
By Admin
ሃሎ
ሃሎ
እንደምን አመሽህ?
እ ን ደ ፈ ለ ጉ ት
አንዳንዴ የጓደኛዬ ወስጠ-ወይራ መልስ ያስቀኛል። ቀንኮ ሞባይል ስልክህ ላይ ደጋግሜ ብሞክር፡ ብለው ብለው አልገባ፣ አልጠራ አለኝ፥ ሪንግ-ቶንህ (ringtone) የነፃነት ደወል ነው እንዴ?
አዎ፥ የእጅ ስልኬ እንደ አንጋፋው የስድስት ኪሎ አንበሳ ከስንት አንዴ ነው የሚጮኸው
ምን ሆኖ ነው?
ምን አውቃለሁ፤ የስልክ ጥሪው የኔት ዎርክ (network) ቅብብል በሳተላይት ሳይሆን በሸረሪት ድር የሆነ ይመስል፡ ጽዳት ሰራተኛዋ መጥረጊያዋን ይዛ ቴሌ ህንፃ ወስጥ ገብታ በወጣች ቁጥር እልም ይላል። አንተ ግን ደህና ነህ?
ደህና ነኝ። አዲስ እንዴት ናት?
ምን ትሆናለች፥ አድጋ ኣድዋ – ሰፍታ አክሱም ደርሳለች
ለማለት የፈለገው እየገባኝ አውቄ እንግዳ ሆንኩኝ፤ ጓደኛዬ ሲናደድ ይበልጥ ይመቸኛል። ሃሃሃ ምን አልባት አክሱም እንዳትሆን ሰፍታ ያደገችው
Whatever! “የአክሱም ሃውልት ለደቡቡ ምኑ ነው?” አሉ መሪ-ጌታ በሀይሉ
እሳቸውማ አረፉ፥ ነፍስ ይማር ነው ወጉ፤ ስልጣን ተረቱን ለ መሪ-ጌታ በዕድሉ አስረክበው
ለዚህ ነው አየህ “ከአንቶኒዮ (Anthonio) ተወለድ ወይ ከአንቶኒዮ ተጠጋ” የሚባለው
ማነው ደግሞ አንቶኒዮ?
እሱንም አታውቁም? አይይይ የኢትዮዽያ ዲያስፖራ …
አላውቅም
በል እዛው ጣልያኑን ጠይቀው፤ እዚህ ደደቢትን – እዚያ ዲያስፖራውን አንቅተን እንዴት እንችለዋለን?
Seriously አልገባኝም
Anthonio የሚለውን የጣልያን ስም ወደ አማርኛ ስትመልሰው “እንትና” ማለት ነው። ሁለተኛ እንዳትጠይቀኝ
አልጠይቅህም፤ አመሰግናለሁ። ግን እንዲህ “አይይይ የኢትዮዽያ ዲያስፖራ” ብለህ ያማረርከው ምን አልገባ ሲለን አይተህ ነው?
ህይወት፣ ቀልድ … በቃ በአጠቃላይ ሙድ፤ ከኣንድ ነገራችሁ በስተቀር ምናችሁም አያምረኝም
ብራችን ነው?
እሱም አያምረም፥ ላብ ላብ ይሸታል
ታዲያ ምናችን ነው የሚያምረው?
ነፃነታችሁ
ታዲያ ከነፃነት በላይ ምን አለ?
TPLF አለ
አይዞኝ! አልኩኝ የምለው ቢጠፋኝ፤ ኣንድ ቀን TPLF ከታች ነፃነት ከላይ የሚሆንበት ቀን ይመጣል። እስከዛው ግን …
እሰከዛው ምን? እናንተን ተሰፋ አድርገን እንጠብቅ? ስራም አላጣን
እንዴት?
ምን እንዴት ትለኛለህ? ሁሌ ንቅናቄ – ሁሌ መነቃነቅ ነው ስራችሁ። “እባብ ልቡን አይቶ እግር ነሳው” ይላል፤ እናንተንስ “እግራችሁን አይቶ ነው ልብ የነሳችሁ?” እስቲ እንደው ኣንድ ጊዜም ቢሆን ጨከን ብላችሁ – ልብ ገዝታችሁ ተነቃነቁና፡ ብዙም ባትርቁ እንደው ትንሽም ቢሆን ፈቀቅ ብላችሁ የሆን ቦታ ድረሱ። ዛሬም – ነገም ግንባር፣ ህብረት፣ ንቅናቄ ብቻ እየመሰረታችሁ፡ ኣንድ ፋይዳ ያለው ነገር ሳትሰሩ፡ እንዲሁ ምላሳችሁ ብቻ ሲነቃነቅ ይኸው በሞት እና በሚልዮን በሚቆጠር ህዝብ መካከል ኣንድ እርምጃ ብቻ ቀረ። ከዚህ ሁሉ ግንባር መሃል እንደው ኣንድ እንኳ ዘለቅ ብሎ ገብቶ ጭንቅላት የሚሆን ይጥፋ?
