Post

የሳምንቱ  ስልኬ VII

የሳምንቱ ስልኬ VII

By Admin

    ሄሎ ኣዲስ አበባ         

   ሄሎ መቐሌ ሆይ

    ስልጣንም  እንደ  ____

   አ’ደይ  … ይናፍቃል ወይ!  ብዬ ልጨርስልሃ፤     

    ጥሩ  ነህ  ባክህ

   የሞላውን  አጉድል ”  ሳይሆን “በጐደለ  ሙላ ”  እየተማርን’ኮ  ነው  ያደግነው፤ ረሳኸው  እንዴ?  

    እኔ  ምርጫ (multiple choice) ነበር የምወደው  ባክህ

   ለዛ  ነዋ ቅንድብህ  ያለቀው?

    ታዲያ ሚሚዬን  ልምሰል ብዬ  መሰለህ!  ደግሞ ምርጫ ቦርድ ነው  “ምርጫ የሚጠላና  የሚፈራ  ቅንድባም  ነው”  ያለው? አንተ  እንዴት  ነህ ግን?

   አለነው፥  …  መሐሉን አረጋግተን ዳር ዳሩን እያደራደርነው       

   ማንን  ነው  የምታደራድረው?  አልገባው  ካለ፥  ተጐትቶ  ከወጣው  ከተራራ  ጫፍ  ቁልቁል  ማንደርደር  ነው  እንጂ

   ወንድሜ አንተ ገና ፀበኛው ስርዓት  ላይ ነህ መሰለኝ፥ … እኛ ወደ ፀባየኛው መንግስት ተሸጋግረናል

  እና?!   እብሪተኛ  በእሹሩሩ  ሲተኛ  የት  ነው  ያየኸው? ህዝብ  እኮ  ከቅዬው  እየተፈናቀለ  ዱር  ነው  እየገባ  ያለው፤ ከግብፅ ምድር ወደ ከንዓን  እየተመመ  መሰለህ?  

   እስቲ  ድምፅህን  አስክነው … ብሔራዊ  ሀዘን  ላይ  ነን። ደግሞም  “Ethiopia out of Oromia! ስል  ሰምተኸኛል  እኔ  ላይ የምትፎክረው?

   ነፍስ ይማር  ! ብያለሁ። መልስህም  ግብቶኛል፤  Mr  Pendulum’ን  ጠይቀው  እያልከኝ  ነው?     

   አይሻልህም?  ኮራ … ደልቀቅ ብሎ፦  ካልኩሌሽኑን   የሰራሁት  እኔ  ነኝ …  ሳናስበው  ግን  ህዝቡ ከእኛ ፈጥኖ  ሶዶ፣  ጅጅጋ ይዞት ገባ ”  ይልህ  ይሆናል፤ ማን  ያውቃል

   እስቲ ኦቦ ፔንዱለም’ን … ለቀቅ አድርጉት፥  እንደ  ልጃገረድ  ከንፈር  ስንቱ  ይዛትበት?

   እኔ መች ያዝኩት ወይ ዛትኩበት?  ያለውን ቃል ነው የደገምኩት      

   ነፍሱን  የሽጠ  አንደበቱም የእርሱ አይደለም።  ያዋጡህን   ካልተፋህ   ያጠፉሃል።  ምንም  ይበል  ምን  እኔ  አልቀየመውም።  የ-Jamal Khashoggi’ ን  ደመ ከልብ መሆን ያየ፥  በእዛ  ሰፈር  ሰዎች  ፍላጎት (interest)  አይቀልድም።  ትናንሾቹን አሳዎች አፍ  ማስከፈት  ብቻ ሳይሆን፥  አጥብተው  እንደ  አሳደጉህ፥ አድብተው  እና  ድንበር  ተሻግረው   ያሻቸውን  አድርገው  ትልልቆቹንም አርጃኖዎች  አፍ  ማዘጋት  ይችላሉ። አሜሪካና  ዶናልድ  ትረምፕን  አላየኸም?  ስለዚህ ኦቦ ፔንዱለም’ን  ተዉት፤ ከውስጥም  ከውጭ  አታዋክቡት

