በሆነ አጋጣሚ የተዋወኩዋቸውና ምክንያታዊ በሆነ የስራ ግንኙነት ለአመታት አብረን ያሳለፍን አንድ ከጐንደር የመጡ አዛውንት ግርምትና አድናቆታቸውን ለመግለፅ የሚጠቀሙባት ሐረግ ነበረች – ኧረ በአባ ጃሌው!
እኔም ዛሬ ጎንደር ላይ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ በየድህረ-ገፁ ላይ የተለቀቁትን መረጃዎች ተመለከትኩ – አዳመጥኩና በዝምታ ማለፍ ስላልቻልኩ የእኛን አዛውንት ሐረግ ተበደርኩ።
በእርግጥ “ሰላማዊ-ሰልፉን ተቀላቀሉ” የተባሉትን የሀይማኖት አባቶችና መሪዎች ስመለከት፣ “ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ!” የሚለውን ቃለ-መሀላዊ መፈክር ሳነብና “በኦሮሚያ የሚደረገው የወንድሞቻችን ግድያ ይቁም!” የሚለውን የማስጠንቀቂያ መልዕክት ሳዳምጥ – ታሪክ ራሱን ደገመ! አልኩ አንጂ ፍፁም እንግዳ ሆኜ እጅግ አልተገረምኩም። ለምን? ካላችሁኝም፦ ለመይሳው ካሳ ክፋዮች፡ ሀገር ማለት ፅላት ናት። ቅዱስ፣ ንፁህ፣ ማንም እንደፈቀደ የማይነካት! ከማንም ከምንም በላይ የሚያስቀድማት! ከፍ አድርጎ በእራሱ ላይ እንጂ በትከሻ – በጀርባው እንኳን የማይሸከማት። ያም ቢሆን ግን እነዚህ ሰልፈኞች፦ አባቶችና እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች በዚህች ታሪካዊ ቀን ለደገሙት ኢትዮጵያዊነት መታሰቢያ ትሆነኝ ዘንድ ይህቺን አጭር ፅሁፍ አዘጋጀሁ።
ኢህአዴግ የተሳፈረበት – ህወሀት የሚዘውረው ባቡር ነዳጁን ሳይሆን ሐዲዱን ጨርሱዋል። ከዚህ ቦኋላ የሚደረግ ጉዞ በራስ እና በንብረት ላይ ጉዳት ከማደረስ ውጪ ተጓዡንም ሆነ አጓጓዡን የሚያደርስበት ፌርማታ (ጣቢያ) አይኖርም።
ብዙ ግዜ ህወሀትና ፍሎ ፍሎ ( floo floo ) ወፍ ይመሳሰሉብኛል። ይህቺ ወፍ ስትበር ወደ ኋላ ነው። የነበረችበትን ሥፍራ እየተመለከተች እንጂ የምትጓዝበትን ቦታ እያስተዋለች አይደለም። የህወሀትም ፖለቲካ እንዲሁ ነው፤ ዛሬን ሳይመለከት፣ ነገን ሳያገናዘብ፣ ትላንትን ብቻ እያሰታወሰ የሚበር – የሚጓዝ።
ፖለቲካ እንደ መርህ ያለውን ትውልድ ማህበራዊ ህይወት ማስተዳደሪያ እንጂ ያለፈን ትውልድ ቂም መበቀያ ወይንም ደግሞ የሚመጣው ትውልድ ህልውና ማስጠበቂያ መሳሪያ ሆኖ አገልግሎ አያውቅም። ይህ ሳይሆን ቀርቶ፡ የዛሬን ፖለቲካ (ስልጣን) ለትላንት ቁርሾ መካሻ፣ ለነገ ዋስትና ማስከበሪያ ለማድረግ ሲሞከር ግን – ህግና ስርዓትን ጥሶ ከመርህነት (አይዲኦሎጂ) ባሻገር በደል እየዘራ፣ ቂም እያበቀለ፣ በቀል እያጨደ የሚሄድ ከባድ ማሽነሪ (Heavy Machinery) ይሆናል። ደግሞም ትዝ ሲለኝ፥ ከላይ የጠቀስኳቸው አዛውንት “በፋሲካ የተሸጠች ባሪያ፡ ሁሌ ፋሲካ ይመስላታል” ይሉ ነበር። ጎንደርን እንደ የመን አስቦ፡ ዘሎ ገብቶ የፈለጉትን ይዞ መውጣት የማይደገም ህልም ሆኗል።
* Feature Image credited for Delasshadow