ምንድነው የምታወራው? አእምሮ – ማሰቢያ አንጎል የላችሁም እያልክ ነው?
ምን አንጎል አላችሁ?! እኛኑ አንጎል አደረጋችሁን እንጂ
ዛሬ ብሶበታል ጓደኛዬ አልኩኝ በልቤ፤ አሁን ምን አዲስ ንቅናቄ ወይ አዲስ ግንባር ተፈጥሮ ነው እንዲህ ምርር የምትለው?
ያልተፈጠረውን ጠይቀኝ?
እኮ ንገረኛ ካለ? እኔ እስከማውቀው ድረስ መጨረሻ ላይ የተመሰረተው እንግዲህ PAFFD ነው። ያውም እሱም በጣም ቆይቷል፥ እንጃ … ኣንድ ወር ገደማ ሳይሆነው ይቀራል?
ግራ-እግርን እና ቀኝ-እጅን አስታርቆ መርቶ የመኪና ማርሽ ከዜሮ ወደ ኣንደኛ መቀየር የሚያስችል አእምሮ እንኳ የሌለው ጎሰኛ፡ እንዴት ብሎ በሰው ስጋና ደም የደለበ መንግስት እለውጣለሁ ብሎ እንደሚያስብ ይገርመኛል
በሰው ስጋና ደም የደለበ መንግስት… ስትል፡ በቀደም ዕለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ – አቶ ደመቀ መኮንን ረሃቡን አስመልክቶ መግለጫ ሲሰጡ፡ የአንገታቸውን ዙሪያ (circumference) ተመልክቼ የጉሮሮአቸውን ወርድ (diameter) ገመትኩና፡ ያቺ ሃገር ለምን በተደጋጋሚ እንደምተራብ የነበረኝ እንቆቅልሽ ሁሉ ተፈታ
ገዘፉብህ?
ገዘፉብህ ብቻ? ስምን መልአክ ያወጣዋል አሉ … ቦልድ (BOLD) ሆነዋል። እኔ የምለው፦ የዚህ መንግስት የከፈተኛ አመራር አባላት ሹመት፡ በዕውቀት ነው በክብደት? ፕሬዘዳንቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ፣ ተዋራጅ ሚኒስትሮቹ … ኣስሩን ብቻ እንኳን አደራርበህ ብታጋደማቸው፡ አይደለም የኣባይን ወንዝ፡ አምላክ በኖህ ዘመን ምድርን ያጠፋበትንም ውሃ ገድበው ማቆም የሚችሉ ነው የሚመስሉት። ምናለ እንደሰውነታቸው ጭንቅላታቸውም … አላስጨረሰኝም ጓደኛዬ
ጭንቅላታቸውስ ቢሆን ምን ይወጣለታል? ለእንደአንተ አይነቱ በጥላቻ ዓይኑ ለተመረዘ “ቶክሲክ ዲያስፖራ” አልታይ ብሎት እንጂ፡ ጥሩ ግንበኛ አግኝቶ ቢፈለፍለው፡ ከእያንድኣንዳቸው ጭንቅላት ሦስት ሦስት የላሊበላ ግንብ ያወጣበታል። ይብላኝ ለእኛ እንጂ
እናንተ ምን ሆናችሁ?
ከጥቂት ወራት በፊት፡ እዛው እናንተው አካባቢ ተወልዳ ከአደገች አንዲት ዲያስፖራ ጋር በመከረኛው ፌስ-ቡክ ተዋውቀን ጨዋታ ብጤ ብንጀምር፡ ፎቶ ካልላክልኝ ብላ ወጥራ ያዘችኝ። እኔም ፍቅር ቢጤ ጀማምሮኝ ነበርና፡ ሰውን፣ ቤቱን፣ የሰፈሩን ወሻ ሳይቀር አንስቼ ስልክላት፡ እልም ብላ ጠፋች!
