Post

እውን  ልጅ  የእናቱን  ሰርግ  አይበላምን?

እውን ልጅ የእናቱን ሰርግ አይበላምን?

እነሱ እኛን  ሆነው፣ የእነሱ  ሁሉ  ለእኛ  ትክክለኛነቱን  ብጠራጠርም፤ ፈረንጆች  ስለ  ባህል  ከሚናገሩት  ብሒል  መካከል  አንዱን  ለጽሁፌ መግቢያ  በረንዳ  ባደርገው  ደስ  ይለኛል።

A tradition may be good; but even the best tradition shouldn’t continue forever. Tradition, if continued for too long, it will corrupt people

የሚሉት  የባህር  ማዶ  ሰዎች፡ ለእኛም  አንድ  ነገር  የሚያስተምሩን  ይመስለኛል። እነዚያን፦ “የትኛውም  ባህል  ወይንም  ልምድ  ዘልአለማዊነት የለውም፤ ይኑረውም  ቢባል፣ ተብሎም  ቢሞከር  መጨረሻው  የሰው  ጥፋት  እንጂ  የሰው  ልማት  አይሆንም”  የሚሉት  ነጮችን፦ እንዴት  ተደርጎ ባህል  ወይም  ልምድ  ሰውን  ያበላሻል  ብዬ  መጠየቅ  ብወድም፥ የባህልን  (የልምድን)  ኢ-ዘላለማዊነት  ግን  ተቀበዬ  እደግፍላቸዋለሁ።

እዚህ  ላይ  ሃሳቡ  ከሃሳቤ  ጋር  የሚጣረዝ  አንባቢ  እንደሚኖር  ባውቅም፣  “ምን  ማለትህ  ነው?”  የሚል  አእምሮም  እንደሚኖር  አልዘነጋም።

ባህል (ልምድ፣ ወግ፣ ትርክት፣ ምሳሌ፣ ቅኔና ወዘተ) ካለፉት  አያት  ቅድመ-አያቶቻችን  ለምናልፈው  ለእኛ  እንደደረሰን  ሁሉ፤  የምናልፈው  እኛም ለመጡት  እና  ለሚመጡት  ደግሞም  ለሚያልፉት  ልጅ፣  ልጆቻችን  ማስተላለፋችን አይቀሬ ነው። እንዲህ እንዲያ ሲባልም፡ እኛ ኢትዮጵያውያኖች  “ኢትዮጵያውያን” የሚያስብለንን ባህል፣ ወግ እና ልምድ በሙሉም ባይሆን በከፊል ይዘን ለመጠበቅ ችለናል። የወደፊቱን አንድዬ  ይውቀው  እንጂ።

አበው  ከሰሙትና  ከነበሩበት  ዘመን  ባህል  ጋር  አጣጥመው  “እንሆ!”  ያሉን  ልምዳቸውም  ሆነ  ወግ  እና  ምሳሌያችው፡ ዛሬ  ለእኛ  እና  እኛ ላለንበት ዘመን  “ኦፍሳይድ” (offside)  ገብቶና  “ፎሪ” ወጥቶ፣ ፊሽካ  አስነፍተን  ወደ  ኋለኛው  ዘመን  የመልስ-ምት (free kick)  ማስመታታችን፡ ከፈረንጆቹ  ብሒል  ጋር  በመስማማታችን  አይሆን?

ድሮ  ድሮ  አባቶቻችን  ባይሆኑም  አያት  ቅድመ-አያቶቻችን  ሲተርቱ  “ውሽታም  ልጅ  የእናቴን  ሰርግ  በልቻለሁ  ይላል”  ይሉ  ነበር። በአንድ ድንጋይ  ሁለት  ወፍ  እንዲሉ፡ ይህ  ተረት  ልበል  ምሳሌ  እውነት  በነበረበት  ዘመን  የነበሩ  ሰዎቻችን፡  አንድም  የውሸታምን  ሃያል  ቀጣፊነት፣ ሁለትም  ከጋብቻ  በፊት  የሚኖር  ፍሬ  ማፍራትን  ሲኮንኑበት  ኖረው  አልፈዋል።

ታዲያ፦ የእናቱን  አይደለም  የአያቱን  ሰርግ፡ መንጋጋ  አብቅሎ  አጥንት  የጋጠ  ትውልድ  በበዛበት  በዚህ  ዘመን  እንዲህ  ብዬ  ብተርት  ውሸታሙ  እኔ  እንጂ  ሌላ  ማን  ሊሆን?

ዛሬ  ዛሬ  በከተማችን  አዲስ  አበባ  ከአንድ እና ሁለት  አንሰቶ፡ በሃምሳ  እና ስድሳ  መኪና  አጃቢነት  የሚደገሰውን  “ሠርግ”  ለተመለከተው፡ ሠርግነቱን  እንጂ  የጋብቻውን  ጋብቻነት  እና  የሙሽሪትን  ሙሽራነት  አዋቂ  የለም። ቢኖርም  አንድ  እግዚአብሔር፣  ካልተደባበቁም  እርሷና እርሱ፣  ሙሽሪት  እና  ሙሽራው  ናችው።

