
By Admin
አንዴ ካመለጠህ አባረህ የማትይዘውን፥ ዙሪያውን በሚገባ ሳታጥር አታሯሩጠውም። ደግሞም፦ አካባቢህን ከሌባና ከተናጣቂ አውሬ አፅድተህ ሳታበቃ፥ የቤትህን አጥር ተቻኩለህ አታፈርስም። በቅንነትም ይሁን በይቅር-ባይነት ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ያደርጉት ግን ይህንን ነው።
ከኣውሮፓና አሜሪካ በጅምላ የተመመው የ-hamburger እና hotdog ድልብ ብቻ ሳይሆን፥ በሀገር ውስጥም አድብቶ የነበረው የ-ማርና ቅቤ ቅልብ ጅብ ለስልጣን ሲስገበገብ ይኽው ንፁሃንን መፍጀት እና ማፋጀት ጅምሯል። ጥልቅ ተሃድሶው ከቀን ጅብ ወደ ቅልብ ጅብ እያዘገመ ይመስላል። እስቲ … ይህንን ጅብ ለአሁኑ እዚሁ ላይ ልሰረውና ወደ ዛሬው ሃሳቤ ልመለስ።
ኣዲሱን የአዲስ አበባ ከንቲባ ሹመት ስስማ፥ ከኣንድ አመት በፊት ያዳመጥኩት የ-Bob Geldof ቃል ትዝ አለኝ። በሀገሯ Burma (Myanmar) ሙስሊሞች ለደረሰባቸው ሀይማኖታዊ መድሎና ጥቃት አፋጣኝ መፍትሔ ለመስጠት ከተሳናት መሪ – ከ Aung San Suu Kyi – እኩል ልቀበለው አይገባም ያለውን የአየርላንድ Freedom of Dublin የክብር ሽልማት ሲመልስ፥ አርቲስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ Bob Geldof እንዲህ ብሎ ነበር: “ We (the world) thought she was something but she is not. I feel like she made me a chump. ”
እኔም ዛሬ የተሸውድኩና የተሞኘሁ መስሎ እየተሰማኝ ነው። ህግና ሥርዓት ከመጣስም አልፈው በጠባብ ምህዋር የሚሽከረከርን “ምሁር” በሰፊዋ የኣዲስ አበባ ከተማ ላይ በማንገሳቸው፥ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እኔን ብቻ ሳይሆን ቀላል ቁጥር የሌለውን የኣዲስ አበባ ነዋሪም ጭምር የመከዳት ድባብ እንዲያጠላበት አድርገውታል። ይህን የክህደት ደመና በአፋጣኝ መግፈፍ ሳይችሉ ቀርተው ማካፋት እና መዝነብ ከጀመረ ደግሞ፥ ድንገተኛው ጎርፍ የሚጠርገው ህይወትና ንብረት ቀላል አይሆንም።
ሌላው ቢቀር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለምን አዲስ አበባን ከዘር ባሻገር ሀገርን ማየት በተሳነው ግለሰብ ስር ማስተዳደር እንደፈለጉ አልገባኝም። ሊገባኝም የሚችል መስሎ አይሰማኝም። ምክንያቱም፦ ይህ ድርጊት ትላንት መስቀል አደባባይ ላይ ለራሳቸው ለጠቅላይ ሚንስትሩ መቆም በወደቀ አስክሬን ላይ – በዘር መርዝ የተመረዘ አፍ ምራቁን እንዲተፋ፣ ለእርሳቸው መኖር በፈሰሰ የእህት ወንድሞቻችን ደም ላይ – በብሔርተኝነት የቆሸሸ ስብዕና ቆሞ እንዲሽና መፍቀድ፥ በየትኛውም መንገድ ህጋዊም ሆነ ግብረገባዊ ውሳኔ ሆኖ ሊቆጠር አይችልምና ነው።
