Post

ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን “የልማት ተነሺ”  ሆነች?

ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን “የልማት ተነሺ” ሆነች?

By Admin

ለዚህ ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን መስቀል ኣደባባይን አስመልክቶ የኦርቶዶክስ እምነት ቤተክርስቲያን እና የኣዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እንደ ህፃናቶቹ ጭቃ የሚወራወሩት መግለጫ ነው። ቤተክርስቲያን … ከጥንት ከጠዋቱ ጀምሮ አደባባዩ የእኔ ንብረት ነው ስትል፥ የኣዲስ አበባ ከንቲባ ደግሞ … ህዝብ በከፈለው ቀረጥ የለማ የህዝብ አደባባይ ነው ብለው ሞግተዋል። ዳኛ ሆኜ መፍረድ ባልችልም፥ ታዛቢ ሆኜ ግን ኦርቶዶክስን፦ የእጅሽን ነው ያገኘሽው ብያታለሁ።   

የዛሬ ሁለት ዓመት፥ በወርሃ በመስከረም 2019 . . . … የሸኔ ስውር ክንድ በሆነው ኦህዴድ ቤተክርስቲያን እንደ ጧፍ ስትነድ፣ ምዕመናኑ እንደ እንስሳ ሲታደኑ፥ ኦርቶዶክስ በቃ!ብላ ተነስታ ነበር። የኣዲስ አበባ ቅድስት ስላሴም፦ መሬት አንቀጥቅጥለሆነው ሰለማዊ ተቃውሞ ተዘጋጀሁ ስትል፥ እኛም አበጀሽ የኛ ሎጋለማለት ቢከብደን አበጀሽ የጓደኞቻችን እምነትስንል ደግፈን ነበር ። ኋላ ግን፥ አፍታም ሳይቆይ፥ ቤተክርስቲያኗ ግማሽ ሰዓት ባለሞላ ዝግ ስብሰባ፥ ከይሁዳው ኣውራ ጋር በቢሮአቸው መክራ፣ ከእያንዳንዱ ተሰብሳቢ ፊት ለፊት የተደረደረ የቡና ሲኒ የሚታይበት ፎቶግራፍ በመለጠፍ … ጠቅላይ ሚንስትሩ ቃል ስለገቡልን የተቃውሞ ሰልፉን ሰርዤዋለሁ ” አለች። እኔም በወቅቱ የሰጠሁት አስተያየት … ተሰብሳቢዎቹ እንደተደለሉበት ቡና … እንደወረደ  … እንዲህ የሚል ነበረ፦ 

መስከረም 2019 እ. ኤ. አ

የሰንበት ት/ቤት አባ እና የባቄላ ሽሮ አንድ ናቸው … ድንፋታቸው እንጀራ እስኪቀርብ ድረስ ነው። የአዲስ አበባው ሰልፍ አስተባባሪዎች ችግራቸው መፍትሔ እንደሚያገኝ እና ጥያቄያቸው እንደሚመለስ ቃል ስለተገባላቸው አይደለም ተመልሶላቸውም ቢሆን እንኳ ይህን ሰልፍ መሰረዝ ወይንም ማስተላለፍ አይገባቸውም ነበር።

በየክፍለ ሀገሩና በየአጥቢያው የፈሰሰው የአገልጋይ ወንድም / አባቶቻቸው ደም በግፍ የፈሰሰ እንጂ የሚመለስ ጥያቄ አይደለማ! ግና አስተባባሪ ኮሚቴው ክርስቶስን በሰላሳ ዲናር እንደሸጠው የአስቆርቱ ይሁዳ ወንድምና አባቶቹን በቤተመንግስት አንድ ሲኒ ቡና ለወጠው። @ቃል ተገባልን ሲሉ ቃል የማያጥራቸውን ጠቅላይ ሚንስትር ዋቢ አድርገው ህዝቡን ሐሞቱን አፈሰሱት።

የዛሬ ሁለት ወር ቀርቶ ከሁለት ሰዓት ቦኃላ ይህ ሰላማዊ ሰልፍ ዳግም ቢጠራ ቀድሞ በነበረው ወኔና መንፈስ አልፎም እንደ ቀድሞው ሙሉ እምነት ጥሎባቸው የሚወጣ መስሎዋቸው ይሆን? እስከ ሁለት ወር እነ አጅሬ በምርጫም ይሁን በሜንጫ ይህንን ኮሚቴ ሁለት መቶ ሰባሰባት ቦታ ይሰነጣጥቁታል። ግን ግን ይህ አስተባባሪ ኮሚቴ አዴፓ ይሆን እንዴ? … ተልፈሰፈሰብኝ!

ይኽው ዛሬ ሀገር ሲረጋጋ … ከሀዲው ሀዲዱን ሲይዝ፥ ቤተ-እምነቷን ከመስመር አስወጥቶ የልማት ተፈናቃይ አድርጓት አረፈው። የምዕመናኖችሽን ደም አርክሰሽ፥ የይሁዳን ቃል ያከበርሽ ገና ብዙ ትከስሪያለሽ። ትንሽ ጊዜ ይቀርሻል … ከኣደባባዩ አይደለም ከቅድስተ ቅዱሳኑም ጓዳ ያፈናቅልሻል።

ከዚህ ቀደም እንዳልኩት፦ እነዚህ ፈጣን በሆነ የማስመሰል ፈረስ እየጋለቡ ቀን ቀን ቀራንዮ እየዋሉ ማታ ማታ ሰዶም ጎሞራ የሚያድሩት አማኞችነን ባይ ዘመነኞች …  ሸርሽረው የሚንዱት የሀገሪቷን ህዝብ ኣንድነት ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ እምነትም ጭምር ነው።

ኢትዮዽያ የነፃነት ብቻ ሳይሆን የእምነት ፅናትም ተምሳሌት ናት። ነበረች ልበል መሰለኝ፥ ከርሞ እንዳይቆጨኝ። ጠግቦ በሚያድረው ህብረተሰብ መካከል ሀገራችን ብቸኛ የረሐብ trade mark ሆና የመቆጠሯ ምክንያት፥ የሚበላ አለመኖር ሳይሆን በእምነት የመኖር ምግባር ነው። ባሳለፍናቸው ዝናብ አልባ ዘመናቶች ሁሉ የዜጎቻችን እንደ ቅጠል የመርገፍ ምስጢር፥ የድርቁ ብርታት ሳይሆን የአማኙ ፅናት ነው። አሊያማ፦ እንደ እሪያ ያገኘውን በልቶ ካገኘው ጋር ስሪያ ጠፍቶት አልነበረም። ማተብን በጥሶ፣ አህያና ከርከሮ አድኖ ነፍስን ከማቆየት፥ ለእምነት ትዕዛዛቱ ታምኖ፣ መንምኖ መሞትን ክብር አድርጎት ነበር። ይህ ጽናት ያልገባቸው የብልፅግና ወንጀለኛውያን (“ወንጌላውያን) የት ድረስ እንደሚጓዙ ከነገ በስቲያ የምናየው ይሆናል። የቤተክርስቲያኗ የጽናት ውርስስ? የከርሞ ሰው ይበለን።

Comments are closed.