
By Admin
ዛሬ እንዴት ደወልክ?
ወዳጆች አይደለን እንዴ? እንኳን ደስ አለህ ልልህ ነዋ
ለምኑ?
አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር መረጣችሁ አይደል?
“አስመረጣችሁ” በል … ገና ደግሞ አፍንጫቸውን ይዘን እንመርጣለን። አማርኛ ጠፋህ እንዴ?
በዚህ ከቀጠልን’ማ ኣማራ ሳይጠፋ አማርኛ መጥፋቱ ይቀራል ብለህ ነው? አማርኛ ከተሰደደ’ኮ ብዙ ቆየ። የአማርኛ ቋንቋ ዲፓርትመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተዘግቶ፥ ግዕዝ በምዕራባውያን መምህራን Toronto University ውስጥ እንደሚሰጥ አልሰማህም?
ሰምቼቻለሁ፤ ‘ጉድ በል ጐንደርም’ ካልኩ ቆይቻለሁ። አንተ ግን ምን ሆነህ ጠፋህ? ብዙ ጊዜ ሆነን ከተደዋወልን
ያው … ስራ በዝቶባችኋል ብዬ ነው፤ እስረኞች እየፈታችሁ ስታስሩ። ማሰር የለመደ … የሚታሰር ሲያጣ ያሰረውን ፈቶ ያስራል ልበል
የሚታሰር ሲያጣ እራሱን ያስራል ብትል አይሻልም? ወደዚያ እየሄድን ያለ ይመስላል
አሜን ለዚያ ክብር ያብቃን እስቲ! … የሙዚየሙስ ጉዳይ ምን ደረሰ?
አትቸኩል … ለ-display የሚሆኑ ቋሚ እስረኞች እየተመረጡ ነው፤ ልጠቁምህ እንዴ?
ለማን ነው የምትጠቁመኝ?
ለወርቅነህ ወይ ለወርቂቱ
አይሻልህም ለወርቅነሽ? ግን’ኮ እነዚህ ሰዎች ተራራ እና መሬት ማመሳሰል ያውቁበታል። አዶላን “አድዋ” ብለው አስጎብኝተዋቸው ይሆን እንዴ ጠቅላይ ሚንስትሩን ያዞሩባቸው?
አይመስለኝም … እሳቸው አይደለም የአድዋን ኮረብታ፥ የአደይ ሮማንንም ሚጥሚጣ ገና አልረሱም
ሀገር ሻጩንም፣ ሀገር ገዢውንም እንዲህ በጅምላ ኣንድ ላይ “አንሰላስለው” “ወርቅ” ሲሉ አስገረሙኝ እንጂ፥ ነቅሰው አውጥተው፦ አሉላ፣ አብረሃ ብለው ዘርዝረው፥ “ወርቅ” አይደለም “አልማዝ” ቢሉዋቸው ያሳነሷቸው ሆኖ ነበር የሚሰማኝ። ከሁሉም ከሁሉም ግን “መቐሌን አፅዱ!” ያሉት ተመችቶኛል፤ እሳቸውም ቤተ-መንግስቱን ለማፅዳት የቆረጡ ይመስላል
በደንብ አዳምጠሀቸዋል ማለት ነው። እኔማ ሳይገባኝ … “እነሱ አዲስ አበባ እና አካባቢዋን በግሬደር ያፅዱ እንጂ መቐሌ’ማ ማን ኖሮባት ትፅዳ?” ብዬ ነበር
አንተ ልብህ ኬኩ ላይ ነበር መሰለኝ፥ በደንብ አልሰማሀቸውም
ኬክ ስትል … አምባህሻ ጠፍቶ ነው ኬክ የተቆረሰው?
ጎጎ በ-croissant፣ አምባህሻም በ-torta ከተቀየረ ቆየ። አንተ ግን ቀንተህ ነው ወይንስ ጐምጅተህ?
አልቀናሁም። ላለመዋሽት ግን፦ ጠቅላይ ሚንስትሩ በዛ ስል ቢላዋ መሀል-ለ-መሀል ሰንጥቀው ህወሀትን ሲያወጡዋት ስመለከት ፥ ምራቄ መፍሰስ ብቻ ሳይሆን ጥርሴም ሊረግፍ ተነቃንቆ ነበር። ግን እውነት አምባሻው የት ጠፍቶ ነው ኬክ የተቆረጠው?
