Post

ዕድሜ እና ሴቶቻችን

ዕድሜ እና ሴቶቻችን

ዘበኝነት  ልቀጠር  ያሉት  ሽማግሌ  ናቸው  አሉ  ከቀጣሪ  አሰሪያቸው  ፊት  ለፊት  ቆመው  መልስ  እየሰጡ  ያሉት፦ “ዕድሜዎ  ስንት  ነው?” ቀጣሪው  ነበር። ያረጀውን  ነገር  ግን  በረጅም  ግራጫ  ካፖርት  የተሸፈነውን  የሽማግሌውን  ገላ  አንድ  ዙር  በዓይኑ  ሄዶበት። “ሃምሳ-አንድ  ነው ኸረ  እንዳውም  ገና  አልሞላም መሰለኝ ልጄ?” አሉ  ሸማግሌው። “የሥራ-ልምድ?” የቀጣሪው  ቀጣይ  ጥያቄ  ነበር፤ የሰድሳ-ኣምስት  ዓመት”  አሉ አባት  ሽማግሌ። ቀጣሪው  ድንጋጤ  ይሁን  ግርምት  ጭንቅላቱን  አቀርቅሮ  ከሚጽፍበት  ወረቀት ላይ  ቀና  ቢያሰደርገውም እሳቸው  ግን ሽምግልና  የወተት  ሰልባቦት  ያስመሰለውን  የፊት  ቆዳቸውን  ዘና  አድርገው  በግድ  ሊያፈታቱት ሞከሩ። ምናልባት  የጠየኳቸውን  በቅጡ አላጤኑት  ይሆናል  ብሎ  የሰማውን  የተጠራጠረው  ቀጣሪ  ቀድሞ  የጠየቀውን  የሥራ-ልምድ  ቢደግመውም፡ እንደ  ጥያቄው  ሁሉ  የሽማግሌውም  መልስ  ያው  እንጂ  ለውጥ  አልነበረውምየሰድሳ-ኣምስት  ዓመት  የስራ  ልምድ። በነገሩ  የተገረመው  ቀጣሪ  ዕድሜ  ሃምሳ-አንድ  የሥራ  ልምድ  ደግሞ  ሰድሳ-ኣምስት  የሆነበትን  እንቆቅልሽ  ቢጠይቅ  ሽማግሌው  የሰጡት  መልሶ  “ኦቨርታይ (overtime) እሰራለሁ  ልጄ  እኔ  አባትህ  ብርቱ  ነኝ  እንቅልፍ  አልወድም”  የሚል  ነበር።

እኔም  እንደው  እስቲ  ስለ  ዕድሜ  ትንሽ   ማለት  ከቻልኩ  ብዬ  እንጂ አነሳሴ  እንኳን  በቀጣሪ  እና  በተቀጣሪ  መካከል  ያለውን  እንካሰላንቲያ አልያም  በቀልድ  መልክ  የቀረበውን  ያረጀ  ጆክ (joke)  እንደ  ሞኝ  ለመድገም  አይደለም።

የዕድሜ  ጉዳይ  በተነሳ ቁጥር እንደ  ህጻናቶቹ  ሁሉ  የዕድሜም  እናት  የሆኑ  ይመስል  አብረው  እየተነሱ  የሚጣሉት  ሴት  እህቶቻችን  አንደሆኑ ሃሰት  አይባልም። “የወንድ ልጅ  ደሞዝ የሴት ልጅ  እድሜ  አይጠየቅም”  አይደል  እስከነተረቱ  የሚባለው። የደርጉ  ዘመን  ብሔራዊ  የውትድርና አገልግሎት ቆሌ  አሳጥቶ ወኔያችንን  ከገፈፈን  ወዲህ እኔም ወንድ ሁሉ  ሰለ  ዕድሜው  ሃቅ  ይናገራል  ብዪ  ባልዋሽም፡  ከዘጠናው  ሴት  መካከል የዕድሜዋን  ትክክለኛ  ቁጥር  ለመናገር  የምትደፍር  ኣንዲት  ሴት  ትገኛለች  ብዪ  በኣንዲቷ  ጣቴ  ከመፈርምይልቅ  ሁለት  እጄ  ቢሰየፍ እመርጣለሁ።  ለዚህም  ሚስቴ  ቆንጆ  ማስረጃዪ  ናትና  ዋስ  አያስጠራኝም።

የዛሬ  ሃያ-ሶስት  አመት  ገደማ እኔ  የሰላሳ-ሶስት  እርሷ  ደግሞ  የሰላሳ  ዓመት  ኮረዳ  እያለች  እንደ  አቅሜ  ደግሼ  እና  ሰረጌ  ያገባሁዋት  ውዷ ባለቤቴ ዕድሜዋን  በሶስት  እና  በኣምስት  ዓመት  እየመተረች  እና  እየጠረዘች  ስትከረክመው የከርሞውን  አላውቅም  እንጂ  ዘንድሮ  ሃያው ቤት  ገብታብኛለችና ነው። ጉዳዩ  ለሰሚው  ባይገርምም ለእኔ  ግን  እኩያዪ  የነበረችው  የትዳሬ  አጋር እኔን  በሃምሳው  የዕድሜ  ክልል  እንጋላኝ እሷ  ወደ  ሃያው  ድንበር  የሗልይሽ  መፈርጠጧ  ከማስደንገጥም  አልፎ  አስጨንቆኛል።

