Post

የሳምንቱ ስልኬ X

የሳምንቱ ስልኬ X

By Admin

   ሄሎ

  ጤና ይስጥልኝ፤ ምነው ደጅ አስጠናኸኝ? ኣማሮች የውጭ ስልክ ለማንሳትም ከብልፅግና ፓርቲ ፈቃድ ትጠይቃላችሁ እንዴ? እኔ እንኳን የሰማሁት ወደ ስልጣን ለመምጣት ብቻ ነበር

   Sorry, ሥራ ይዤ ነበር … ላዛ ነው ቶሎ ያላነሳሁት

  ምን ዓይነት ሥራ ነው ስልክ የማያስነሳ? ተሰብስባችሁ ሰንደቅዓላማ እየሰቀላችሁ ነበር እንዴ?

   ሰውየው፥ ዘንድሮ ህዝብ ተሰብስቦ የሚሰቀለው ሰንደቅዓላማ ሳይሆን የሰው ገላ እንደሆነ አልሰማኽም? ደግሞምኮ አዲስ አበባ ገና የራሱዋን ሰንደቅም አላፀደቅችም

  Ok … በል ሰንደቁን ስታፀድቁ ንገረኝ፤ ቢያንስ የክልላዊውን መዝሙር ስንኝ እኔ እደርስላችኋለሁ

   ያለውስ መዝሙር? አልተስማማህም?

  አለመስማማት ብቻ ሳይሆን፤ ኣንደኛ፦ ግጥሙንም አታውቀውም! እንዲሁ ብቻ ቀኝ እጅህን ግራ ደረትህ ላይ ለጥፈህ መስማት በተሳናቸው‘ mood ታልፈዋለህ እንጂ፥ ኣንድ ቀንም በትክክል ስትዘምረው አይቼህ አላውቅም። ሁለተኛ፦ የክልል ባንዲራ በብሔራዊ መዝሙር መስቀል ይደብራል

   እና? አዲስ ግጥምና ዜማ ደርሰን እሱን እናጥና?

  ምን ይላችኋል? ከሸከካችሁም ይበለኝ የእጄን ነው ያገኘሁት የሚለው ዘፈን ግጥም በደንብ ይጋጠማችኋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ተሹመው ገና ወዳጅ ዘመድ እንኳ በቅጡ ሳይሰማ፥ የድጋፍ ሰልፍ ብላችሁ ከኣውራ ጎዳና እስከ እህል በረዳ እንደ በረሃ አንበጣ የወረራችሁበትን ያን ክፉ ቀን ያስታውሳችኋል

   ያኔማ ተሸውደናል። አንተስ ብትሆን አልደገፍክም ነበር?

  ስማ … እንኳን እኔ ሳኦልንም ያነገሰ አምላክ ተፀፅቷል። ዛሬ ግን የማይመልሱልንን ሰው ነጥቀውን የማይፈታ ቂም ተቀባብረናል

    ታዲያ … የእኛስ ፀፀትና ቂም ለምን አልታየህም?

  መነፅሬን ስላላደረኩ ይሆናል

   ቀልዱን እናቆየውና … ደህና ነህ ግን?

  ደህና ነኝ! እናንተስ? PP እንዴት ይዟችኋል? ከኣንድ ለኣምስት አምልጠህ ኣምስት ለኣንድ ሊጠረንፍህ ODP ሲዝትብህ ሰማሁ

   ኤዲያ! ኦዲፒም በለው አዴፓ ሁለቱም የሙጃ እርሻ ናቸው። በየመድረኩ ጃኖና ቡልኮ እየተሸለሙ፣ ዱላና ጦር ጨብጠው ሲቆሙ ወንዶች መስለውህ ነው? አቶ ሽመልስ አብዲሳም ሆኑ አቶ አዲሱ አረጋ፦ ትላንት … ለሰላምታ የተዘረጋ የአቦይ ስብሐትን መዳፍ ሲጨብጡኮ በፍርሃት ትኩሳት የጣታቸው ጥፍር እንደ ሰም የሚቀልጥ ፈሪዎች ነበሩ። መቀሌ ለተመታው የህወሃት የአሽንዳ ከበሮ፥ አዲስ አበባ ላይ የአካላቸው መሸፈኛ ጨርቅ ብቻ ሳይሆን፥ የስጋቸው ከረጢት የሆነው ወፍራም ቆዳቸው ጭምር ወልቆ እስኪወድቅ ከቆመው የአክሱም ሃውልት በላይ ሲዘሉ እንዳልኖሩ፥ ዛሬ መድረክ አግኝተው ሲፎክሩ ቼ ጉቬራን ያስንቃሉ

