Post

የራስን ዕድል በራስ መወሰን ኣማራን እስከመግደል

የራስን ዕድል በራስ መወሰን ኣማራን እስከመግደል

By Admin

የሰው ልጅ የሆነው ኣማራ፥ ለአደን እንደተፈቀደ  እንስሳ (game animal) ያለ ከልካይ በቀስት ሲቀሰት፣ በካራ ሲታረድ አደባባይ ላይ ወጥተው ችግሩ ህገመንግስቱ ነውየሚሉን ሰዎች በጣም ያስገርሙኛል። እኔ እስከውማቀው ድረስ ህገመንግስቱ፦ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠልይላል እንጂ፥ የራስን ዕድል በራስ መወሰን ኣማራን እስከመግደል የሚል አንቀፅ አለው እንዴ? አጥንትአልባው ብአዴን ሰው ባስበላ፣ ኣራዊቱ ኦህዴድ ሰው በበላ ቁጥር  ህገመንግስቱ ላይ ማነጣጠር ምን የሚባል ፈሊጥ ነው? ተጠያቂነትን ከነፍሰገዳይ ሰብ ወደ ነፍሰአልባው መዝገብ መሳብ? እንደዛ ነው?

እርግጥ ነው ህገመንግስቱ ስህተት የለሽ ነው ብዬ አላምንም። ነገር ግን የት?” “እንዴት እና ለምን?” ብሎ ችግሩን ነቅሶ ከማውጣት ይልቅ፥ ለሠርግ ለፍቺው፣ ለውልደት ህልፈቱ ሁሉ ህገ-መንግስቱእያሉ መጮህ፤ ንዝህላል የHiAce ሹፌር አዲስአበባ ላይ ሲያሸከረክር ሰው ገጭቶ ነፍስ ቢያጠፋ፥ አሽከርካሪውን ይዞ የወንጀል ሐቁን ከመስጠት ይልቅ፥ ጃፓን ሀገር ያለው የToyota መኪና ፋብሪካ ይዘጋልን!ብሎ አደባባይ ሰልፍ እንደ መውጣት መስሎ ይሰማኛል።

የባሱት ደግሞ፦ በየሳምንቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሀን በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈው ወደ መቃብር ሲወርዱ እየተመለከቱ፤ ወገኔን ያለ ሰው አደባባይ ወጥቶ ሲቃወም ዝም በሉ … በህወሃት ጉድጓድ ውስጥ አትውደቁየሚሉት ስሜትየለሽ ሰሞነኞች ናቸው። እነዚህ ስግብግብ ተራማጅ-እባቦች …  የእነርሱ እግር ከጠላት ጉድጓድ ውስጥ እንዳይገባ፥ ስንት የአምላክን እስትንፋስ በአፍንጫው የተሸከመ ክቡር የሰው ፍጡር በመቃብር ኣፍ መዋጥ እንዳለበት አይገባኝም።

አንተም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ ከነዚህ ተራማጅእባቦች መካከል ኣንዱ ከሆንክ፥ እስቲ ልጠይቅህ፦ በአንተ ልጅ ወይንም በታናሽ እህትህ እና በሚገደሉት ህፃናት ነፍስ መካከል ያለው የዋጋ ልዩነት ምን ያህል ነው? ብትፈልግ በዕንቁ፣ ብትፈልግ በብር አስልተህ ንገረኝ። አምላክ ደምና ውሃ አዋህዶ፣ አጥንት እና ሥጋ አዋዶ የአንተን ልጅም ሆነ ታናሽ እህትህን ወይንም የተቀጠፉት ህፃናትን ሲፈጥር የፈጀበት ጊዜ እኩል ዘጠኝ ወር አይደለምን? ነው ወይንስ የአንተ አብራክ ለአምላክ ፍፁም ውድ ሆና፥ በእናቷ ማህፅን ጅማት አጥንቷን ሲያዋህደው ሁለት ዓመታት ነው የወሰደው?