ለምን?”  ካላችሁኝም ይህን  የዕድሜ  የሗልዮሽ  ሶምሶማ  አይደለም  ቅልጥ  ያለ  ሩጫ  ስራዪ  ብላ  የተያያዘችው  ሚስቴ ጡረታ  ልወጣ  ሦስት እና  ኣራት  ዓመት  ሲቀረኝ አብረን  ያፈራናችውን  ሰባት  ልጆች  ከላዪ  ላይ  ከምራ  ቀስ  በቀስ  ስትንሸራተት  ጭራሽ  “ገና ሽል ነኝ”  ብላ  እናቷ መሃፀን  ጥልቅ!  ብትል  ለማን  ነው  አቤት  የሚባለው? ደግሞስ  ሚስቴ  እንደ  አያያዟ  ሰምሮላት  እናቷ  ሆድ  ብትመለስ፡ ይሄ  በረባ  ባልረባው ቀን ከሌት  የሚናቆረኝስ  ጎረቤት ዝም ብሎ ይቀመጣል ብላችሁ ነው? ያው  ሰበብ  ነው  የሚፈልጉት ሚስቱን  ገድሎ  ቆፍሮ  ቀብሯል – ብለው ተጩዋጩኸው  ያስይዙኛል  እንጂ። ይህስ  ባይሆን፡ “ዳዲዪ” ማሚዪ”  እያሉ  የሚጠሩን  ያ  ሁሉ  ማቲ  ልጅ  ከየት  መጣ  ሊባል  ነው? እኔ  ደግሞ ሰው እንጂ  ሸንኮራ-አገዳ  አይደለሁ ግንዱ  እየተቆረጠ  ተራብቶ  ነው  አይባል። ይገርማል። ግን  ጎብዝ እንደው  የስምንት  ዓመቷ  ህጻን  “ዕድሜዪ  ሰማንያ  ነው”  ብላለች  ተብሎ  ያለ  ዕድሜዋ  ላትቀጭ፣  ወይ  ደግሞ  ጉልበቷ  ደክሞና  ዓይኗ  ፈዞ  ሽመል  ጨብጣ  ስጥ  እየጠበቅች ከመንደሩ  ኣውራ  ዶሮ  ጋር  ግብግብ  ላትገጥም  አለበለዚያም  የስድሳ  ዓመቷ  አሮጊት  ዕድሜዋን  ስትጠየቅ  አፏን  አኮላትፋ  “ኣሽላ-ሾሽት  ነኝ” ሰላለች  ዲሞ ፔፕሲ  እና  እንኮይ-እንኮይ  አምሮባት  ላትጫወት ዕድሜን  እንዲህ  እንደ  በሶቢላ  እንጨት  እየሽመጠጡ  ማራቆቱና  ባዶ ማስቀረቱ  ምኑ  ላይ  ይሆን  ጥቅሙ? 

ነው ወይንስ  እግዜሩም ከፈጠራችው  የምድር  ነገስታቶች  ቀረጥን  ተምሮ፦ በመጨረሻው  ቀን  ከፍርድ  ባሻገር በፈጠርኳት  ምድር  ላይ በተመላለሰበት  ዓመት ልክ እንደ  ዕድሜው  ቁጥር  እየታየከእያንዳንዱ  ሰው  ግብር  እሰበስባለሁ”  አለ?  ደግሞስ  ቢል እግዜር  እግዜር  እንጂ ሰው  ሆኖ  ላይታለል  ዕድሜን  መቀነሱ አትዋሽ  ከሚለው  የኣስርቱ  ትዕዛዛት  ጋር  ተጋጭቶ  የገሃነሙን  እሳት  ይባስ  ያፍማል  እንጂ  ያዋጣል?

ባለፈው  ሰሞን እንደኔው  ሚስቱ  ዕድሜዋን  እንደ  ቋራው  ታጠቅ  ሹሩባ  ወደ  ሗላ  ቆንድላ  እና  ሸርባ ከጨቅላ  ልጁ  እኩል  ኒዶ (NIDO)  እና ሴሬላክ (CERELAC)  እየተሻማች ጡጦ  እየተናጠቀች  ምርር  ያደረገችው  ነው  መሰለኝ  አንዱ  የሃገሬ  አዝማሪድሮም  የሴት  ዕድሜ  ዘጠኝ ቅናሽ  አለው” ሲል  ሰማው እሰቲ  እውነት  ይሆን  እንዴ  ብዪ ከምሄድበት  ተመልሼ፣  ንጋፋዋን  ሚስቴን  አዋዝቼ  የዕድሜዋን  ቁጥር ብጠይቅ  የዘፋኙ  መላምት  ልበለው  ግኝት  ውሽት  ፈጽሞ  ከእውነት  የራቀ  ሃሰት  ሆኖ  አገኘሁት።

