Post

የሳምንቱ ስልኬ III

የሳምንቱ ስልኬ III

By Admin

ዘንድሮ ምነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨከኑብን የሠርግ ዶሮ ይዘው ሳይጎበኙን?

ሰላምታው አይቀድምም?

በጣም ይቅርታ! የሆድ ነገር ሆኖብኝኮ ነው። እንደምን ሰነበትክ? የጣሪያህስ ዲሽ ሰላም ውሎ አመሸ?

የጣሪያውን ዲሽ ቢነቅሉት ግንባሬ ላይ ያለው ዓይኔን ቆፈረው አያወጡት፤ ግፍና በደሉን እንደው በገሀድ እያየነው ነው

ገና እንዴት ነበር?

ጭር ብዬ ነው የዋልኩት ባክህ፤ ጭራ አልቆብኝ

ጭራ?

አዎ ጭራ

የመምህሬ ዝንብ ማባረሪያ?

አሁን የምዕመናኑ ረሃብ ማርገቢያ ሆኗል። የሰፈራችንን ስጋ-ቤት ባለቤት አስቀምጥልኝ ብዬ ነግሬው ረስቶ ሸጦት፡ ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀን የኣንድ ቀበሌ ህዝብ ነው የገላገለን

አንተ በጭራ ምን አጣላህ? ጭቅና አትበላም? አልኩት ልነጅሰው ብዬ። ባለፈው እንደነገርኳችሁ ጓደኛዬ ሲናደድ ነው ይበልጥ የሚደላኝ

አንተ ምን አለብህ 12 ሆኖ ተፈልፍሎ በ12 ቀኑ ለእርድ የሚደርስ አሳማ የሚበላ አሳማ ህዝብ መሀል እየኖርክ እንደፈለክ ተናገር። በሬ ዛሬ ለአብዛኛው ኢትዮዽያዊ የሥጋ-ከብት ሳይሆን የስጋ ዘመድ ሆኗል። የማይነካ፣ የማይበላ ዕርም!

ለራስህ ብዬ ነው። በበዓል ምድር … በልቶህ ነበራ በዛ ስል ቢላዋ?

ቢላዋ’ኮ አሁን የጦር-መሳሪያ ነው። ባለስልጣኖቹ ቤት ካልሆነ በስተቀር እንደ ዱሮው የትም አታገኘውም። በልማታዊው ኑሮአችን ስጋ ተቆርጦ የሚሽጠውም ሆነ የሚከተፈው በምላጭ ሆኗል። አንተ ግን ደና ነህ?

አለሁ ይመስገነው። ባለፈው’ኮ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ተከትሎ ተቋውሞው እንደተነሳ ልደውልልህ ብዬ … አላስጨረሰኝም ጓደኛዬ

እኔ ሲገባኝ ተቃውሞው የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ሳይሆን – የሀዲሽ አበባን ማስፈር ፕላን ነው

ማነች ደግሞ ሀዲሽ አበባ?

ልማዳዊው ተቃዋሚ “አዲስ አበባ በል – እምቢ ፊንፊኔ” እያለ ባዶ ሜዳ ላይ ሲንፈራፈር፡ ልማታዊው መንግስት ድምፁን አጥፍቶ የገነባት አዲሲቷ የፈርኦን ከተማ ናታ ሀዲሽ አበባ። ስለዚህ ሰው ስትከስ እያስተዋልክ። ዕድገት፣ ለውጥን የሚጠላ ማን አለ? የትኛውም ህብረተሰብ ኢፍትሀዊ ስልጣንን እንጂ ፍትሀዊ ስልጣኔን ይቃወማል የሚል ግምት የለኝም። ሀዲሽ አበባ ባትሰፋ ባታድግም’ኮ አጓራባቾቿ ሰፍተውና አድገው መቀላቀላችው አይቀሬ ነው

ይሁንልህ

ይሁንልህ አትበል! “ልክ ነው” ብለህ እውነታውን ተቀበል

ብቀበል ባልቀበል እኔና መሰሎቼ ምን እንፈጥራለን? “ፋርዳ” ነን! እዛው ሜዳ ውስጥ ያለው ሀቁን ተረድቶ ኣንድ ሆኖ ቢቆም እንጂ …

ተስማምቻለሁ። ያ ነበር ፋይዳ የሚኖረው

ለዚህም አንድነት ሲባል ጥያቄውን ማዕከላዊ ቢያደርጉት ጥሩ ነበር፥ ለምሳሌ “መሬት ለአራሹ” ብለው አልኩ ውስጤን ሳቅ እያፈነው

ታዲያ የካሩቱሪ ልጆች ከዴሊ ይምጡና “ማዕከላዊ” ያድርጉታ? ህዝብ ከመሬቱ ተፈናቅሎ ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚሆነውን እርሻ ገበሬ ሳይሆን ነጋዴ በሚያርስባት ሀገር “መሬት ለአራሹ” ብሎ ደሃው በክላሽንኮቭ የሚታረሰው በምን ሂሳብ ነው? የደቡብ፣ የጋምቤላን መሬት ቀምቶ በግሬደር የሚንደው ማነው? የእነ ወዲ – አላሙህዲንን ልጆች ከሰሜን ሳውዲ ሰብስብና አስጩሃቸዋ?