ሳይደርሳት ቀርቶ አኩርፋህ ይሆናላ
ምን አኩረፋኝ … አፍራብኝ ነው አንጂ። ከሁለት ወር ቦሃላ በዛው በፌስ-ቡክ አግኝቼ ብጠይቃት “Sorry, አንተም፣ ህዝቡም፣ እንስሳውም ሳይቀር ጐብጣችኋል – ልክ አይደላችሁም ተንጋዳችኋል“ አለችኝ። ተይ ግድ የለም ኑሮ ነው፡ ሁሉም ሲስተካከል ቀጥ እንላለን ብዬ ብለምናት “በቃ ቀጥ ስትሉ ሪኩዌስት (request) ላክልኝ” ብላ አን-ፍሬንድ አደረገችኝ
አንተ ነሃ ጥፋተኛ
ምንድነው ጥፋቴ?! በኣንድ-ለኣምስት ታሰርን አንጂ ኣንድ-በኣመስት የተደገፍን መሰለህ? እንዴት ብለን ቀና-ቀጥ እንበል?
ማለቴ … ቢያንስ – no no የካሜራውን ፒክቸር ፎንት (font) ኢታሊሳይዝድ (Italicized) አድርጌው ነው – አትላትም ነበር?
እሱማ ኑሮ ራሱ Italicized ሆኗል
ረሃቡ ግን እንዴት ነው?
ባክህ ተወኝ፤ ትራንስፎርብሜሽን፣ ልማት፣ ዕድገት ስንል ከርመን በስተመጨረሻ የአቶ መለስ ቪዠን (vision) ኤክስ ሬይ (X-ray) ሆኖ አረፈው። በቀን ሦስት ጊዜ የሚበላ – የፋፋ ህብረተሰብ ጠበቀን በቪዠኑ ውስጥ አሻገረን ብናይ፡ ያለችውን ስጋ አራገፎ – ኣስራ አምስት ሚልዮን ህዝብ በአጥንቱ ቆሞ አፈጠጠብን
አንድ ጊዜ የሆነውን ልንገረህ፤ አንድ የኢንቨስትመንት አማካሪ ቢሮ ከኣንድ ክልል ጋር ይወዳጅና፡ የክልሉን ኣራት ዞኖች ተፈጥሮአዊ ገፅታ በማጥናት ለልማት የሚሆን ጠቋሚ መረጃ እንዲያቀርብ ወደ ኣንድ ሚልዮን ብር በሚጠጋ የገንዘብ ክፍያ ውል ይፈፅማል። በሁለት ሳምንቱ ጥናቴን አጠናቀኩ ይልና በክልሉ ከፍተኛ ሴምናር ይዘጋጃል። እኛም የኢኮኖሚና ልማት ሰነዱን ገምግሙ ተብለን ሶሾሎጂስቱ፣ አንትሮፖሎጂስቱ፣ የሳይንስ – የጥበብ ተመራማሪው፣ ከየዘርፉ አንዱም ሳይቀር ከሞላ ጐደል ሁለት ቀን ተጉዘን የከልሉ ዋና ከተማ ገባን
በሪፖርቱ በስተመጨረሻ፦ የአጥኚው ቡድን መሪ – አንድ የተከበሩ ኢኮኖሚስት “የጥናቱ መረጃ እንደሚጠቁመውና እኛም በክልሉ ስንዘዋወር እንደተመለከትነው፡ ለክልሉ የከብት ማድለብ ተግባር ትርፋማ የልማት ዘርፍ ነው” ብለው የመሰብሰቢያ አዳራሹ ሙቀት አድክሟቸው ነው መሰለኝ ከወንበራቸው ላይ በጀርባቸው ዘፍ አሉ። እግዚኣብሔር ያሳይህ! ጥናቱ ያለቀው በሁለት ሳምንት፣ ተጠቀምነው ያሉት የአካባቢ ጥናት ዘዴ – ተሳትፎአዊ (participatory research method)፣ ክልሉ ያለው ኣራት ዞን፣ ከመንገዱ አስቸጋሪነትና ከአየር ንብረቱ ሞቃታማነት የተነሳ፡ እረፍትና ቀዝቃዛ ነገር መጐንጨት ግዴታ ስለሆነ ከኣንዱ ዞን ወደ ሌላው ዞን ለመሄድ፡ በዘመኑ ኮብራ (cobra) እና ፓዝ ፋይንደር (path finder) መኪና እንኳን በትንሹ ኣንድ ቀን ይፈጃል። በክልሉ ኣንድም የበሬ ስጋ መሸጫ ስጋ-ቤት እንደሌለ፣ ለሆቴል-ንግድም ይሁን ለግል ፍጆታ ህብረተሰቡ የሚጠቀመው የፍየል ስጋ ብቻ እንደሆነ እየታወቀ፣ የደለበውን እንስሳ አጓጉዞ በአቅራቢያው ወዳለው ገበያ ለማድረስ እንኳን ምንም አይነት አመቺ የመንገድም ሆነ የተሽከርካሪ አገልግሎት በሌለበት ሁኔታ፡ ጥናቱ ያንን ሁሉ ብር ተሸለመ
ታዲያ ምኑን አይቶ ነው ከብት አደልቡ ያለው?
