Post

እግዜርን በሆንኩኝ …

እግዜርን በሆንኩኝ …

By Admin

 

 

መንፈሷ … ከውስጧ
ስሜቷ … ከአካሏ
እንደ ጨርቅ ወልቆ
ብቻውን ሲንሳፈፍ … በሙታን ሸለቆ

ገና ሳለች ህያው … ለብሳ እርጥብ ሥጋ
ከሞት መንደር ቆማ … እንደ ሓውልት ተተክላ
ባያት በተመስጦ
ለጋ አጥንቷ ጎብጦ

ምን እንደምታስብ … ማውቅ ቢያዳግተኝ
እንደ ትንሽ ጣቷ … በሃሳብ ብታኝከኝ
ሓጢያት ሊሆንብኝ
ክፉ አምሮት አገኘኝ …

ለኣንዲት ሰከንድ ብቻ
የሌለውን አቻ
‘እግዜርን በሆንኩኝ’
ብዬ ተመኘሁኝ!

እንደ ኤርትራ ባህር … ሀዘኗን ልከፍለው
ውስጧን ያራሳትን … እንባዋን ላደርቀው
ለቅፅበትም ቢሆን
ብችል እሱን መሆን?

ኣጥንት ሥጋ ለብሶ … እርሱ እኔን ከሆነ
እኔም እርሱን መሆን … ቢያስችለኝ ምናለ?
አውሶኝ ጥበቡን

ሰጥቶኝ ተኣምራቱን
እንደ ማርታ ወንድም … ከፊቷ ባቆመው?
ከጉድጎድ አውጥቼ … ውዷን ባራምደው?

Comments are closed.