
By Admin
እንኳን አደረሰህ
እንኳን አብሮ አደረሰን። አንተ ሰው ትዝ የሚልህ ኣውደ-ዓመት ሲመጣ ነው?
አትፍረድ፥ ዕውቀትና ሙቀት ብርቅ የሆነበት ምድር ላይ ስትኖር አእምሮህ በዓመት ዘጠኝ ወር “hibernate” ያደርጋል፤ ለዛ ነው እንጂ ተረስተህ አይደለም
ይሁንልህ
ኑሮ እንዴት ነው?
ምን ትጠይቀኛለህ? እንደ ግንባርህ ነው
አትቆጣሃ፥ ሁሉም ነገር ተወዷል ሲባል ስለሰማሁ ነው የጠየኩህ
ውሸት ነው፤ አምፑልና ባልዲ በጣም ረክሷል። መግዛት ካማረህ ና
ሃሃሃ … ይበልህ ልል ነበር። ያኔ ትዝ ይልሃል በግድ “መብራት አብሩ” ብለን ስንቀጣችሁ? እኛ እናንተን ለመጠበቅ ሰፈር መንደሩን ስንዞር፥ እናንተ ተኝታችሁ የከተንበሪ (የበር) መብራት እያጠፋችሁ በእንቅፋት ስታስጨርሱን?
ወሬ አለብህ፤ ያኔ ሰው ልትጠብቅ አይደለም አንተ እራስህ ጠባቂ ያስፈልግህ ነበር
Anyways … በዓል እንዴት አለፈ? ዘንድሮ በግ ስንት ገባ?
ማን ጠይቆ ልንገርህ?
እንዴት?
ዱሮ በግ ለመግዛት በግ ተራ ሔደህ ገና ወደ መንጋው ስትጠጋ ያለውን ትርምስ ታስታውሳለህ? ደመ-ነፍሱ ነግሮት ተገዝቶ ላለመታረድ አንዱ በግ በሌላው በግ ሲደበቅ የሚፈጠረው የበጎች ትርምስ? ነጋዴው አሳዶ በስንት መከራ ሁለት የፊት እግሮቹን ይዞ ወደ አንተ ሲያመጣው እንኳን፡ ነፍስ ነውና በሁለት የኋላ እግሮቹ ከነጋዴው ቁመት በላይ ነበር የሚዘለው፤ አስለቅቆ ሊበር፣ ሊጠፋ። ዛሬ ወንድሜ፦ ገና ወደ መንጋው ስትጠጋ – ሴቷ በግ ጀርባዋን ስጥታህ ደረቅ ላቷን እንደ Shakira ነው shake የምታደርግልህ። በላቲኖ ባት ሳይሆን በአዳል በግ ላት “booty shake” ተገርመህ ሳታበቃ፥ ወንዱ በግ ከየት መጣ ሳትለው ልክ አሳድገኸው ሳያይህ እንደከረመ የቤትህ ውሻ፡ ሁለት የፊት እግሮቹን ደረትህ ላይ አሳርፎ ጆሮህን እየላሰ በሹክሹክታ “እስቲ ልብ! እስቲ ወንድ ዋጋ ጠይቅ?!” ይልሀል
ህወሃት የብሔር ብሔረሰቦችን ብቻ ሳይሆን የከብትና በጐችንም መብት ጭምር ነዋ ያስከበረው? አሁን የቀራቸው እንግዲህ የተወካዮች ምክር ቤት ወንበር መጠየቅ ነው
ለምን? በቀንድ ከብት እና በፀጉር ከብት መካከል ምን ልዩነት አለና ሌላ የውክልና ወንበር ይጠይቁ?
እና በቃ … በግ የቤት-እንስሳ ሳይሆን የቤት-ዕቃ ሆነ ነው የምትለኝ? የማይበላ?
እሱማ፦ ክፍልፋይ ሳይሆን ህይወት አጣፍተው፣ ቁጥር ሳይሆን ሞት አባዝተው ክቡር ፕሮፌሰር የተባሉት፤ እንደ እኔና እንደ አንተ ዕድሜያቸውን ሙሉ “ሁለትን ጽፌ ኣንድ አለኝ” እያሉ ሲደምሩ የከረሙት ሳይሆኑ፡ በአዲሱ የባንክ ሒሳብ ስሌት “ኣምስትን ጽፌ ኣምስት መቶ ሺህ አለኝ ” ብለው የከበሩት “ባለሃብቶች” በግ አይደለም ሰውም ገዘተው እየበሉ ነው
በጉስ ይቅር እሺ … ዶሮ በላህ?