በመስኖ ለምቶ ያደገወን የበቆሎ አገዳ – አልኩኝ እየሳኩኝ
እንኳን ብቻ አምላክ ዓይኑን ጋርዶት ያንን ምስኪን ህብረተሰብ በከብት ማደለብ ድካም ብቻ ገላገለው። እሸቱ ተገሽልጦ – በቆሎው አፍጥጦ ቢመለከት ኑሮማ፡ የዶሮና የተርኪ (turkey) እርባታም ይጨምርባቸው ነበር
ታዲያ አሁን ለእኛ ረሃብ ይነሰን? የገበሬው ችግር፣ የህብረተሰቡ ፍላጐት ሌላ – ተማርኩ የሚለው፣ የመፍትሔ ተቋሚው ምክርና መላ ሌላ …
ለዚህ’ኮ ነው እኔም አልማርም ብዬ ኣራተኛ ላይ ያቆምኩት። ለነገሩ ኣምስተኛ ክፍል ገብቼ ቢሆን ኖሮ ይኼኔ – የስልጣን ጥመኛ ተብዬ ተገምገሜ ነበር
እና አሁን ላለመማርህ ሰበብ (excuse) እያቀረብክ ነው?
የምን ሰበብ? ሀቅ ነው አንጂ፤ የተማሩት ምን ፈጠሩ? ከዘንድሮ የሀገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምርቃት፡ መሬት ጠብ የማይለው የእማሆይ ብርቱኳን ዕርግማን ይሻላል
ፈጠሩም አልፈጠሩም ብቻ መማር ጥሩ ነው፤ ያኮራል – ያስከብራል
በለውውውውው
ምነው? እውነቴን እኮ ነው። የተማረ ይግደለኝ ሲባል አልሰማህም?
በል እንዲህ ብለህ ተመኝተህ፡ በገዛ ኣፍህ አሟሟትህን እንዳታከፋው
እንዴት?
ያ ተረት ድሮ በድርጉ ዘመን … ይቅርታ አኮላትፎኝ ነው … በደጉ ዘመን ነበር የሚሰራው። አሁን የተማረው ተማሮ ኮብል-ስቶን በጨበጠበት ዘመን “የተማረ ይግደለኝ” ብለህ ብትተርት፡ እንደ ቅዱስ እስጢፋኖስ አቧራ ሆነህ እስክትቦን ድረስ ነው የሚፈጠፍጥህ። ቅዱስ እስጢፋኖስስ ለፅድቃቸው ነው አንተ ለምንህ ሊሆንህ ነው?
እኔን ተወኝ፤ አንተ ግን አሳዘንከኝ
ምን ሆኜ ነው የማሳዘንህ?
አኮላትፎኝ ነው ብለህ ስትርበተበት ነዋ። ጎረቤትህ ፌደራል ነው እንዴ? ወይኔ ጓደኛዬ! ድሮኮ ሳውቅህ ደፋር ነበርክ
ሲጀመር፦ እዚህ ሀገር ፌስታል እንጂ ፌደራል የሚባል ነገር የለም። ሁለተኛ ደግሞ፦ ድፍረትና ደፋሪ ዱሮ ቀሩ፤ ዘንድሮ ተረቱም፣ ኑሮውም፣ ህልሙም፣ ሁሉም ተቀይሯል
ማለት?
በቃሃ በፊት “ኣፍ ሲያመጥ – ራስ ሲመለጥ አይታውቅም” ነበር የሚባለው፤ አሁን “ኣፍ ሲያመልጥ – እግር ሲያዳልጥ” ሆኗል። ዛሬ ለወለድከው ለገዛ ልጅህ እንኳን ሽብሩ ብሎ ስም ማውጣት አሸባሪ አስብሎ በሚያስወነጅልበት ሰዓት ምን ህግ አለ ብዬ ልድፈር? ዳር ነኝ ብለህ አፍህ ትንሽ ትንፍሽ ሲል፡ እግርህ አዳልጦት ዱብ ነው – ማዕከል ላይ
አይዞህ! እዛው ዳር እያለህ ማዕከላዊም ሳትገባ፡ እኛው ዱብ እንላለን ኣዲስ አበባ
አዲሱን የከተማ ካርታ እልክለሃለሁ
ምን ያደርግልኛል?
