Post

ዝቅ እንዳደረጉሽ … ዝቅ ይበሉ!

ዝቅ እንዳደረጉሽ … ዝቅ ይበሉ!

ወቅታዊ ዕውነታዎችን ለማንበብ ዓይኔ በሳይበሩ ዓለም ከድህረ-ገጽ ወደ ድህረ-ገጽ ሲሯሯጥ፡ ድንገት በኣንድ ምስል ተደናቅፎ ወደቀ፦ መንግስት ለሀዘን መግለጫ ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡ በሰቀላቸው ሶስት ባንዲራዎች። ዓይኔ’ን ከወደቀበት ትቶ፡ መንፈሴ – በታሪካችን ባንዲራችን እንዲህ ዝቅ ብሎ የተውለበለበበትን መሪር የሀዘን አጋጣሚም ለማስታወስ ወደኋላ ኮበለለ። ከንቱ ድካም ነበረ።

ሀሳቤ ከኋልዮሹ ጉዞ ሲመለስ፡ የዓይኔ እንቅፋት፣ የመገረሜን ምክንያት – ከላይ የምትመለከቱትን ፎቶ – በደንብ ማስተዋል ጀመርኩ። እናንተስ? አሰቃቀሉን ተመልክታችኋል? የእጥፋቱን ብዛት ታዘባችኋል? መስመሩ በዝቶ፣ አንዱ ባንዲራ ሰማንያ ቦታ ተሰባብሮ፣ ከአፍ እና ከአፍንጫ ጉድፍ ማፅጃ መሀረብ አንሶ፣ ተጠቅልሎ ስትመለከቱ፡ ሰቃ’ዮ ግለሰብ፡ ባንዲራውን ከሚስጢር ኪሱ አለበለዚያም ከገንዘብ ቦርሳው መዞ እንዳወጣው አልገመታችሁም?

ይገርማል፦ እንኳን የሀገር እና የህዝብ መለያ የሆነው ባንዲራ፡ የመንደር መሸታ ቤት አስተናጋጅ ዩኒፎርምም ክብር ኖሮት ይተኮሳል፣ ተስተካክሎ ይለበሳል። ባንዲራ እኮ የኣንድ ህዝብ መጠሪያ/መለያ ነው፤ ቃላታዊም ባይሆን ቀለማዊ ስም። ፎቶው አስገረመኝ እንጂ አላስቆጨኝም። ምክንያቱም፦ ትላንት “ጨርቅ” ነው ብለው ካረከሱት፡ ዛሬ ቢያጨማደዱት አይደለም ቢቦጫጭቁት ምን ያስቆጫል? ብቻ … ዝቅ ማለትዋ ቢያስከፋኝ … “ዝቅ እንዳደረጉሽ ዝቅ ይበሉ!” አልኩኝ፦

ዝቅ እንዳደረጉሽ ... ዝቅ ይበሉ!

ewb1

ለሰው አረም እርሻ
ሆነው ዘብ ውሻ
ነክሰው ከአስነከሱት
ያን ክቡር ሃበሻ

ewb2

የአዳም ሥሩን
የፍጥረት ግንዱን
ነቅለው፣ ቆርጠው … ካሰደዱት
አጠውልገው … ካከሰሉት

ewb4

ከምዕራቡ ሊዳሩ
ሊሴስኑ ከሰሜኑ
በከል፣ በማቅሽ ተሞሽረው
በለቅሶሽ ዳስ ከተኳሉ

ewb5

የይሁዳ መርገምት ላይፀዳ
ላይስተሰረይ የደም ዕዳ
የማታሽን ግንባር ነጥቀው
ከሠዉት እንደ በግ አስረው

ewb6

ከብዶ ቀንበሩ
የፈርዖን ግብሩ
ሩህ እንደ ጠል … ነፍስ እንደ ቅል
ሲንጠባጠብ … ሲንጠለጠል

ewb7

እንደ ባዳ፣ እንግዳ
ያ  ዘ-እምነገደ ባንዳ
አጥንት ሲቆጥር … ሲመዝን ስጋ
ደም-መላሽ ጠፍቶ … መሽቶ ከነጋ

የዚህ ግጥም አብዛኛው ስንኝ እና ሐረግ ለአንባቢው ፍቺ ያስቸግራል የሚል ዕምነት ባይኖረኝም፤ ለግንዛቤ ያህል ግን አንዱን ቃል መፍታት እወዳለሁ
ግንባር = ዕድል (የማታሽን ግንባር = ጧሪ፣ ደጋፊ)

ቃል / May 2015.

Comments are closed.