   የውጭውን  እንደፈለክ  ተርጉም  ተርትረው፥  የውስጡን  ግን  አንተም ተወን፤ በፀባዩ   መንግስታችን  መዋብ  እንጂ  መዋከብ  ቀርቷል። የድንግል  ከንፈር፣  ዛቻ  ምናምን  እያልክ  ስም  አታጥፋ  

   ጤንነቱ  አደጋ  ላይ ነው  የሚለውን  ልማታዊ-ዛቻ  አልሰማሁም  ለማለት  ነው? ወይንስ  በጉንፋንና  ትኩሳት  ተረጎምከው?  መቼም  ህይወቱ  አደጋ  ላይ  ነው  ሲባል  ካልሰማሁ የምትል  ልበ-እውር  አትመስለኝም።  የሆነው ሆኖ …  እናንተ እንዴት ናችሁ?  የሸገር  ዋስትና … የኣዲስ- አበባ  ወጣቶች ፓርቲ  ምስረታ  ምን  ደረሰልን?

   ፖለቲካ  ፓርቲዎች  ይታጠፉ  እየተባለ  …  ጭራሽ  አንተ  ሌላ  …  

   ታዲያ  እጅህን  አጣምረህ  እንደ  በግ  ትበለታለህ?  መቼም  አራዳ  እንደ  በሬ  ከአራጆቹ   ጋር  መዋል  ከጀመረ  ወራቶች  ተቆጥረዋል 

   ቢሆንስ፥  ኣዲስ  ፓርቲ  ከመመስረት  የተመሰረተው  ውስጥ  መጠቅለል  አይሻልም?  

   የት? ከማን ጋር  ነው የምትጠቀለለው?   ብአዴን/ አዴፓ  ልትለኝ  ባልሆነ  ብቻ   

   ምናለበት?  ወይ  ደግሞ  አንዱ  የተስማማኝ  ውስጥ።  ታውቀኛለህ  በኢትዮጵያውነቴ  የማምን  ኣማራ  ነኝ  እንጂ፥  ኣማራነቴን የማመልክ  ኢትዮጵያዊ  አይደለሁም    

   ብአዴን  እኮ  እብድ  ነው

   ማለት?

   ይሻለዋል  እንጂ  አይድንም             

   አቅጥነው

   ምን  እንዳልገባው  አቅጥነው  ትለኛለህ። ብአዴን  በረታ  ብለን  ቆመን  አጨብጭበን  ገና  ቁጭ  ሳንል፥ ህወሃት   በማን   አለብኝነት  ጎንደር  ገብታ  በሌት -ጨረቃና  በቀትር -ፀሐይ  ከተማ በጥይት  እሩምታ  አሸብራ፣  ቤት  አጋይታ፣  የንፁሀንን  ህይወት  በደርዘን  አጥፍታ  እንዳልተመለሰች፦  “ የኣማራ  ክልል  ሰላም እንዲደፈርስ  ህወሃት  ምክንያት  ተደርጎ ሊወሰድ  አይችልም።  ህወሃት  እያስተዳደረ  ያለው  የትግራይን  ክልል  ነው። አለማም  አጠፋም  መወቀስም  መመስገንም ያለበት  በዛው  በክልሉ  ነው”  ይለናል።  አህያ  ወደ  አመዱ፥  ብአዴንም  ወደ-ፈጣሪው ተመለሰ  ብለን ቁርጣችንን  አውቀን  ስንቀመጥ  ደግሞ  ሌላ  ፉከራና ቀረርቶ ት ይዞ ‘ዘራፍ!’ ይላል

   እና ምን እያልክ ነው?

   እያልኩ  ያለሁትማ  ከገባህ፦  ብአዴን  ለአንተ  ለሸገሬው  አይደለም  እላይ  አጠገቡ  ላለው  ጐንደሬውም  ቢሆን  መታፈሪያ ክብር  ቀርቶ  የክር  ቀበቶ  መሆን  አይችልም። ሲጀመርም  ስምና  ስልጣኑ  የኣማራው  ክልል  እንጂ  የኣማራው  ህዝብ መሪ፣ ተቆርቋሪ  አይደለም።  ጊዜ  ስጣቸው  እንጂ፥  ከሰሜን  አሜሪካ  መልስ  ትንሽ  አየር  ስበው  ያስገርሙኃል። ማለቴ ያስረግሙኃል  

   ምንድነው የሚያስረግሙኝ?