ዱብ ስትል ከስማይ አንተው ራስህ ማዕከላዊው ግቢ ላይ እንዳታርፍ ነዋ
ግድ የለም አታስብ – ጂፒኤስ (GPS) እጠቀማለሁ
በል ደህና እደር
እንዴ – ዋናው የደወልኩበትን ጉዳይ ሳትነግረኝ?
ምንድነው ዋናው ጉዳይ?
ረሃቡ ነዋ
ሰለረሃቡ ምን ልንገርህ?
የሚባለውን ነዋ፡ ከተማው፣ ባለስልጣናቱ የሚያወሩትን
እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም። ቆይተው ረሃቡ ከፈነዳ ግን “በዚህ ረሃብ ውስጥ አካባቢውን የሚያተራምሰው ፀረ-ልማት የሆነው ሀይል – የሻቢያ እጅ የግንቦት ሰባት እግር አለበት” ማለታቸው ስለማይቀር ያኔ እኔ ራሴ ደውዬ እነግርሃለሁ
ሰውን እና መሬቱን እንዲህ በዘር በሜትር ሲሽነሽኑት፡ የአደጋ ዝግጁነቱንና የመከላከሉን ተግባር ለምን በክልልና በዞን ደረጃ አጠናክረው ማዋቀር እንዳልፈለጉ ገርሞኛል። ጐርፍም መጣ ረሀብ፣ በሽታም ይሁን ዝናብ – የዝግጁነቱ እና የመከላከሉ ተግባር ክልላዊ ቅርፅ ኖሮት በአገባቡ ቢዋቀር ኖሮ፡ ብሔራዊው ተቋም እንዲህ ፍርክስክሱ ባልወጣ ነበር። ተፈጥሮ ሰፊና ጉልበታም ናት። የጥቃትዋን ሀይል ማሳነስና መመከት የምትችለው የተግባርና የሀላፊነት አጥርህን በማጥበብ ነው። ያኔ በምን ላይ እስከምን ድረስ መዘጋጀት እንዳለብህ በቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ይቀልሀል። ወባ ይሁን ረሀብ ወይንም ጐርፍ የመከላከያ ግብዓትህን አይነትና መጠን – ከሰው ሀይል አንስቶ እስከ መድሃኒት፣ እህልም ይሁን አሸዋ ሁሉን በአገባቡና በቅደም ተከተሉ እንድታደራጅ ከማገዙም ባሻገር፡ የስርጭት መስመርህን በማሳጠር አደጋው በተከሰት ወቅት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ይስችልሃል
አሁንስ መች ዘገዩ? ቀድመው’ኮ ነው የውጭ ምንዛሪ ችግር አንዳለባቸው ያሳወቁት
እስቲ አንተ ደግሞ እንደ መሪ-ጌታ በዕድሉ ስለ ኢትዮዽያ ሲወራ ዘለህ ካሊፎርኒያ አትግባ። ቢያንስ ጋምቢያ ላይ እንኳን ትንሽ አረፍ በል
ታዲያሳ! ለመኑ ለመኑ ለመኑ መጽዋች ጠፋ። ያው ረሃቡን አፋፍመውብን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ አደረጉን። “እህሉ አለን፥ ለግዢ እና ለስርጭት የምናወለው ገንዘብ ነው የቸገረን” ሲሉ አልሰማህም?
ታዲያ እህሉ ካለ … ጓደኛዬ አላስጨረሰኝም
በል በል ቻው በቃህ
ምነው?
የስልኬ ባትሪ አለቀ፡ ምልክት እየሰጠኝ ነው
እንዴ – የቤት ስልክ ላይ አይደለ እንዴ ደውዬ የምናወራው?
ኦፋ! እሺ በቃ ኤሌክትሪክ እያለቀ ነው
ከመቼ ወዲህ ነው ደግሞ የስልክ መስመር …
ነገርኩህ አይገባህም… የእኛ ቤት የስልክ ቀፎ ከቻይና ነው የመጣው በኤሌክትሪክ ሀይል ነው የሚሰራው
ቆይ አንዴ ስማኝ
እኔ ዘጋሁት እሱ ይስማህ
እሱ?
አንድዬ ወይ አንዱ
ስልኩን ዘጋው … እኔም ዘግይቶ ገባኝ። ወይ ወንዱ! በገዛ ወሬያችን እንዲህ ተሳቀን እስከመቼ? ቆይ – ይንጋ እንጂ ነገውኑ ኣንድ ግንባር መስርቼ …