Post

የሳምንቱ ስልኬ V

የሳምንቱ ስልኬ V

By Admin

Hello!

Hi! ምነው ጠፋህ?

Eduardo ዱሮ ጠፍቶ ነበር። Chung Lee’ን ባለፈው ለስድስት ወር  ማን አየው? ማን ሰማው?  Aphrodite እራሷ ወደ ሀገሯ Greece ከደወለች ቀናቶችን አስቆጥራለች

ምንድነው የምታወራው … ማነው Eduardo? ማናት Aphrodite?

ግራ ገባህ አይደል? ይሔ logic በትክክል የሚገባቸው፦ ሰለ ኢትዮጵያ ረሃብ ሲጠየቁ ሰለ ካሊፎርኒያ ድርቅ፣ ስለ ሀገራዊው ህዝባዊ ዓመፅ ሲመልሱ ስለ ቱርክ ብጥብጥ የሚዘባርቁት – ሀገር በኩረጃ የሚያስተዳድሩት የህወሀት መሪዎች ብቻ ናቸው

የሚያስተዳድሩት? የሚያወዳድሩት ማለት ፈልገህ ነው?

ታርሜያለሁ!  የአስተዳደር እና የዕድገት ህግ (principle) ካለው ማህበራዊ ዕውነታ ጋር እያስታረክ፣ እንደ ቦታና ወቅቱ እየሞረድክ Adapt አድርገህ የምትተገብረው መርህ እንጂ፥ እንደ አንድዬ ትዕዛዝ ነጥብ እንኳን ሳትሰርዝ እንደወረደ Adopt የምታደርገው ዶግማ አይደለም። South Korea ታራምድ የነበረውን የኢኮኖሚ ዕድገት ፖሊሲ የቀዳችው ከ”ታላቋ” ብሪታንያ ቢሆንም፥ ከማህበረሰቡ ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ተጨባጭ ዕውነታ ጋር ማጣጣም ስለቻለች – እንግሊዝ በተመሳሳይ ፖሊሲ 100 ዓመታት የፈጀባትን የኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ በሁለት አስርት አመታት ውስጥ ብቻ ለማጠናቀቅ በቅታለች 

ይኼን ስታነብ ነበር የጠፋኸው?

ሎል … No እዛው ሜዳው ላይ፡  ከፈረሱ አፍ ነው የሰማሁት

እና ምንድነው እንዲህ ያጠፋህ?

ምን መልካም ነገር ሰምተን ወይንም አይተን ልደውልልህ? ከጫፍ ጫፍ የደም ጎርፍ ነው የሚፈሰው

እና ይኼ ምን አዲስ ነገር አለው? ስልጣን ላይ ያሉት’ኮ ትላንትም የነበሩት የደም ዋናተኞች ናቸው። ነው ወይንስ “ግንቦት 7  እራት ጋብዞ – በአንድ ጀንበር አወፍሮ ቀየረው እንጂ እኛ ስንልከው ሸንቃጣ ነው” ያሉትን ዋናተኛ Rio ላይ ተመልክተህ፦ ሰዎቹ በደም ሳይሆን በውሃ መዋኘት ጀመሩ ብለህ አስበህ ነበር?

በተለይ ደግሞ የደብረዘይት ዕልቂት በጣም ያሳዝናል። የሞቱትን አምላክ ነፍስ ይማር! ለቤተሰቦቻቸውም ጽናቱን ይስጣቸው! 

አሜን! መንግስታችንም “ከዕቅድ በታች” ሰለገደለ፥ ለሶስት ቀን የሀዘን አዋጅ አውጆ አምርሮ አልቅሷል

ሃሎ

ሃሎ 

ሃሎ

አቤት? አይሰማኽም እንዴ?