እኛኮ ለመብላት ሳይሆን ለመበላት የተዘጋጀን ህዝቦች ሆነናል። ጓደኛዬ የመገረምም የፌዝም የሚመስል ሳቅ ሳቀ
ምን አሳቀህ?
የሆነ እውነት ትዝ አለኝ። በፊት ገና ወረርሽኙ ጎንደርና ጎጃም ገባ ሲባል – አዲስ አበቤውም “የትም አይደርሱም” በሚል ንቀት ሲዘናጋ፥ ካልተሳሳትኩ ከኬንያ ይመስለኛል አንድ ፀሐፊ “ንጉሱ ሰለሞን” በሚል የብዕር ስም “የፋሲካው በግ በገናው በግ ይስቃል” የሚል መጣጥፍ አስደምጦን ነበር። ዛሬ እውነት ሆኖ ሳገኘው አስገረመኝም አሳቀኝም
አዎን አስታወሳለሁ፤ እንዳውም እሑድ ቀን ይመስለኛል በመዝናኛ ፕሮግራም የተላለፈው። “ወረርሽኝ” ያልካት ቃል ግን ተመቸችኝ። ሰሜን ደቡብ ሳይል – ድንበር ሳይገድበው ከወልቃይት አምቦ፣ ከአፋር ጋምቤላ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ኤርትራ ኬላ ጥሶ እየገባ ነፍስ በጅምላ የሚያጠፋ የምስራቅ አፍሪካ ኢቦላ (Ebola)
የጋምቤላው ነገር ደግሞ በጣም ያስገርማል
እውነት ለመናገር፦ የህዝባችን መከራና እልቂት፣ ዜግነት የሌለን ዜጐች፣ ሀገር የሌለን ባለ-ሀገሮች፣ በአጠቃላይ መሪና ተቋርቋሪ ያጣን ህዝቦች መሆናችን አሳዘነኝ እንጂ አላስገረመኝም። ምክንያቱም ከእባብ እንቁላል እርግብ አይጠበቅማ! ባይሆን እኔን ያስገረመኝ፦ ልክ ገና ጥንታዊ የጋርዮሽ ሥርዓተ-ማህበር ውስጥ ያለን ይመስል “የዘር – የጎሳ ግጭት ነው” መባሉ ነው። የሰው ልጅ ከቡድን አኗኗር ወጥቶ፡ ሀገራዊና ህብረ-ብሔራዊ አስተዳደር ከጀመረበት ዘመን አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የተፈፀሙትና የሚፈፀሙት የጎሳ ወይንም የዘር ግጭቶች፡ አንዳቸውም ቢሆኑ በአካባቢው ካለው መንግስታዊ ስልጣን፣ ዕቅድና ፍላጎት ውጪ አይደሉም። አውሮፓም ብትል አፍሪካ፣ Serbia (ሰርቢያም) ሆነ ኢትዮጵያ የተፈፀመውና የሚፈፀመው የዘር-የሀይማኖት ዕልቂት ልቃቂት የሚፈተለው በመንግስት ባለስልጣናት ቢሮና ጓዳ ውስጥ ነው
ቆይ አንዴ ትጠብቀኝ? ሁለት ደቂቃ?
ይቻላል። በስልኩ ውስጥ ጓደኛዬ ከሰው ጋር ሰላምታ ሲለዋወጥ ይሰማኛል። ደስ የሚል ሰላምታ። ለካስ አንዳንዱ ሰላምታ ልክ እንደ ፊት ገፅታ የሚስብ ደም ግባት አለው እያልኩ ሳስብ ጓደኛዬ ተመለሰ …
Sorry በጣም … ከአቆምክበት ቀጥል
ማንን ነው ሰላም ያልከው?
አንድ ከልጅነት ጀምሮ አብረን ያደግን የሰፈሬ ሰው ነው። ከተያየን ትንሽ ቆይተን ነበር … ለዛ ነው፤ እንዳውም አንተም ሳታውቀው አትቀርም
ማነው? ብዬ ጠይቄ ሲመልስልኝ ግለሰቡን ስላወኩት ኦ! አለ እንዴ እሱ ሰው? አልኩኝ
የት ይሒድልህ? የ”ሌባና ፖሊስ” ዘመን ትውልድ እኮ ነው፤ እንዳሁኑ “ሔሮድስና ክርስቶስ” ተጫውቶ ያደገ መሰለህ?