አንተ ራስህ ጮህክ እኮ እስቲ ቀስ በል

አንተ ነሃ የምታስጮኸኝ፤ እወነቱን እያወከው እንዳላወቀ ስትፈታተነኝ

እንጫወት ብዬ’ኮ ነው። እንተ እንዳልከው የዚህ “ማስፈር ፕላን” ዋና ኣላማ ለሀዲሽ አበባ የጸጥታ ቀጠና (buffer zone) መፍጠር ይመስለኛል። አለበለዚያማ በጤናማ የኢኮኖሚ ዕድገት፦ ህብረተሰብ፣ ሃብትና ባለ-ሃብት የሚያብቡት አብረው በጋራ ነው። የእኛ የ25 ዓመት የዕድገት ቀመር ግን የሃብት እንጂ የባለ-ሃብት ለውጥ አላሳየንም። የኢንዱስትሪያላይዜሽን መሠረታዊ ፍልስፍና’ኮ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን አምራች ገበሬ (subsistent farmer) መካናይዝድ እንጂ መካን ማድረግ አይደለም።

ዛሬ በሀገሪቷ ውስጥ ለሚታየው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትና ረሃብ ዋነኛው ምክንያትም እንዲህ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪያል የልማት ዘርፍ በድንገት እና በጉልበት መታጠፍ ነው። ኣዲስ የኢኮኖሚ ዕድገት paradigm ተፈጠረ ካልተባልን በስተቀር የለውጡ ስርዓታዊ ጉዞ፦ ከግብርና ወደ ግብርና-መር-ኢንዱስትሪ ከዚያም ወደ ኢንዱስትሪ ነው። እንዲያውም ይህንን ባለ ሶስት ጣቢያ (station) ስምሪት የበለጠ ለማለሳለስ እኔ በግሌ በግብርና-መር-ኢንዱስትሪውና ኢንዱስትሪው መካከል “ኢንዱስትሪ-መር-ግብርና” የሚል ኣንድ ፌርማታ አበጅቼለታለሁ። ኢንዱስትሪውን እያደመቀ፣ እያሰፋ የግብርናውን ደብዛ ጨርሶ ሳያጠፋ ነገር ግን ቀስ በቀስ የሚያደበዝዝ መድረክ ማለት ነው። በዚህ የኢኮኖሚ ዕድገት ሽግግር ውስጥ ኢንዱስትሪያላይዜሽኑን ፍጹማዊ ለማድረግ የምርት እና የአመራረት ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአምራቹንም ልማዳዊና ተፈጥሮአዊ ማንነት የመነካካት፣ የማበጃጀትና የመቀያየር ተግባራት ሊከናወኑ ይገባል

ሃሎ? እየሰማኸኝ ነው?

ምን ምርጫ አለኝ? ቀጥል

እውነቴን’ኮ ነው። የአምባገነኖች የዕድገት ፕሮጀክት ጥናት እና ዕቅድ ዋነኛው ራስምታት፦ ህብረተሰቡን እንዴት የልማቱ ተሳታፊ (ለልማቱ ጠቃሚ) እናደርገዋለን የሚል እንጂ ህብረተሰቡ እንዴት የልማቱ ተጠቃሚ ይሆናል የሚል አይደለም። ለዚህ ነው ኣንድ ሳይሆን ሰባት ዓባይን የሚገደብ መዋዕለ ንዋይ ያለ አግባብ የፈሰሰውና የሚፈሰው። እውነታው ግን፦ ህብረተሰቡን የልማቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ ጥናት በራሱ ብቻ የህብረተሰቡን የልማት ተሳትፎ ለማግኘት አስተማማኝ ዋስትና ነው። ኢኮኖሚውን ብቻ ሳይሆን ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪው ቀጠና በጉልበት መግፋት፥ የህብረተሰቡንም ልማድና አኗኗር (አመለካከት፣ ዕምነት፣ ባህል፣ ወዘተ) ቀስ እያሉ በጥንቃቄ ማንሸራተት ያስፈልጋል። የማህበረሰብን አመለካከት፣ አመጋገብና taste (ጣዕም) ሳይቀይሩ ከስንዴ ገንፎ ወደ ስንዴ መኮረኒ፣ ከጤፍ እንጀራ ወደ ጤፍ ላዛኛ፣ ከሸንኮራ ስኳር ወደ በቆሎ ማጣፈጫ (corn syrup)፣ ከጀበና ወደ ማሽን ቡና፣ ከዳማከሴ ወደ ኪኒንና መርፌ በዝላይ መሻገር የገበያ ብቻ ሳይሆን የህይወትም ዋጋ ያስከፍላል

እሺ አሁን እኔም የህይወት ዋጋ ከመክፈሌ በፊት በጥንቃቄ ልሻገር ትንሽ ጊዜ ስጠኝ

ምንድነው የትነው የምትሻገረው?