ምንድነው? የማን ውሻ ነው ከጀርባህ የሚጮኸው? ለምን ሥጋ ነገር … የሚዋጥ ምናምን ወርውረህለት ዝም አታሰኘውም? … አትሰማኝም

ወይ የሚዋጥ … ዘንድሮ ወሾቹ የሚወጡት ሥጋ አይደለም ጌቶቹም የሚግጡት አጥንት እየጠፋ ነው። ቆይ ድምጹን ልቀንሰው፥ ሳምሶን ማሞ ነው የሚያወራው።  ግብጽና ሻቢያ ሲመጡ አልጋዬ ላይ ተኝቼ አልጠብቅም እያለ ነው። አልሰማኸውም መሰለኝ

ኧረ እኔስ ሰምቼዋለሁ፤ እሱ ነው እንጂ ወንድሞቻችንን ያልሰማቸው። ባዶ እጃቸውን አጣምረው ሲጮሁ እያያቸው “የጥፋት ሀይሎች” ብሎ የጦር መሳሪያ ያሰታጠቃቸው 

በደንብ ሰምተኸዋል ማለት ነው  

አሁን ብቻ ሳይሆን ያኔም ዱሮ እንደዛሬው  “የአፄ ዮሐንስ ልጅ” ሳይሆን ከደሃው ጉሮሮ ላይ ተነጥቆ፡ የአንበሳው ድርሻ ይገባኛል ብሎ በቴሌቶን ሁከት ሲያስነሳም በደንብ አዳምጬዋለሁ። ዛሬ በየትኛው ድንበር ይህን የሀገርና የወገን ፍቅር በኮንትሮባንድ እንዳስገባው አላወኩም እንጂ

ዛሬም’ኮ – ኢትዮዽያን እኔና እኔ እንጂ ግብጽና ሻቢያ አይብሉዋት – እያለ መሰለኝ ያለው

ባለፈው ሰሞን የአንድ ግለሰብ የድካም ውጤት የሆነን Yellow Pages የራሱ ስራና ህትመት አድርጎ አሰራጭቷል ተብሎ በፕላጂያሪዝም  (plagiarism) ሲካሰስ አንብቤ ነበር፥ ዛሬ የፍርድ ቤት ቀጠሮ የለውም ማለት ነው – “በጥፋት ሃይሎች” እና “በአጥፊ ሰለባዎች” መካከል ያለው ልዩነት በቅጡ እንኳን ሳይገባው ግብፅን ለመመከት Mic እንደ MIG የታጠቀው?

ምን አውቅልሀለው? ጠበቃው ነኝ ወይስ ጉዳዩን የያዝኩት ዳኛ ስለ ፍድር ቤት ውሎው እኔን የምትጠይቀኝ? ደግሞስ ይህ በራሱ የክሱ መከላከያ፣ የይግባኝ ሐተታ መሆኑ ጠፍቶህ ነው?

እንደሱ በል። በጣም ደስ ያለኝ ግን  “አሁን ለምሳሌ እኔ ከመንግስት 1 ካሬ ሜትር አልወሰድኩም” ያላት ኑዛዜ ናት። እነ ዘበናይ አዶናይ “mood አላት” ሲሏት፤  እነ አቶ አዱኛ ደግሞ “አልበላሽምን ምን አመጣው?” ይላሉ፦ ጅብ – “ነይ ከዛፉ ላይ ውረጂና እንጫወት፤ አልበላሽም” ያላትን ጦጣ አስታውሰው። “አልጋዬ ላይ ተኝቼ አልጠብቅም” አለ?!  ሳምሶን ማሞን ሳስበው ቅርስ እንጂ ቅኔ ለመዝረፍ ግድም ያለው አይመስለኝም። አለበለዚያ ግን ዛሬ እሱ ተኝቶ ግብፅን የሚጠብቅበት አልጋ ትላንት የወጣቶቹ ጥላ የነበረ ዋርካ ነው። ሚሊዮኖች ከቅዬያቸው እየተፈናቀሉ የቀኑን ሃሩር የሚያሳልፉባት የዛፍ ጥላ እንኳን ተነፍገው ጠውልገው ሲጮኹ፥ እርሱ የሌት ብርዱን፣ የማለዳ ቁሩን ተጋድሞ የሚያሳልፍበት- አልፎም ግብፅን ተኝቶ የሚጠብቅበት አልጋ በማግኘቱ ምንኛ እንደታደለ ማን በነገረው። … ሃሎ

ሃሎ … አቤት

ዝም ስትል’ኮ አዲሱን አዋጅ ፈርተህ ስልኩን አስቀምጠህ የተኛህ መሰለኝ

የቱን አዋጅ ነው የምፈራው?

አዲሱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነዋ! አልሰማሁም ለማለት ነው?

ሰምቻለሁ … አልገባኝም እንጂ

ምኑ ነው ያልገባህ?

በቀን ኣንድ ጊዜ እንኳ የማይበላን ህብረተሰብ “ከአሁን ቦሗላ ለስድስት ወር በቀን ኣራት ጊዜ አትበላም!” ብለህ ነጋሪት ብትመታበት ምን ይገባዋል? እንደዛ ቁጠረው። ለነገሩ አዋጁ የታወጀብንን ብቻ ሳይሆን ያወጁብንንም የገባቸው አልመሰለኝም

እንዴት?

ከትላንት ወዲያ ማታ መከላከያ ሚኒስትሩ የአዋጁን ዝርዝር አንብበው፣ የሚወሰደውንም “ጠንካራ እርምጃ” በጥብቅ አብራርተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፥ “ከመንገድ ግራና ቀኝ 25 ኪሎሜትር” በሚለው ህግ ቪላቸው ቀዩ ክልል (Red Zone) ውስጥ ወድቆ ጠበቃቸው። አንድ ኡዚ የታጠቀ አጋዚ፦ “ከፕሮፌሰሩ የይለፍ ወረቀት ይዛችሁ ካልመጣችሁ በስተቀር ሰዓት እላፊ ነው አታልፉም!” ይላል። ኧረ ባክህ አቶ ስራጅ ፉርጌሳ ናችው ቢባል – “ስራ ላይ ነኝ! ናይ ፉገራ!” ብሎ ማምረሩን ለማሳየት አንድ ሁለቴ ወደ ሰማይ ሲተኩስ፡ መከላከያ ሚኒስትሩ ስምጥ ይግቡ ስልጤ ሳይታወቅ በሰከንድ ተሰወሩ። በሹፌር፣ በአጃቢያቸው በአካባቢው ተፈልገው ስላልተገኙ “ሀገር ከዱ” ተብለው ሲወነጀሉ፥ አጅሬ ቢሮ ጠረፔዛቸው ላይ ዝርዝር አዋጁን ተንተረሰው እንደተኙ ማለዳ በቁጥጥር ስር ዋሉ … ብለው አዲሰ-አበባውያን ያወጋሉ

ማናቸው ደግሞ የይለፍ ፈቃድ ሰጪ ፕሮፌሰሩ?  

አሁን አንተ ፕሮፌሰሩ ጠፉህ? ለነገሩ አንተን ምን አድርገውህ ታወቃቸዋለህ – የጣሉት እኔን! 

ካልተሳሳትኩ ሰለ ኤታማዦር ሹም ሳሞራ የኑስ መሰለኝ የምታወራው

ሌላ በዚህ 25 አመት የትኛው ምሁር  ሀገር ሲመራ፣ የትኛው ፕሮፌሰር ትዕዛዝ ሲሰጥ አየህ?

ምን አድርገው … የት ነው ደግሞ የጣሉህ?

ባለፈው አንድ የውጭ ድርጅት በሴኩዩሪቲ (security) ሙያ ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ አውጥቶ፦ “የውትድርና አገልግሎት ልምድ ያለው ቢሆን ይመረጣል” ይላል።  ዘንድሮ መቼም ፎርጅድ ልምድም ግድም ነው አልኩና 2ሺህ ብሬን ከፍዬ “ሻለቃ” የሚል ዶክመንት አሰርቼ ገባሁ። የፅሑፉን ፈተና አልፈን ቃለ-መጠይቁ ላይ ስንደርስ “ከፍተኛው የጦር መኮንኖች ማዕረግ (ሹመት) ምንድነው?” ብለው ጠይቁ፥ እኔም “በቃ ተቀጠርኩ” ብዬ ተሽቀዳድሜ “ፕሮፌሰር” አልኩኝ … በሳቅ አሳፍረው፣ በሰርቪስ አሳፍ’ረው፣ እስከ ሰፈር ሸኙኝ

ታዲያ “አቤት! የሰሚ ያለህ!” አትልም ነበር ለፕሮፌሰሩ?