ጥያቄ  አታብዙና “እንዴት?” ብትሉኝ  ግን ሚስቴ  ከነገረችኝ  የዕድሜዋ  ቁጥር  ላይ  ዘፋኙ  አለው  ያለውን  ቅናሽ  አስልቼ  ዘጠኝ  ብደምርበት ሂሳቡ  እንኳን  ሊጠጋጋጭራሽ  ከበኩር  ልጃችን  ዕድሜ  በሁለት  አንሶ  የባሰ  አታምጣ  አስባለኝ። ቢያውቅበትማ  ኑሮ  ዘጠኝ  ሳይሆን  ሃያ-ዘጠኝ ቅናሽ  አለው  ቢል  ኖሮ  እንደው  ትንሽ  እንኳን ይጠጋጋ  ነበር። ከሃበሻ ሴት  የዓይን  ግልምጫJean Claude Van Damme እርግጫ  ይሻላልና፤ እንደው  መንገድ  ላይ  ስንተያይ  እንኳ  ቢራሩልኝይህ  የዕድሜ  ገመጣ  የኛዎቹ  ሴቶች  ብሔራዊ  የቤት  ጣጣ  ብቻ  ሳይሆን  አለምአቀፋዊ ገጽታ  እንዳለው  ልናዘዝ። በአንድ አጋጣሚ Oscar Wilde ስለዕድሜ  ተጠይቆ “You should never trust a woman who tells her age. A woman who would tell you that would tell you anything”  (ዕድሜዋን  የምትናገርን  ሴት  ማመን  የለብህም። ሴት  ልጅ  ዕድሜዋን  ሳትደብቅ የምትነገርህ  ከሆነየምትደብቀህ  ሌላ  ምንም  ምስጢር  አይኖራትም) ሲል የውጪዎቹም ሴቶች ዕድሜያቸውን  ባይዋሹም  ለመናገር  ግን እምብዛም  ፍቃደኛ  እንደማይሆኑ  መስክሯ። ግን  ግን  ዕድሜ  እንዲህ  የሚያስፈራው  ቀንድ  ነው  ጥርስ  ያለው?

በሉ  እስቲ  እኔም  እንደ  ባሏ  ጸጉር  ወደ  ሗላ  ስትሸሽ ስትሸሽ ዕድሜዋን  ከክርስትና ልጇ  ዕድሜ  አሳንሳ  የተደላደለችው፡  የያኔዋ  ውድ  ባለቤቴ አንጋፋዋ  ወይዘሮ  ተናኜ  የአሁኗ  ውድ  የልጅ  ልጄ  ቲኔጀሯ (teenager) ቲና  ተመልሳ  እናቷ  ሆድ  ሳትገባ፤  አምላክ  አዛውንት  እናቷን  በቶሎ ቦታ ፈልጎ፣ በእቅፉ  አሳርፎ፣  እኔንም  በእስተርጅና ያለ  ሚስት፣  ልጆቼንም  በመዳሪያቸው  ያለ  እናት  ከመቅረት  እንዲያተርፈን  ሱባኤ ከያዝኩበት  ሥፍራ  በጊዜ  ልሂድ።

ይህ  ጽሁፍ  የቆየ  ቢሆንም፣ ዛሬም  ቢሆን  ዕድሜ  እንደ  ቄጤማ  ይቀጠፋል  ልበል  ወይስ  ይታጨዳል? በተለይ  ኣውሮፓ። ስለ  ዕድሜ  አላወራምነገር  ግን ጊዜ  ካገኝን ወደፊት ስለ ኣውሮፖ እና ሴክሲ  ስሞቻችን ትንሽ እናወጋልን። እ ዶጮ– ዶልቼ (Dolce) ሲባሉ ጎበና‘ም ተጠጋግቶ ጋባና (Gabbana) የሆነበትን – (Dolce & Gabbana) ደብሪቱ– ዲቦራ (Deborah)፣ መኩሪያ– ማካርቲ (Maccarthy) ለማጠጋጋት የከበዳት ሀገሬ-ኩሪ  እንኳን  ሳትቀር  “who-minus-who”  ብላ  ከIndian Curry  ተበድራ  ኢትዮዽያን-ከሪ ሆና  ተሰይማልናለች። አቋም  እና  ፊታቸው የከባድ  ሚዛን  ቦክሰኟ  መስሎ  ለዓይን  ቢያስፈራም፤  ስማቸው  ግን  ለምላስ  ሴክሲ (tasty)  ሆኖ  ተክሰናል። ድምጻዊው  ቴዎድሮስ  ታደሰ  አጉል  ሰዓት  ላይ ዘፈነው  እንጂ ያ  የዱሮው ሳዱላዪ ነይ አልቦሽን  አርገሽ በትልፉ  ቀሚስ  አምረሽ  ተውበሽ”  ግጥም  ዛሬ  ላይ  ቢሆን  ኖሮ፦ “Sandra  ነይ  tattoo’ሽን  አድምቀሽ በthong  bikini  ደፍረሽ  ተራቁተሽ”  ተብሎ  ይዘፈን  ነበር።

Comments are closed.