያስፖራው ማለት ባልችልም የአብዛኛው “ስደተኛ” የፖለቲካ ትግል መዝሙር “የሚሻክርን ስደት ለማለስለስ” በተቃኘ ክራር እንደሚከር ደርሰውበታል። እንደ ህዝብ ነፃ ለመውጣት የሚከፈለው መስዋዕትነት የመብዛቱና የመክበዱ ምስጢርም – የራስን ግለሰባዊ ማንነትን ነፃ ለማውጣት ሲባል በሚደረግ የማስመሰል “ብሔራዊ ተጋድሎ” ስለተተበተበ ነው።   

በለስ ቀንቶን የ Zeus ልጅ Ares ከፊታችን ተሰልፎ አዝምቶን ግንቦት 7 ኣራት ኪሎ ገብቶ ቢያድርና፥ ከተማ ውስጥ ከሰው ፍጡር ጋር ውሎ ማደር ያልሆነለት ህወሀትም አብሮ-አደጉን አውሬ ፍለጋ ተመልሶ ጫካ ቢገባ፥ ይኼ ዛሬ በስንዴ እንጀራ ኩፍ ያለ ሠውነቱን “እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ” በምትል ሚጢጢ ካኔቴራ ጠቅልሎ – የሚሽሊን (Michelin) ጐማ ሎጐ መስሎ በየአውራ ጎዳናው የሚንከባለለው አትናገሩኝ፣ አትንኩኝ ባይ አርበኛ፥ በንጋታው – ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ክብር እንኳን ሲባል ካኔቴራውን ሳያጥብ እንዲሁ ገልብጦት “እኔም ጌታቸው አሰፋ ነኝ” ብሎ በየስደተኛው ቢሮ ደጃፍ ሲጋፋ እንደሚውል ፕሮፌሰሩ ብቻ ሳይሆኑ እኛም ከተረዳን ቆይተናል። የእስካሁን ዝምታችን ምስጢር ደግሞ አለማወቅ ሳይሆን መተዋወቅ ነው። አልፎም ዋና ጠላትን ለይቶ ማወቅ።

አሁንም ቢሆን ህወሃትን የመሰለ ባለ ረጅም ቀንድ ኣውሬ ትተን “አንተ እንዲህ ነህ” “አንተ እንዲያ ነህ” እየተባባልን እርስ በእርስ መዋጋቱ ለማንም አይጠቅምም። ህዝብ እያለቀ፣ ሀገር እየፈረሰ፣ የዜግነት ክብር እየተዋረደ መደጋገፉ ቢከብደን እንኳ መደነቃቀፉን መተው ይበጀናል። በየትኛውም ሰልፍ ለቆምን ተቃዋሚዎች፣ የትኛውንም ቋንቋ ለምንናገር እውነተኛ ለውጥ ፈላጊዎች – ብሔራዊ መዝሙራችንን “Down Down ወያኔ!” አድርጐ በወል መታገል ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው።

አማራው በዘር ይደራጅ – አይደራጅ፤ በአማራው አደረጃጀት የህወሀት እጅ አለበት – የለበትም፤ አርበኞች ግንቦት 7 የተኮስው ከግንባር ነው – አይደለም ከኒያላ ግንብ ላይ ነው፤ … ወዘተ የሚለው ሰሞነኛ አተካራ የታጋዩን ምራቅ ከማድረቅ ባሻገር ትግሉን በኣንድ ምዕራፍ ወደፊት ፈቀቅ አያደርገውም። አማራው መደራጀት ብቻ ሳይሆን ከዛም አልፎ የህልውናውን ስጋት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚያጠፋበት ካልሆነም እራሱ የሚጠፋበት መራር ትግል ውስጥ መግባት አለበት ብዬ አምናለሁ። ለዚህ የህልውና ትግል ዘለቄታዊ ስኬት ተዋንያን (stakeholders) መሆን ያለባቸው ደግሞ የብሔሩ ተወላጆች ብቻ ናቸው ብሎ ማሰብና የሌላውን ዕርዳታ ለማሳነስ ወይንም ለመከልከል መሞከር ግን አላዋቂነት ነው። ዛሬ በየሶሻል ሚዲያው “አማራው የዓይኔ ብሌን ነውጠባቂው እኔ ብቻ ነኝየማንንም ድጋፍ አይፈልግም” የሚሉት ግለስቦች ቆም ብለው የዓይናቸውን ብሌን ከጨረር፣ ከአቧራና ነፋስ የሚከላከሉበትን የመነፅር መስታውት ደግመው ማስተዋል ያለባቸው ይመስለኛል። ከዓይን ብሌናቸው በብዙ እጥፍ የሰፋ እንጂ የጠበበ ወይንም ደግሞ በልክ የተቀረፀ አይደለም። ትዕቢት ብቻ ሳይሆን የጦር መሣሪያም እስካፍንጫው ድረስ የታጠቀውን የህወሃትን ሰራዊት እጅግ ባነሰ ትጥቅና ስንቅ ገጥሞ ያለው የአማራ ገበሬ ከየአቅጣጫው ሰፊ ድጋፍና ዕገዛ ያስፈልገዋል።

አዎ አንወሻሽም! የዚህ የሰሜኑ ትግል ማራቶን መነሻ ወልቃይት ናት። የመደምደሚያው ሪቫን (finishing line) ግን ነፃነት እንጂ የተከዜ ወንዝ አይደለምተጋድሎው የተዘረፈን መሬት ከማስመለስ ባሻገር በካቢኔትና በካህናት መተካካት ሳይደለል በሥርዓት ሞት መደምደም አለበት። ይኽ ደግሞ አማራው ከሌላው – ሌላውም ከአማራው ድጋፍ ማግኘትን ግድ ይላል። ከህወሃት ውድቀት ማግስት አንስቶ ቢያንስ ለቀጣይ ብዙ ዓመታት ስልጣን የሚያጓጓ ወንበር ሳይሆን ከግራ ከቀኝ የሚያላጋ ወጀብ እንደሚሆን ቅንጣት አልጠራጠርም። ዛሬ ያንን ማዕበል መተንበይ ተስኖን እንዲሁ በአፍቅሮ-ስልጣን እርስ በርስ ለመንገስ ስንታኮስ ይህ በብዙ ንፁሀን ደም የቀላ የድል ወጋገን ተመልሶ እንዳይመሽ እፈራለሁ። ያ ከሆነ ግን … እውነትም … ንጋት ስጋት የሚሆነን ብርሃን ናፋቂ የጨለማ እስረኞች ነን። ለባርነት የምንሳሳ የነፃነት ህልመኞች።

Comments are closed.