   ከኣማሮች  ይልቅ  የአፄ  ዮሐንስን  አንገት  የሰየፉት  ሱዳኖች  ይሻሉናል  ያሉትን  የትግራይ  ክልልን  ርዕሰ መስተዳድር፥  ይቅርታ እንኳን  ሳያስጠይቋቸው፦  በቀይ ጥለት ጃኖ  አስውበው፣ ሽክ  ቅብርር  ጅንን  አድርገው  ከአፄ  ፋሲል ግንብ ላይ መግለጫ ይሰጡኃል። ያኔ  አቦይ  ስብሃት  ይሻሉኛል!  ሌላው ቢቀር  “የኢትዮጵያ  ህዝብ  ወዳጁን  ጠላት፥  ጠላቱን  ደግሞ ወዳጅ  አድርጓል”  ብልው  ሳይገባቸው ዶክትሩን  ዠልጠውልኛል  ብለህ  አዴፓን  ትራገማለህ

   ዶክተሩ  ኢትዮጵያዊ   ነኝ  ብለው  ካሰቡልህ  ነዋ  ዠለጣው  ዠለጣ  የሚሆነው

   መቼም  የትግራይን  ክልል  እያስተዳደሩ  የታይዋን  ዜጋ  ነኝ  አይሉም     

   አቦ  ምን  እንደሰለቸኝ  ታውቃለህ?  ትግራይ፣  ኣማራ፣  ክልል   ምናምን  የሚል  ነገር  መስማት  … አደከመኝ

   ብቻህን  አይደለህም።  “ክልል”  የሚለው  ቃል  በራሱ  negative vibe የሚፈጥር  ነው

   ምን  እንበለው  ታዲያ?  ግዛት?

   “ትሻልን  ፈትቼ  ትብስን  አገባሁ”  ነው  የሚባለው?  ወዴት ልትነዳን  ነው?

   እውነቴን  እኮ ነው

   ባይሆን  የእገሌ   ጐሳ  ክልል፣  የእንትን  ብሔር  አጥር  የሚለው  ስያሜ  በራሱ  በታዳጊዎቻችን   አእምሮ   ውስጥ  የሚበትነው ዘር  “ብሔርተኛ  ወሰንተኛነት”  ከመሆኑም  አልፎ፥  ዛሬ  ደቡብን  የሚያስነጥሰው  የመካለል  እንፍሎዌንዛ፥  እንደ  ወረርሽኝ  ሁሉንም  አዳርሶ  ሀገሪቷ  76  ቦታ  በብሔር  ሳትቦረቦር፥   አፋር፣   ትግራይ፣  ኣማራ ፣  ደቡብ፣  ኦሮሞ፣  ጉራጌ  ክልል  የሚለው  ስያሜ፦  በቅርስና   በልዩ  የጋራ  ፀጋችን   ቢተካ  ምን  ይለናል?  ድንቅነሽ  ምድር፣  አባይ፣ ሶፍ-ኡመር፣  ካራማራ፣   ምናምን  ምድር  …

   ወይ ጣጣ … እስቲ በቃህ … ከክልል ቀንሰህ  በምድር  ልትደምረን  ነው?  

   ምን ይልሃል?  ብሔርህ  መገለጫው  ማንነት፣ ባህል፣ ውስጥህ  እንጂ  ምድሪቱ – አፈሩ  ላይ አይበቅል።  ቦረናን  ቶራ-ቦራ  ብትለው  እንኳ  ቦረናነትህ   ቀርቶ  Afghan  ልትሆን  ነው?      

   ቆይ  እስቲ  እኔንም  ፈትሸው  “ጅምላ  ጨራሽ  መሳሪያ  ነው”  ብለው  ካላሰሩኝ ፥ ይህንን  ሃሳብህን  ለ-144ኛው  የተወካዮች ምክር  ቤት  ስብሳብ  አቀርብልሃለሁ

   ማን  ደግፎ  ማን  ድምፀ-ተዐቅቦ  እንደሚያደርግ  ባላውቅም  ቢያንስ  ግን 33  ተቃውሞ  የግልህ  ነው። ለማንኛውም  መልካም እድል፤  ደህና ስንብት

   ደህና  እንሰንብት      

Comments are closed.