“አቤት!” ብዬ  ልበለት? ሰርጐ የገባ የግብፅ ሻለቃ ተብዬ የአኬልዳማ ሰለባ ልሁን? ፎርጅድ ለእነሱ እንጂ ለእኛ … ዋናውም … 

አላገለገለንም አትለኝም። አይዞን … ለውጥ በደጅ ነው

የትኛው ለውጥ? የህወሀት?

ህወሃትማ መለወጥ፣ መታደስ እንደማትችል እራሷም አምና፥ ተቃዋሚውን በአዋጅ፣ በልምምጥ ለመለወጥ ስትራወጥ እያየሀት አይደል? ደፍራ እንኳን እራሷን ለመለወጥ ኣንድ እርምጃ ብትራመድ ያበቃላታል። የህወሃት ብልሹነት ከአንድ ክር የተሰራ ዳንቴል ነው። ልንቀሰው፣ ልተርትረው ብለህ አንዱን ጫፍ ለመምዘዝ ብትሞክር፥ ከላይም ጀመርከው ከታች አጠቃላይ ኪሮሹ ሳይበተን ማቆሚያ የለውም። የአስተዳደር ብልሹነት (administrative corruption) ባህሪ እንደ ኩፍኝ ነው። በጮርቃነቱ ተገልጦ ካላከምከው በስተቀር፥ ዘግይቶ፣ ስር-ሰዶ ሲከሰት ገዳይ ነው፤ እራሱን ይበላል። ህወሃት ከአሁን ቦሃላ ለለውጥ የምትወስደው የትኛውም እርምጃ እራሷን ይውጣታል። እኔ “ለውጥ” ያልኩህ አጠቃላይ የስርዓት ለውጥን ነው

እሱማ መች ይቀራል፤ መውደቁ ላይቀር ይንገዳገዳል ነው ነገሩ

አትጠራጠር! በቅርብ የጊዜ ገደብ ህወሀት መሄዷ እርግጥ ነው። በዚህም በዚያም “የነፃነት ቻርተር” “የአስተዳደር chapter” እየተባለ ሩጫ የበዛው ለምን ይመስልሀል? 

አንዱ ሲናገር ሌላው ተከትሎ መብረር – ፉክክር ስለምንወድ ይመስለኛል፤ መቼም እኛ ስንፈጠር መፎካከር እንጂ መመካከር አልታደልንም

ምናልባት አዎ፥ በአንድ ወገን ያለው አዝማሚያ ያ ይመስላል፦ “አልበለጥም!” አይነት የእቃ እቃ ጨዋታ። ለእኔ ግን ከዛም የዘለለ ትዕይንት ነው። ያኔ … አንድ ዕቅድ ለመተግበር ስናስብ ገንዘብ ለማስለቀቅ ለ-Donor Agency የምናስገባው project proposal ትዝ ይልሃል?

ይለኛል … እና? 

መንግስት ብቻ ሳይሆን ካኔቴራም ስንቀይር ምዕራባውያንን አስፈቅደን እንደሆነም ታውቃለህ። አሁንም በህወሃት ተስፋ የቆረጡት ሀያላን መንግስታት “post TPLF era blueprint አምጡልን” ብለው ያዘዙ ይመስለኛል። ከረቂቁ በመነሳት ትርፍ ኪሳራቸውን መዝነው፣ ጥቅም ጉዳታቸውን ተንትነው፣ ቀስ ብለው … ሳይበርዳት ሳይሞቃት ህወሃትን በ-room temperature ሊያተኗት።