ሰንደቁ ላይ ተንጠልጠሎ ልበልህ? በነካ እጃቸው ወልቃይትንም ሊይስቆርጡዋቸው ፈልገው ይሆናላ
ወልቃይቴ ላይማ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀዩን መስመር ረግጠው “ቃጤ” ሆነው ነበር
እኔ ሲመስለኝ ግን … ከስብከታቸው ጋር አልጋጠም ብሏቸው ነው ሊፎርሹ የተንገዳገዱት
ማለት?
ማለት’ማ … “ያለን ምርጫ አንድ ሆኖ መደመር ነው!” የሚል ቡራኬ ያላቸው ሚንስትር፥ ማካፈሉን አልወደዱትም … አልፈለጉትም
እና? እንደዚህ ፍልስፍና … ነገ አስመራም ገብተው የባድመ ጉዳይ ቢነሳ፥ “ጥያቄው የልማት ነው፤ ግማሽ ጐናችሁ ትግራይ ነው፤ እንደ ዱሮአችሁ ይሻላችኋል” ብለው ያልፉታል ነው የምትለኝ?
የት ይቀርልሀል! ይከፋሀል?
አንተ በምን አወቅህ?
ክርክር ትወዳለህ አቦ። ግምቴን ነው የነገርኩህ፥ እውነቱን ማወቅ ከፈለክ ደግሞ እሳቸውን ጠይቃቸው
የት አግኝቼ ነው የምጠይቃቸው?
ሚልኒየም አዳራሽ አልነበርክም እንዴ?
ነበርኩ … ምነው? ከላይ በሳተላይት አየኸኝ እንዴ?
አዳራሹን እንደዛ … ልክ እንደ ጽዋ ሞሶብ … ጣሪያ ግድግዳውን ሳይቀር በጨርቅ ጠቅልላችሁት እንኳን እኔ አምላክስ ያይሀል?
በጨርቅ?
ታዲያስ … መቼም የሞተ ሲነሳ ነፍስ ይማር ማለት ወግ ነውና … “ጨርቅ” አይደለ እንዴ ያሉት ያረፉት ጠቅላይ ሚንስትር? ግን እንደው አዳራሹን እንደዛ ቀለም በቀለም አድርጋችሁት ስታጨበጭቡ፥ ድንገት ከአንቀላፉበት ከርሰ ምድር ባነው ቢመለከቷችሁ ምን ይሏችሁ?
“እንኳን ሞትና!” ብለው ይሸበለላሉዋ … ሌላ ምን እንዲሉን ፈለክ? መቼም “እንኳን ተፈጠረና!” አይሉ
ትገርማላችሁ! እሺ እሱስ ይሁን … አሁን ከእዛ ጀግና’ና በኢትዮዽያዊነቱ ከሚኮራ የአፋር ህዝብ መካከል ኣንድ ሰው ጠፍቶ ነው በአፋርኛ ለመዝፈን ሑሴን ዓሊ ከጅቡቲ የመጣው? ሁሉም አፋር እንደ ማፋራ መሐመድ “አልገዛም!” ቢል እንኳ፥ የእስማኤል አሊ ሴሮ ጉሮሮ ለዛች ሰከንድ እንጉርጉሮ አልሆን ብሎ ነው?
ምን አውቅልሃለሁ? ዝግጅቱ ላይ ታደምኩ አልኩህ እንጂ “ደገስኩ” ብዬሀለሁ እኔን የምትጠይቀኝ? ደግሞ ከእዚች ከቅርብ ሀገር ለተጋበዘው ነው የገረመህ? ገና Liu Huan ከቻይና ለ“ቼ-በለው” ይመጣልሀል
ግን አንተ ለምን’ና እንዴት ሄድክ? በ“ተፎካካሪ” ተጋብዘህ ነው ወይንስ ከኢዴፓ ጋር በፎጋሪ ረድፍ ተሰልፈህ?