ምንም  እንኳ  ዘንድሮ  ወንደላጤነት  ባያስመርርም፥  አንደው  ለክፉም  ለደጉ  ከአንድ  ሁለት  መሻሉ  አይቀርም  ብዬ  ትዳር  ብጤ  ባስብ፡ ባልነት እስከ  “መል”  ዕለት  አንጂ፡  የ”ቅልቅሉ”  ማግስት  የሚቀላቀለው  “ውሪ”  እና  “ማቲ”  ሳይወዱ  በግድ  የእንጀራ  አባት  ማድረጉ  አይቀሬ  ሆኗል። መቼም  በእዚህ  ሁኔታ  የእኔኑ  የእግዚአብሔር  ጣት  የጋብቻ  ቀለበት  አጥልቆ  ከምመለከት፤ የጠላቴን  ሌባ  ጣት  የጠመንጃ  ቃታ  ዉስጥ  ማየቱን መርጬ፡  አርፌ፣  አደብ  ገዝቼ  ብቀመጥም፤ በተጋበዝኩበት  የጋብቻ  በዓል  ላይ  የታዝብኩት  ድርጊት  ግን  ከማሳቅም  አልፎ  አስገርሞኛል።

ከእናት  ወይ  ከአባቱ  የጋብቻ  ዕለት  በፊት፣ ክርስትና  እና  ደቱን  አክብሮ፣ ሚኒስትሪ  ወስዶ  አለበለዚያም  ማትሪክ  ወድቆ፦ በወላጁ  የሠርግ ቀን  ከተጋባዥ  ዕድምተኛው  እኩል  ተሰይሞ  የተጋበዘ  እና የጋበዘ፣ ጢምቢራው  እስኪዞር  ጠጅ  እና  ጠላ ሌላ  ሌላውንም  ቀምቅሞ የዕድር ብርጭቆ፣ የውሰት  ሸክላ  ሳህን  አንኩሮ  እና  አንኩቶ  የሙሸሪት  ግን  የእናቱን  ናላ  ያዞረ፤ ወይ  ደግሞ  የአባቱን  ግን  የሙሽራ  ተብዬውን  ራሰ በረሃ  በንዴት  ላብ  ያወዛ  “ጃዊሳ”  አይታጣም  ብልም፥ እሰቲ  በእርግጥ  ከአየኸው  እና  ከደረሰብህ  ንገረን  ካላችሁኝ  ግን፡ ከእናቷ  ጋብቻ  በፊት ተወልዳ ለእናትዋ  ሰርግ  እግዜር  እድሜ  የቸራት  የስድስት  አመት  ህፃንዋ  “ፌቪ”  እስቲ  የሰርግ  ዘፈን  አውርጂልን  ተብላ  በትለመን፦ “ማሚዬ ለምዳለች፣ ማሚዬ  ለምዳለች  ከእናቷ፣  ከአባቷ …” ብላ  የጀመረችወን  ሀረግ  እንኳን  ሳትጨርስ  ኣስራ-ስድስት  መዳፍ  ከአፏ  አልፎ  ፊቷንም የአፈናት ምስኪን ህጻን ስትጎራበተኝ፤ እንደው ለወጉ በሚደረገው  “የምስራች”  ግን  ልጇ  የደፋችውን  ድፎ  ዳቦ  አሳዝላ፣  እግዜር  በፀሃዩ  ብርሃን እንዳያያት  ነው  መሰል በውድቅት  ለሊት  ሚዜዎችዋን  ከወላጆችዋ  ቤት ያስማለደች፡  ጥሩ  ባለሞያ  ልጅ  ያላት  ሙሽሪት  ተዛምዳኛለች።

ሰዎች  ሆይ  ምን  ዋጋ  አለው፡ ብዙ … ብዙ  ላወጋቹህ  ብፈልግም  መስከረም፣ ጥር  እና  ሐምሌ  በመጣ  ቁጥር  ሳልፈልግ  በግድ ሚዜ  ሁን እየተባልኩ  ለጉድ  መሸፈኛ  የምበጣው  የሌባ  ጣቴ  ህመም  ብዕሬን  አላስጨብጥ  አለኝ። ታዲያ  ለምን  አንድ  ቀን  ተቆርጦ  ከመውደቁና  እኔም ጽሁፍ  ከማቆሜ  በፊት፡ ባህል፣  ልምድ፣  ተረት እና ምሳሌ  ሁሉ  “ፉርሽ”  ሊሆን የሚችል፦ አምላክ  እንጂ  ሰው  የማያነበው  “expire date” እንዳለው   አንተማመንም?

አደራችሁን  ታዲያ፦ ሠርግ  ነው  ተብሎ  በየመንገዱ  ሲግተለተሉ  ከምታዩት  መኪኖች  መካከል፡  መሶብ  ጭና  ክላክሷን  እያንባረቀች ከምትጓዘው  “ፒክ ኸፕ”  መኪና  ላይ  የሃገር  ባህል  ልብስ  ለብሳ  “ሙሸራዬሙሸራዬየወይን አበባዬ …”  እያለች  አዚማ  የመታስዜመው፣ የሁለተኛ  ደረጃ (high school)  ተማሪዋ  ልጃገረድ፡ እሷ  የእነሙሽሪት  ተብዬዎቹ  የበኩር  ልጅ  ትሆናለች  እንጂ፥  አፌን  ሞልቼ  ነች  አላልኩም። ደግሞስ  “አለ”  ብትሉ፦ ልጅ እና እናት በአንድ  የበሬ  ስጋ፣  በአንድ ቀን፣ በአንድ  ድንኳን  የሚዳሩበትን  የጉድ  ዘመን  ልናይ፣  ይሄ  ምን ያስደንቃል።

1981 ዓ.ም.

Comments are closed.