የመኪና መንገድ ነዋ። ወደ እስጢፋኖስ እየሄድኩ ነው

እንዴ ጥምቀት ነው እንዴ ዛሬ?

ጥምቀትን ለማክበር ብቻ ነው እኔ ቤተ-ክርስቲያን የምሄደው?

ታዲያ እንደ ክርስቶስ በ30 ዓመትህ አትጠመቅ – ምን ትሰራለህ?

በጣም ትገርማለህ፤ መፀለይ፣ ማህሌት መቆም አልችልም? ለዚህ አባባልህ ተመጣጣኝ መልስ ስለሚያስፈለግህ መጀመሪያ ልሳለም

ምን ልትል ነው? ፀሎት ካማረህ ደግሞ መቋሚያህን ሳይሆን መታወቂያህን ይዘህ ቂሊንጦ ማርያም፣ ቃሊቲ ገብርኤል፣ ማዕከላዊ እየሱስ አትሄድም? በዛውም አስተዋሽ ያጣ እስረኛ ጠይቀህ – ለነፍስህ ብቻ ሳይሆን ለስጋህም ፅድቅ አስቆጥረህ ትመለሳለህ። እስጢፋኖስ ምን ታደርጋለህ? የተማረከ እንጂ የተባረከ ደጀ ሰላም የት አለ? ቤትክርስቲያን ቅስቀሳ እንጂ ቅዳሴ ቀርቷል።

ነገርኩህ’ኮ አሁን ክፉ አናግረህ አታርክሰኝ ደርሼ እስከሳለም ትንሽ ጠብቀኝ

ይገርምሃል ጥምቀት ስል አርሙኒካ ትዝ አለኝ

የት የምታወቀው አርሙኒካ ነው ትዝ የሚልህ? “ትዝ አለኝ” ስትል ትንሽ ሼም (shame) አይዝህም?

ስማ አርሙኒካ’ኮ በጣም ከባድ ነው፤ የቱን ያህል ትንፋሽ እንደሚፈታተን እኔ ነኝ የማውቀው 

ሞክረኸው ነበር?

አልሞከርኩትም

ታዲያ ሳትሞክረው እንዴት ከባድ ነው ትላለህ?

አንተ ደግሞ ሁሉን ነገርን መጠየቅ ትወዳለህ

ስትዋሽ ነዋ?

ምንድነው የዋሸሁት?

ያልሞከርከውን አርሙኒካ ልክ እንደሞከርከው ሆነህ ታወራለሃ

ስማ … በስሱ፣ ትንሽ እንኳን በጨረፍታ ፈገግ ስትል የሚያማምሩ ወተት የመስሉ 32 ጥርሶቹዋን የማይላት girlfriend ነበረችኝ

እና?

እናማ ስስማት – ከዚህ ጥግ ወደዚያ ጥግ ያለማቋረጥ ኣፌ ሲመላለስ – አርሙኒካ የምነፋ ነበር የሚመስለኝ። ለዛ ነው ስሜቱን አውቀዋለሁ – ከባድ ነው የምልህ

እሷም ይሄኔ “ዋሽንት መንፋት ከባድ ነው” ትል ይሆናል

ሎኦኦል … በትክክል ተመልሷል። ገባሁልህ አይደል?

በደንብ 

የት ደረስክ አሁን?

መስቀል አደባባይ?

“አብዮት አደባባይ” በል የአብዮቱ ልጅ አይደለህ

አብዮቱ ናፈቀህ እንዴ?

ሀዲሽ ናት የነፈቀችኝ?

ታዲያ ኣንድ ሲንግል (ነጠላ ዘፈን) ልቀቅላታ?

ደብሉስ (ድርቡስ) መች ገብቷት። እንዳውም እውነትክን ነው መሀል ላይ ስትደርስ ንገረኝና የናፍቆቴን ኣንዴ አንጐራጉሬላት ከሷም ከአንተም ጋር በዛው እንሰነባበታለን

መሐሉ ላይ ነኝ’ኮ

እሺ ስልኩን ስፒከር (speaker) ላይ አድርገው

አደረኩት

ተምተረረም በል

ተምተረረም

“በፍቅር ማነቂያው ዶሮ እንዳይል በከንቱ እሪ አንቺን ወዶ – ክራሩን ስትሰሚ ብቅ በይ ቆሜያለሁ ከበርሽ ማዶ

በሙዚቃ ሳይሆን በጦር መሳሪያ የሚታጀብ ጥሩ ድምፅ አለህ። ሰለተግባባን ሁለታችንም ሳቅን

በል ደህና ሰንብት

ቆይ ጠብቀኝ እንጂ ተሳልሜ መልስህን እስክሰጥህ

ለሚቀጥለው ጥሪ አቆይልኝ

Comments are closed.