  ቀስ ቀስ ወንድሜ! ወቅቱ ጥሩ አይደለም። እንዲህ ተናደህ ስታወራ ትኩሳትህ ይጨምርና፥ ሰዎቹ በCovid-19 አሳበው isolation room እንዳያከርሙህ

   እውነቴንኮ ነው! ከዓለም ቀድመን እንዳልተጠበብን፥ አሁን ዓለም ሁሉ ሲጠበብ እኛ መጥበባችን እንዴት አያናድድም? ወደድንም ጠላን፥ በዚህና በሚመጣው ዘመን እኩልነት እንደ ትላንቱ ሶሻሊዝምና ካፒታሊዝም ኣንድ እራሱን የቻለ ሥርዓተማህበር ሆኗል። ማንም ይህን እወነት ጥሶ በስልጣን ወንበር ላይ ተቀምጦ ሀገር መግዛት አይደለም አምሽቶ ማንጋት አይችልም። በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮዽያ ላለ ባለ ብዙ ነገድ፥ ወጥ የሆነ ብሔራዊ ስሜት ሁሉን አብሮ መቋጠሪያ ገመድ ነው። አንዱ ብሔር፦ በዛም አነስ፣ ወፈረም ቀጠነ፣ ወዛም ገርጣ በጋር ተደጋግፎ እንደተቀመጠ ዶቃ ነው፤ ለዛች ሀገር ውበት የሆነ – ፈርጥ! ኢትዮዽያዊነት ደግሞ የማይታይ፥ ነገር ግን በእያንዳንዱ የዶቃ ቀዳዳ ውስጥ በማለፍ ሁሉን በኣንድ ላይ የሚያስር ድብቅ ክር። ከጫፍም ይሁን ከመሀል፣ ከሰሜንም ይሁን ከደቡብ፥ ይህንን ክር በጥሼ ብቻዬን ማጌጫ ፈርጥ ሆኜ እቀመጣለሁ የሚል ዶቃም ሆነ ጨሌ ካለ ግን፥ ሁሉም … ኣንድ በአንድ እየተንጠባጠበ፣ ከወለል እየነጠረ መፈነጣጠሩ የተራ ጉዳይ ነው የሚሆነው። እየሰማኸኝ ነው?

  አይዞህ አታስብ፥ በዚህ ጩኽትህ እንኳን እኔ ጎረቤቶቼም እየሰሙህ ነው። ቀጥል … ስለ ቅርቡ ሹምሽር ላወጋህ ብደውል፥ ዶቃ” “ዛጎልእያልክ ታወዛግበኛለህ

   የምን ሹምሽር? የሹም ሸር አትለኝም። ዘንድሮ ሸረኛ እንጂ ሹመኛ የታለ? ሹመኞች ቢሆኑ ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደ stock market graph በየሰከንዱ እያወጡ የሚያውርዷቸው?

  ለጠበበ ጫማ የእግር ጥፍርን መቁረጥ መፍትሔ አይሆንም … በለኝ

   ታዲያስ … ብዙም ሳትራመድ ዳግም ቆስለህ ትቆማለህ

  ምን ትዝ እንዳለኝ ታውቃለህ? … ሄሎ? … ሄሎ?

   ሄሎ … እየሰማሁህ ነው

  ምነው ድምፅህ ራቀ? /ር ሊያ ታደሰ፦ ስልክ ስታወሩም የcovid-19ኝን ርቀት ጠብቁ ብለዋል እንዴ?

   ዶክተሯን ትተህ ትዝታህን ቀጥል

  ኣንድ አጉዋጉል ጂኒ ያገኘው የgenetics ሳይንስ ተመራማሪ፦ ከgenetic modification ውጪ hereditary የሆነ አካላዊ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ ቀንና ለሊት ላቦራቶሪው ውስጥ ውሎ ማደር ጀመረ፤ የሴትና የወንድ አይጦችን ጭራ ቆርጦ እያዳቀለ ጭራ የሌለው አይጥ ለመፍጠር ። ቢቆርጥ … ቢቆርጥ … ጭራቸውን የተጐመዱት አይጦች ሁሉ የሚውልዱት ባለ ጭራ አይጥ እየሆነ ቢያስቸግረው፥ ምርምሩን ትቶ፣ ቤተሙከራውንም ዘግቶ፣ መኝታ ቤቱ ገብቶ ሚስቱን አቅፎ ተኛ። ከዛም … በዘጠነኛው ወር፦ ሚስቱ ወንድ ልጅ እስከነቃጭሉ ስታስታቅፈው፥ እራሱንም ሆነ በአካባቢው ያለውን እውነታ መመለከት ተስኖት፥ በቤተሙከራው ውስጥ ያሳለፈውን ከንቱ ዓመታት መቆጨት ጀመረ። እሱም ሆነ አለም ከተፈጠረ ጀምሮ ሲገረዝና ሲገርዝ የነበረው አባት በሙሉ የሚወልደው ህፃን ተመልሶ ያው መሆኑ ገባው።

   እና?