እኔማ … መቼም ነገር ሳይስቡ ያለ አስተማማኝ ደህንነትና ጥበቃ እንደዛ መላ-ቅጡ በጠፋ አዳራሽ ጠቅላይ ሚንስትሩን አያስቀምጡዋቸውም ብዬ፥ የመንግስት ልዩ ወንጀል ታዛቢ ለመሆን ነበር አካሄዴ። የአምላክ ፈቃድ ሆነና፦ የሻቢያም እጅ፣ የአርበኞችም ግንባር፣ የግንቦት ሰባትም እግር ሳይወነጀል፥ እንዲሁ ብቻ እኔም ጠቅላይ-ሚንስትሩም በስጋት ሟምተን በሰላም ተመለስን
ጥሩ ጠርጥረሃል፤ ለአጋዳይ ሀይሎም ያልራሩ … ለገላጋይ አብይ ይመለሳሉ ብሎ ማሰብ ጅልነት ነው ። እኔ የምልህ ግን፦ ዘንድሮ ባለስልጣኖቹ ስብሰባም፣ ጉብኝትም ሲሄዱ ለብሰው የሚዞሩትን የጥይት መከላከያ ሰደርያ (bulletproof vest) ሜቴክ ነው እንዴ ከአሸዋ የሚሰራው? እሱን ለመደበቅ የሚለብሱት ሰፊ ኮት’ኮ የትልቁን እድር ድንኳን እያስመሰላቸው መጥቷል
ሰውዬ አሁን መተማመኑ ጠፍቷል! አይደለም ከአሸዋ ገና ከኮብል ስቶን ድርድርም ቢሆን አሰርተው … የላሊበላን ደብር መስለው ይሄዱልሀል። በል እኔም ልሒድ … ስራ አለብኝ
የምን ስራ?
ቁፋሮ … አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር “ጉልበታችሁን ቆፍሩበት” ብለውናል
ምንድነው የምትቆፍሩት?
ወርቅ ልበልህ?
ወርቅ?
አዎን ወርቅ ! ምነው ቀናህ?
በወርቅ ያልተቀና በምን ይቀናል?
እልክልሀለኋ
በኣንድ አፍ! ብያለሁ
አይዞህ! የትግል አጋርነታችን ለመቼ ነው? ያገኘነውን ካልተካፈልን?
ታዲያ ወርቁን ከወርቅ-ቅቡ እየለያችሁ ቆፍሩ … ጉልበታችሁን በከንቱ እንዳታደክሙ
እሱን ለእኛ ተወው። በአይን ብቻ ተመልክተን የወርቁንም ካራት (carat) ለመለየት የ27 ኣመት ልምድ አለን
እንደዛ ከሆነስ መልካም። ግን ቁፋሮውን “ስብሀት” ብላችሁ መጀመር እንዳትረሱ … “በረከትን” እንዲሰጣችሁ
ባይሆን እንደዛ ብለህ ምከረን … ባለ 24 ካራቱ ወርቅ እንዲያጋጥመን
በል አንተም የገባህልኝን ቃል እንዳትረሳ
አልረሳም። እንዳውም የሰሞኑን ሹም-ሽረት ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ በስራ ማቆም አድማና በቦይኮት (boycott) ጭንቅላታቸው መዞሩ ስለማይቀር፥ ያኔ በአሳቻ ሰዓት ከሜቴክ እና ከኢንሳ ፕሮጀክት ጣቢያ (site) የተቆፈረ ንፁህ የአድዋ ወርቅ አለ እሱን አስኮበልልሀለሁ። በተሰናበቱት ጠቅላይ ሚንስትር ላይ ግን ተስፋህን ቁረጥ። እሳቸው እንደ አቶ ታምራት ላይኔ “ገዳም ገባሽ አሉ ደብረሊባኖስ … ሰው እየገደሉ ይማራል ወይ ነፍስ? ሰው እየገደሉ ከተማረ ነፍስ … ትቦሽን ዘግቼው ደብረሊባኖስ” የሚሉ ይመስላሉ። እርግጠኛ ነኝ እንኳን በሰላም ተገላገሉ እንጂ፥ ከዚህ ቦኋላ ተፎካካሪ’ም ፎጋሪ’ም ለመሆን ፍላጎት የላቸውም
ኸረ ቃል የገባህልን ይበቁናል። እንዲሁ ልማድ ስለሆነ እንጂ … አይመዘኑ! አይመነዘሩ! ያው ከአቶ ስዬ አብርሃ ጎን ተቀምጠው ጌጥ ይሆናሉ
በል ደህና ሰንብት
አሜን! ደህና እንሰንብት