እንደው ይኼ እንኳን በቅርብ ባይሳካ … የሰይጣን ጆሮ አይስማውና … ከሰሞኑ ህወሀት በአሳዳሪዎቿ አስገዳጅነት “ለሰላምና ዕርቅ” ድርድር መቀመጧ የማይቀር ይመስላል። ይሄም ያም – ከቀበሮው ጉድጓድም በለው ከተቀበረበት ጐሬ – አንገቱን ብቻ ብቅ እያደረገ “የዚህ ትግል መሪየዛ ዓመፅ አሽከርካሪ እኔ ነኝ” ብሎ በሀገር ውስጥ ያለውን ትግል የመካፈል ጩኸት ሰም-ና-ወርቅ፦ “እኛም እለን! ጉልበታም ነን! በዕርቅና ሰላሙ ኮንፍረንስ እንዳትረሱን” ለማለት ይመስለኛል። ፖለቲካው ለእኔ የሚሸተኝ እንደዛ ነው

ምዕራባውያኑ ፕሮጀክት ፕሮፖዛሉን አንብበው ሳይጨርሱ፣ ለዕርቅና ሰላሙም አዳራሽ ሳይመርጡ ህወሀትን እኛው እዚሁ ቀድመን እንገላግላታለን። ለእሷም ቢሆን ከማታወቀው ICC የምታውቀው “ማዕከላዊ” ይሻላታል

እንተማመንባችሗለን። ለዛም ነው’ኮ የ2015 / 2016 የህብርታችን ሀገራዊ ባለ ክብር ያደረግናችሁ

ብትዘገዩም አዎ

መዘግየታችን ምክንያት ነበረው። በወቅቱ እስረኞችን በእሳትና ጥይት አጥተን ያዘንበት ወቅት ሰለነበር “ሦስት አመት ሞላን!” ብለን ልንጨፍር አልፈቀድንም። ከዛም “አሁን” ብለን ገላጭ ቪዲዮአችንን ልናሰናዳ ስንነሳ የደብረዘይት እልቂት ተከተለ። ለዚያ ነበረ …  

Anyways … ብትዘገዩም አጠቃላይ የአማራና የኦሮሞ ህብረት ምርጫችሁን ወድጄዋለሁ

ላስተካክልህ፦ በእርግጥ አነሳሳችን አጠቃላይ (በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ) ያለውን ህብረት ለማክበር ቢሆንም፥ ከብዙ ውይይት ቦሃላ ግን – “የነፃነት እንጂ የነውጠኝነት ትግል አይደለም!” ብልን ያመንበትን በሀገር ቤት ያለውን የአማራና የኦሮሞ ወንድሞቻችንን ተጋድሎ ብቻ በጋራ ለማክበር ወሰንን። የውጪውን አልጨመርንም፤  አሁንም ቢሆን ፍፁማዊ ነው ብለን ልንዘምርለት ገና አልደፈርንም   

ምክንያት?

ምክንያቱማ ብዙ ነው። በአጭር ሐረግ አስቀምጥልኝ ካልከኝ ግን ፀበኛችን እንጂ ፀባያችን አንድ አላደረገንም። የውጪውን አንድነት የቱንም ያህል ብንናፈቀው፡ ስንክ-ሳሩ እየታየን አይናቸንን ጨፍነን – አጉል “አንድነት አፍቃሪዎች” ለመምሰል መጨፍር ፍላጐታችን አልነበረም። ስለዚህ በሀሰት የሙገሳን በርኖስ ከመልበስ፥ በሀቅ የመፈረጅን ማቅ ማጥለቅን መረጥን

የምን ማቅ ነው የምታወራው?

ድብብቆሽ የህፃናቶች እንጂ የፖለቲከኞች ጨዋታ አይልደለም። የውሸትና የማስመስል ፖለቲካ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ፍቅርም ሆነ ፀባችን ይጥራ – አተላ አይኑረው ብለህ ስትናገር “ትምክተኛ” “ጠባብ” ነህ ይልሀል። እርሱ ጥበበኛ፣ ሰፊ ሆኖ- የማይገባህን የስም ጥለት ጥሎ፣ ማቅ ሸምኖ ያለብስሀል። ይባስ ብሎም አንዳንዴ ወደዚያኛው ክልል ይገፋሀል

ማንን ነው “እርሱ” የምትለው? ይኼ የፀብ አተካራ እንደ አዝመራ ሲዘራ የሚውለውን ዘመምተኛ ነው?