  እናማ በቃ!

   በቃ?

  ታዲያ ሌላ ምን እንድልህ ፈለክ? ሴት ልጅ ፍለጋ እንደገና ተመልሶ ተኛ  ልበልህ? ሰሙን ከእኔ ሰማህ … ወርቁን ከፈለክ ደግሞ ወርቅ የተሸለሙትን ጠቅላይ ሚንስትር ጠይቃቸው። በምሳሌ ሳይሆን በተግባር ያሳዩሀል

   በል ደህና እደር

  ይኼን ነበር የፈራሁት! “ጫጩት ፊት ፈንግል አይወራም ሲባል እየሰማሁ … አልጋ” “ሚስትብዬ በገዛ እጄ አጋልኩህ፤ በጊዜ ልትጀምረው ነው?

   እኛ ጋርኮ መሽቷል

  እና ትንሽ ሳናወራ?

   እሺ ስለምን እናውራ?

  At least … የኣዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ስልጣን ሊለቁ እንደሆነ ጭምጭምታው ሲሰማ፤ አፉን ዘግቶ፣ አንገቱን ቀብሮ የከረመው ኢዜማ ቀን አስልቶ መግለጫ ሲያወጣ ምን እንዳልክ እንኳ ንገረኝ

   ጅብ ከሔደ ውሻ ጮኸ! አልኩ … አንተስ ምን አልክ?

  ጅብ ከሔደ ሌላ ጅብ ጮኸ! እውነትም መተኛት አምሮሃል … መልስህን አሳጠርከው። በል ደህና እደር፤ ታዲያ አደራ … “covid ያለው ኮልፌ ብቻ ነው በሚለው የኣራዳ ቀልድ እንዳትሸውድ፥ ጠንቀቅ በል! አስፈላጊ ከሆነም አስተማማኙን የface-mask እኔ እልካለሁ

   አሁን ማን ይሙት አፍ ለማፈን የሚያስችለውን ጥበብ ከእኛና ከመንግስታችን በላይ እናንተ አውቃችሁበት ነው?

  እሱንስ እውነት ብለሀል! ምን ላድርግ፦ አቶ ንጉሱ ጥላሁን አፋቸውን ያሸፈኑበትን ሳይሆን ጉንጫቸውን የደገፉበትን፥ የባለቤቴን ጡት መያዣ የሚያክል ጨርቅ ተመልክቼ … ተቸግራችሁ እንደሆን ብዬ ነው

   አቦ አንተ እኚህን ሰውዬ … አፉበላቸው እስቲ? ደግሞኮ አሁን ከስልጣን ወርደውልሃል

  አፉማ እኔም ባልላቸው እሳቸው ናቸው። ከስልጣን ወርደውልሃልላልከው ግን … ምናለ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለኣንድ ሰዓት ስልጣናቸውን ቢያበድሩኝ … ኧረ እንደው ለ 30 ደቂቃ እንኳ

   ከአረንጓዴው አሻራ ወደ ቀዩ አሻራ ልታሸጋግረን ነው?

  ምን ይልሃል? ይህንን አዴፓነክ የኣማራ እከክ አራግፌልህ፥ አንተም አለምም እፎፎፎይ ብላችሁ ተንፈሳችሁ ታድሩ ነበር

   እኔስ እሺ … አለሙ ግን በምን ሒሳብ ነው እፎይ ብሎ ተንፍሶ የሚያድረው?

  እሱን ሌላ ጊዜ አጫውትሀለሁ፤ ወይ ደግሞ የ 0zne layer መሳሳትን ለመቀነስ፥ አየርበካይ ኢንዱስትሪዎችን መዝጋት ብቻ ሳይሆን ረብአልባ አካሎችንም ማስወገድ በሚለው ኣዲስ proposal ስሸለም … ያኔ ይገባሀል

   አሃ! በከንቱ የሚባክነውን oxygen ቆጥበህ አተነፋፈሳችንን ፈታ ልታደርገው ነው?

  ታዲያስ! እኔ ጓደኛህ ምህዳሩንም ባይሆን አየር – ህዋውን አሰፋልሀለሁ። በል አሁን ደህና እደር

   አሜን! አንተም ደህና እደር

Comments are closed.