በህዝባችን ላይ፥ በተለይም ደግሞ በኣማራው ብሔር ላይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ ሳይሆን፥ ወደኋላ ተመልሰን ለሦስት ድፍን ኣሥርት ዓመታት ለደረሰው ጭፍጨፋ ቀዳማዊ ተጠያቂው ብአዴን እንጂ አንድአንዶች እንደሚሉት ህገመንግስቱም የጠላት ጉድጓድም አይደሉም። ከላይ ከአቶ ደመቀ መኮንን ጀምሬ እስከ ታች ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ድረስ ስመለከት፥ ብአዴን የአህያና ፈረስ ጋጣ እንጂ የፖለቲካ ዓላማ ያለው ድርጅት ነው ብዬ ፈፅሞ አላምንም። አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ አቶ አበረ አዳሙ፣ አቶ አገኘው ተሻገር … ወዘተ የኦህዴድን ኣማራጠል ፖለቲካ እምቢኝ ብለው የህዝባቸውን መብት ማስከበር አይደለም፥ ፊታቸው ላይ የሚያርፈውንም ወፍራም ዝንብ ያለ ጠቅላይ ሚንስትሩ ፈቃድ ለማባረር ድፍረቱ የላቸውም።

የብአዴን ውክልና ለሆዱ ነው። እንደዚህ ኣሳማ ትርጓሜ፦ የሰው ገላ” … እሸት ነው። ለዛም ነበር ህወሃት በተኮሰችው ከባድ መሳሪያ ሙሉ ቤተሰብ አልቆ፥ በነጋታው አደባባይ ወጥተው የደረሰ ጉዳት የለም በቆሎ ነው የጠበሰውያሉን። የሰው ነፍስ ማሞ” … የፖለቲካ ጨዋታ  መታወቂያ። የማይመሳሰለውን ማመሳሰል የአእምሮ መስለል እንጂ የአስተሳሰብ መብሰል አይሆንም።

አጭር ፅሑፌን ሳጠቃልል፦ ትላንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ በእነ አቶ ታዬ ደንደአ የዘረኝነት ቅስቀሳ እየተሞረደ የኣማራው አንገት ለሚታረድበት ካራ ግንባር ቀደም ተጠያቂው ብአዴን ነው። አለበለዚያማ ጠቅላይ ሚንስትሩም ሆኑ ኦህዴድ  ምን አጠፉ? ኣማራውን የሚያውቁት’ኮ በብአዴን እና በእነ እንትና ልክ ነው።

ከነበሩን፣ ካሉንና ወደፊትም ከሚኖሩን የሀገር መሪዎች መካከል በጀግንነታቸው ወደር አይኖራቸውም ብዬ የማምነው ንጉስ አፄ ቴዎድሮስን ነው። ንጉሱ፦ ለዝና እና ክብራቸው እምብዛም የማትጨነቅ ኣንዲት ልጅቢጤ የትዳር አጋር ነበረቻቸው ይባላል። እናም ከዕለታት አንድ ቀን መኳንቶቻቸውን ሰብስበው ግብር ሲያበሉ፥ ይህቺው የትዳር አጋር፦ ወንድ ለሚያሸኑት፣ እየሩሳሌምን ለሚያሸብሩት ንጉስ ያልተገባ ክብር ትሰጣለች። ይህን የተመለከተ የጦር አበጋዛቸው ገብርዬ በንዴት ፍም ፊቱ ግሎ ቢመለከቱ፥ ንጉሱ “ተዋት ገብርዬ … እሷኮ እኔን እንደ እንናተ ጦር ሜዳ ላይ ሱሪዬን አጥልቄ ሳይሆን ሱሪዬን አውልቄ ነው የምታውቀኝአሉት ይባላል። እስቲ እናንተው ፍረዱ፦ ጠቅላይ ሚንስትሩም ሆኑ አቶ ታዬ ደንደአ ኣማራውን ቢንቁ ፣ በዕልቂቱ ቢሳለቁ በነሱ ይፈረዳል?

Comments are closed.