ማለት? አልኩኝ፤ አንድአንዴ የጓደኛዬ ውስጠ ወይራ ንግግር እንኳን ለአንባቢ ለእኔ ለልብ ጓደኛውም ይከብዳል
ምን “ማለት” ትለኛለህ “ሌባና ፖሊስ” ተጫውተህ አታወቅም? አንዱ ያባርራል ሌላው ይባረራል፤ ከዛ ደግሞ ሲያዝ በተራው ተባራሪው ያባርራል፣ አባራሪው ይባረራል። በቃ! የታሰረው ተፈቶ፣ የተፈታው ታስሮ መኖር ባህል፣ ልምድ ነበር። አሁን ግን ጨዋታው “ሔድሮስና ክርስቶስ” ሆኗል – በተለይ ወንድ ልጅ ከሆንክ – ወይ የስደት በረሃ ወይ የስዶች ሰይፍ ይበላሃል
አይዞን ለትንሽ ጊዜ ነው፥ የታጠቁት ሰይፍ ላይ መውደቃቸው አይቀርም። አሁን ሁሉም ተምሯል። የፋሲካውም በግ በገናው – ማንም በማንም ላይ አይስቅም። የከፋፈሉን መስሏቸው በመለያየት አንድነትን፣ በጥላቻ ፍቅርን ከእነሱ በላይ በሚገባ የሰበከን አቡን የለም። የዘረኝነትን ክርፋትና ክፋት በሚገባ አስተምረውናል። አሁን የቀረን ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
መሪ?
lol ለምን እንደዛ አልክ?
ባለፈው “መሪ ፍለጋ” ብለህ ስትንከራተት ስላየሁህ
ሃሃሃ በትክክል ባትመልሰውም ጥሩ ገምተሃል። ግን’ኮ እውነቴን ነው። ቆጥ ባገኘ ቁጥር ዘሎ ተንጠላጥሎ፡ የአገጭ የጉንጩ ጺም እስኪቆም ጅማቱን ወጥሮና አንገቱን አጉብጦ ያዙኝ ልቀቁኝ ብሎ ጮሆ፡ ተመልሶ ጓሮ የሚጭር አውራ ዶሮ ሳይሆን፥ ለወፍ ለጥንቸሉ የማያገሳ – የጫካ አህያ አይቶ ሲነሳ ግን ማንቁርት ነክሶ፣ ጉሮሮ በስቶ፣ አንገት ሳይቀነጥስ የማይመለስ አንበሳ የሆነ መሪና አስተባባሪ ናፍቆኝ ነው። ከአፋርም ይሁን ከሱማሌ፣ ከአማራም ይሁን ከትግሬ፣ ወላይታም ይሁን ኦሮሞ ወይንም ጋሞ፣ ወላ ጋምቤላም ቢሆን ሐረሬ ቢፈልግም ጉራጌ – ብቻ ምንም ይሁን ከየትም ይምጣ – በቃ ቀጥ! ያለ፤ ሰፈሩን ሳይሆን ምድሩን የሚያይ፥ ዘሩን የማላውቀው እሱም ዘሬን የማይጠይቀኝ ኢትዮዽያዊ መሪ … አቋረጠኝ ጓደኛዬ
እኔም ላግዝሃ፦ ሀያሉን በሀይል ደካማውን በፍቅር የሚገዛ፥ የማይዋሽ፣ ኣዲስ ነገር ማውራት መፍጠር ማስተማር መግለፅ የሚችል። ኣንድ ትልቅ ማህበረሰብን በጨበጣ አስይዞ “ከዝርፊያህ ካላካፈለከኝ ህዝብ፣ ሀገር እከፋፍላለሁ” ብሎ በሆዱ የማይደራደር- ሙሰኛ ሳይሆን ሙሴ ነው የናፈቀህ?
lool አዎ! በጣም!
ከአገኘኸው፦ በነፍስም በስጋም መስዋዕት ልንሆን የተዘጋጀን በሚሊዮን የምንቆጠር ይሕሳቆች እንዳለን ንገረው
ያ መሪ ከተገኘማ – “ሚሊዮን” ለወያኔ አይደለም ለታላቁ የአርማጌዶን ፍልሚያም እጅግ ብዙ ነው። ኣንድ መቶ ሰው ይበቃል
አንተም ደግሞ እጅግ ሲበዛ አሳነስከው፥ ለሰላማዊ ነው ለትጥቅ ትግሉ?
ስማ፦ አንድ ሜዳ ውስጥ በኣንድ ኳስ እየተራገጥክ ሁለት ዓይነት ህግ ሲዳኝህ የት ሀገር ነው ያየኸው?
እና? … ብረት አንሱ፣ ጠመንጃ ንከሱ ነው የምትለን?