ይህ ተቃውሞ ከሀገርና ከህዝብ ጥቅም ጋር እንጂ ከዘር ጋር ተያይዞ ሊመነዘር ወይንም ደግሞ ሊተረጎም አይገባውም። አዲስ-አበባዊው፦ ኢትዮዽያን እንደ ኢትዮዽያ፣ ህዝቧንም እንደ ኢትዮዽያዊ ዜጋ በእኩል አይን የሚመለከት ግለሰብ በከተማው ላይ ቀርቶ በቤቱ ጣሪያ ስርም ቢሾምበት የሚከፋው አይደለም። ከ-አራዳ ምስረታ ጀምሮ፥ ሸጋው ሸገሬ በፍቅርና በመተሳሰብ ያለውን ተካፍሎ አብሮ መኖርን የሚያውቅ ነውና። ለዛም ይመስለኛል፦ “ መገን የኣራዳ ልጅ አይፈራም ኪሳራ … ሺ ብሩን መንዘሮ ገባ ስንጋተራ ” የተባለለት።
እኔም ብሆን በዚህ ፅሁፍ ተቃውሞዬን ስገልፅ፥ ሀቅን እንጂ መንደርተኝነትን አስቀድሜ አይደለም። አለበለዚያማ፦ እንደ ክብር ዶክትሬቱ ሁሉ የክብር ምክር-ቤቱም ማዕረግ ተለምዶና እውን ሆኖ፥ ክቡር ዶክተር አቶ ለማ መገርሳ የኣማራ ክልል ምክር-ቤት የክብር አባል ሆነው ቢሾሙና፥ ምክር-ቤቱ በሚያደርገው ማንኛውም መደበኛም ሆነ ልዩ ጉባዔ ላይ ባሻቸውና በተመቻቸው ሰዓት ለደቂቃም ይሁን ለቀናት ብቅ ብለው መክረው፣ ተመክረውና፣ ተመካክረው ቢመለሱ የምደሰት እንጂ የምቃወም አልሆንም። እኚህ ሰው ዛሬ ባላቸው አስተሳሰብና ስብዕና፥ ከኦሮምያ ያለፈ ሀገር አቀፍ – ኢትዮዽያዊ ክብርና ማዕረግ ይገባቸዋልና።
ለኣዲስ አበባ ወጣቶች መዳፌ ላይ አስቀምጬ እፍፍፍ ባልኩዋት ትንሽ ግጥም ጽሁፌን ከማጠቃላሌ በፊት ግን፥ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የአደማመር ስሌቱን በሚገባ እንዲያስተውሉት ማሳሰብ እወዳለሁ። ሐምሌ 08 / 2010 ዓ.ም. በሚሊንየም አዳራሽ እንደተመለከትነው፦ ይህ የድምር arithmetic ባህር አሻግሮ ከምድረ አሜሪካን ገዳይ አስገዳዩንም እየሰበሰበ ጨምሮ የሚያሰላ ከሆነ፥ በአጭር ጊዜ ውጤቱ ጋሽቦ የድምሩ ፓለቲካ inflation ውስጥ መዘፈቁ አይቀሬ ይሆናል። ያኔ ደግሞ ኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን ፖለቲካውም በከባድ ኪሳራ ይመነዘራል።
ያ ጭራሮ
ከዚህም ከዚያም ተለቃቅሞ
አጀብብብ ብሎ …
ኣንዱ በኣንዱ ተሻሽጦ
መቆም መስሎት ተጠናክሮ
ይታሰራል ሆኖ ችቦ፤
እናም ደግሞ
ያ ችቦ
ተቸብችቦ
ምሰሶውን ዙሪያ ከቦ
ይቆምና ተነባብሮ
ድንገት …
ቡራኬው ሲያበቃ
የዋሁም ችቦ ሳይነቃ
ከድርድሩ ሳይፈርስ
እስራቱንም ሳይፈታ
በካህኑ ፊት
በኣንድ ክብሪት
ይለኮሳል
ነዶ ሊከስል
ይ ደ መ ራ ል!
አዎና …
ደመራ ነው ይ ደ መ ራ ል
ቢቃጠልስ ማን ያጠፋል?
የትስ ሄዶ የት ይከሳል?
በላዩ ላይ Uma ነግሷል!