ደርሶብካል መሰለኝ … ቶሎ ባነንክ

ቢደረስብኝስ? “እርሱ” አይደለም “እነርሱም” ገፍተው አያነቃንቁኝም። ታውቀኛለህ … በዚህኛው ጎራ ስቆም በመልሕቅ አንጂ በመክሊት አይደለም

ትገርማለህ፤  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጆብህም ወኔያም ነገር ነህ

ሃሃሃ … ይልቅስ እኔም እንደ እናንተ እዚህ ባለው የህዝቦች አንድነት – በተለይም በአማራና በኦሮሞ ወጣቶች የትግል አጋርንት ላይ ምንም እንከን ባይታየኝም፥ ጐረቤቶችህ ለሆኑት መሪ እና አክቲቪስቶች ግን መልዕክት አለኝ … ካደረስክልኝ

ምን ልበልልህ?

የግዴታ ጅምራችሁ የውዴታ ፍፃሜ ይኑረው!

ግዕዙን ግረዘው

Oh! ለካ አንተ አማርኛ ትናገራለህ እንጂ አትሰማም

ሎል

ዛሬ ሁላችንም በአንድ መስመር የመግባታችን ግልፅ ምስጢር TPLF ነው። ክፉ እረኛ በጎቹን እየገረፈ በአንድ ስፍራ እንደሚሰበስብ፡ እኛም ከህወሃት የዘረኝነት ዱላ የተነሳ በአንድ ጉሮኖ ውስጥ ገብተናል። አክቲቪስቶችና የፖለቲካ መሪዎች ዞር ስትሉ ከጀርባችሁ እንደሊባኖስ ዛፍ በዝቶና ለምልሞ የምታዩት ጄሌ ሁሉ መልክ – አመለካከታችሁን ወዶ እንደተከተላችሁ አድርጎ በማሰብ ለማበጥ መሞከር ትልቅ ስህተት ነው። ይልቅስ፦ ይህ ክፉ እረኛ በአንድ ላይ የሰበሰበላችሁን መንጋ በጭምትነትና በማስተዋል እንዴት በጋራ አቻችሎ ማሳደር እንዳለባችሁ ከዛሬው ማሰብና መማር ይጠቅማችኋል።  

አለበለዚያ ግን፦ የዛሬው የሰው ጫካ ነገ የሰሀራ በረሃ ነው። ክፉው እረኛ ከመስኩ ሲወገድ መንጋው በመንደር፣ በሀይማኖት፣ በቋንቋ፣ ወዘተ ከዚህም ከዚያም የመጣው ተመልሶ በየጨፌው መበታተኑ የማይቀር ነው። እንደርችት አንድ ሆኖ ወደ ሰማይ ተተኩሶ … አንድ-ሺህ ቦታ ተፈነካክቶ አየር ላይ መቅረት ዕጣ ፈንታችን ይሆናል