በሽሽት ታንኳ ብዙ ሺህ ማይልስ ቀዝፌ፣ ድብና ደደብ የሚራባበት የብርድ ወደብ ላይ ተራግፌ፡ ስንት መከራ ችሎ ሀገር ውስጥ የአቅሙን እየተፍጨረጨረ ያለውን ሰው “ይህን ትግል ጣል – ያንን ትግል አንሳ” ለማለት ሞራሉ የለኝም። ከጥርስ እስከ መትረየስ፣ ከጥፍር እስከ ሞርታር የሚያዋጣውን መርጦ መታገሉ ለእርሱና ለእርሱ ብቻ የተተው ምርጫ ነው። እኔ የማወራህ ስለ እኔና ሰለመስሎቼ ነው፤ ህግ ደፍረን ብንታሰር ህጋችን ስለማይደፈረው። ሁለታችንም ሳቅን …
ታዲያ አንተና መሰሎችህ በኣንድ መቶ ሰው ምን ታደርጋላችሁ?
መቶን ትንሽ ቁጥር አድርገኸው ነው? ወኔና ደም ያለው ወንድ ቢገኝ፡ መቶ ሰዎች በተለያዩ ኣስር ሀገራት ውስጥ በሳምንታት ልዩነት በአንድ ቀንና ሰዓት የሚወስዱት ተመሳሳይ እርምጃ ቢያንስ ለሦስት ወራት ትልቅ ዜናና መወያያ ርዕስ መሆን ይችላል። አላየህም ሶስተኛ ክፍል ሆነን የምንሰራው ጂምናስቲክ መድረክ ላይ ዘጠኝ እና ኣስር የሚሆኑ ዳንኪረኞች በተቀናጀ መልክ በኣንድ ሪትም (rhythm) ሲወዛወዙት እንዴት ያለ ዘመናዊ ዳንስ ሆኖ ህዝብ በጩኸትና በፉጨት እንደሚያብድለት? የኣንድ ተግባር ውጤታማነቱ ትልቅነቱ ብቻ ሳይሆን ወጥነቱና ተከታታይነቱም ጭምር ነው። በተለይ ትግል ላይ ቁጥር ሁልጊዜ የስኬት ምስጢር ነው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። በተለያዩ ስፍራዎች የምትወስዳቸው ጥቂት እርምጃዎች ሲመሳሰሉና በቀን-በሰዓታት ሲገጣጠሙ፥ ያ በራሱ ዓይንና ቀልብን መሳብ የሚችል ደማቅ ክስተት ነው። የአውሮፓንም ሆነ የአሜሪካንን በአጠቃላይ የዓለምን ህዝብ “ለምን?” ብሎ እንዲጠይቅ ታደርገዋለህ። ምክንያቱንና እውነቱን ሲያውቀውም ደግሞ፦ ለወንጀለኛው መንግስት ግብረአበሮች ከለላ መሰጠቱም ሆነ ለፋሽስታዊው ስርዓት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ መሞገት ይጀምራል። ያኔ በምዕራባውያን በጎ ፈቃድ የቆመው መንግስት የሀይል ምንጩ ሲደርቅ፣ የመሸሸጊያ ዓለቱ ሲፈርስ ወዶ ሳይሆን ተገዶ ይንበረከካል። በነገራችን ላይ አይሁድ ቤቱን ሲያፀዳ ለምን መጥረጊያውን ይዞ ከመውጫ በሩ ደጃፍ ወደ ቤቱ መሀል (ምሰሶ) ቆሻሻውን መጥረግ እንደሚጀምር ታውቃለህ?
አላውቅም
እንደ እኔና እንደ አንተ ከውስጥ ወደውጭ ሳይሆን ከውጭ ወደውስጥ ነው ቤቱን ጠርጐ የሚያፀዳው። ለምን እንደሆነ ደግሞ የዛሬ የቤት ሥራህ ነው፥ ገብተህ አንብብ
ቤት እስክደርስ ከማስብ አሁን ለምን አንተ አትነግረኝም?
እኔም አላውቀውም
አትቀልድ
ብዙ ርቀሃል እንዴ ከሰፈር?
አዎ
አይዞህ ከግንቦት ኣንድ ጀምሮ በኣንበሳ አውቶቡስ እንደ ልብህ የሚያጓጉዝህ የነፃ ትኬት ተዘጋጅቶልሃል። ኦ! ለካ አንተ አስተማሪ አይደለህም። አንጀት ራበኝ ብሎ “አምባሻ” ሲጠይቅ አንበሳ አውቶቡስ የሚያዝ መንግስት …
አንተስ ከእነርሱ በምን ተሻልክ? ምክንያቱን ንገረኝ ስልህ …
ሃሃሃ በል ደህና ሰንብት
ደህና ሰንብት