በል ደህና ሰንብት

ምነው ቸኮልክ? ሰዓት እላፊው እናንተንም ይመለከታል እንዴ? ተደናበርክ 

መልዕክትህን ሳይበርድ ሳይቀዘቅዝ በትኩሱ ላደርስልህ ነው እንጂ። እዋይ አለ ወየንቲ ንዋይ! … ደግሞ እኔ  ለምንድነው የምደናበረው? አዋጁ ህዝብን አይጐዳም ህወሃትንም አይጠቅምም። ይልቅ ለግላዊ ቂም መወጣጫና ለግለኝነት ጥቅም ማስከበሪያ አመቺ መድረክ (environment) ሰለሚፈጥር በዚህ አዋጅ ተጠቃሚ የሚሆኑት በየመንደሩ ያሉት ዘረኞች በተለይም እንደ አዲስ-አበባ ባሉ ከተማዎች የሚኖሩ የስርዓቱ ደጋፊዎች ብቻ ናቸው። አጋጣሚውን ተጠቅመው ተራው ህዝብ ላይ የሚሰነዝሩት ወከባና ጥቃት፥ ስርዓቱን በህዝብ ዘንድ ይበልጥ እንዲጠላ ከማድረግ ወጪ ሀገርን በማረጋጋት ረገድ የሚጫወተው ምንም ሚና አይኖርም። ሰዓት-እላፊ አውጆ፣ ኬላ ገንብቶ እንቅስቃሴን በመግታት የህዝብን ቁጣ እቀንሳለሁ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው። ማንኛውንም ሀይል (energy) ከማስተንፈስ ይልቅ ማፈን የሀይሉን መጠን (power)  በእጥፍ እንደሚያባዛው ፊዚክስም (physics) ቢሆን የ-nuclear/atomic ቲዎሪን ዋቢ አድርጐ ያስረዳል

ትንሽ ላስለፈልፍህ ብዬ ነው ባክህ፥  ስለ Angela Merkel ምርጫችሁ ንገረኝና መሔድ ትችላለህ

የእርሷ ምርጫ ሰፊ ታሪክ አለው። በአጭሩ ግን Chancellor Merkel የፖለቲካን፣ የኢኮኖሚና የማህበረሰብን ህግጋት አንድም ሦስትምነት (trinity) በሚገባ የተረዳች መሪ ነች። ይህን መሰል አስተዳደራዊ ፍልስፍና (approach) መጠቀሟ ደግሞ – “ታላቋ” ብሪታንያን ጨምሮ መላው አውሮፓ ከኢኮኖሚው ሴክተር በተነሳ ማዕበል ተመቶ ፖለቲካውም፣ ማህበራዊ እሴቱም በአንድነት አብሮ ሲሰምጥ፡ የአንጀላ ጀርመን ግን ማዕበሉን በብቃት ከመመከትም ባሻገር ለመላው አውሮፓ a rescue lifeboat ሆኖ እንዲያገለግል አድርጓታል።  

ከዚህም ባሻገር Chancellor Angela Merkel ለመካከለኛው ምስራቅ ማህበራዊ ቀውስ በጐ ምላሽ በመስጠት አጋጣሚውን የአዶልፍ ሂትለርን ፖለቲካዊ እድፍ ለማደብዘዝ ተጠቅማበታለች። ይህ በራሱ በእኛ ሚዛን ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ስብዓዊም መሪ ያደርጋታል። ለዛ ነው የዚህ ዓመት የህብረታችን አለማቀፋዊ ባለክብር ያደረግናት። የግሌን አስተያየት ከጠየከኝ ደግሞ፡ አንጀላም ልክ እንደ እኔ – LIBERTY is the empirical formula of LIFE የሚል አመለካከት ያላት ይመስለኛል። … በል አሁን ደህና ሁን

Ok … ደግሞ ተመልሰህ እንዳትጠፋ

አልጠፋም፤ ባለፈውም እኮ አልጠፋሁም – ደወዬልህ ነበር። ሞባይልህ ይጠራል ይጠራል … ወይ አንተ ወይ ከአቶ ጌታቸው አሰፋ ቢሮ አንዱ ታነሱታላችሁ ብዬ ብጠብቅ ብጠብቅ ሳይነሳ ሲቀር ሰልችቶኝ ዘጋሁት

የቤት ስልክ ላይ ደውል፤ ሞባይል አሁን የእጅ ቦምብ ሆኗል። እሱን ይዞ መገኘት ያስከስሳል – ያሳስራል!

ሃሃሃ … ዱሮ “እባብን ያየ … በልጥ ይደነግጣል” ነበር የሚባለው፥ ዘንድሮ “በቦምብ የቆሰለ በ-Apple ይሸበራል” ሆነ?

ደግንቱ የእኔ ስልክ iPhone አይደለም፥ የ-Apple logo apple-logo የለውም

ተርፈሀል … በል መልካም ሰንብት

መልካም ሰንብት

Comments are closed.