Post

የሳምንቱ ስልኬ VIII

የሳምንቱ ስልኬ VIII

By Admin

   ሄሎ?

   እንዴት  ውሏል  ወሎ?

   አንተን  ልጠይቅህ  እንጂ፥  እኛ ጋርማ  ስልክና  ኢንተርኔቱ  ብቻ  ሳይሆን  ፖለቲካውም  ተቆርጧል

   አይዞን!  በፈረቃም  ይሁን  በቆረጣ  … ከአሁን  ቦኃላ  ደም  ይፈሳል  እንጂ  ደም  አይነግስም

   እሰይ  የእኔ  አንበሳ!  ፎክር  አንተ .. “ሶፋ ላይ ቁጭ ብለህ”፤  ግን  ደህና  ነህ? ብዙ  ጠፋህ?

   ምን  ላድርግ … ሀዘኑን  በልክ  በልኩ  እስክናደርገው  ነው

   ኧረ ከዛም  በፊት  ጠፍተሃል

   እህህ …  አዎ፤  ያኔ  እንኳን  ጥግ  ይዤ፣  አገጬን  በመዳፌ  ደግፌ  ስታዘብ   ነው

   ምንድነው?  ማንን  ነው  የምትታዘበው?

   የ“ቶቶ”ን  “የሰብአዊ መብት”  እንቶ  ፈንቶ፣  ከእገሌ  ለእገሌ  እየተባለ  ሲወነጨፍ  የነበረውን  የኢሳትን  የምላስ  ሹሌ

   ታዲያ  ምን  ጥግ  አስያዘህ?  ፈርተህ  ነው?  ድሮ እንኳን መሐል  ገብተህ ስትራገጥ  ነበር  የማውቅህ

   ወንድሜ  ይኼ  ቁጭ  ስትል አልፎህ  የሚሔድ  የዱሮ  የህፃንነታችን  አይነት  ሹሌ  እንዳይመስልህ፤  አውሮፓ፣  አሜሪካ፣ ኤሺያ፣  አፍሪካ  ሳይቀር … መሽቶ  የተኛም  ቢሆን  ተቀስቅሶ  ይረገጣል

   እሱስ  ያስፈራል፤  ደግሞስ  አስበኸዋል?  ያንን  በሚያክል  እግር  መረገጥ  የሚያስከትለውን  የአካል-ቅርፅ  ለውጥ?

   ማስፈራት  ሳይሆን  ያሳፍራል። ጐበዝ፦  ለካ  አንገት እንደ  ሐረር ሴት ዳሌ ሲወፍር፥  ለሸሚዝ  ኮሌታ ብቻ  ሳይሆን  ለህሊናም ይጠባል … አዙሮ  ማየት  ይከብዳል። የዚህን  ትውልድ  ስብዕና  አቦይ  ስብሃት ሰረቁት።  ስለዚህም  በየሶሻል ሚዲያው የሐሜት አሹቅ ሲያደቅ፣ የወሬ ጥሬ  ሲቆረጥም መንጋጋውን  ይሸርፋል ብለን ስናማርር ኖረናል። ታዲያ  የዚያኛውን  ዘመን ትውልድ አስተውሎት ማን  ሰልቦት ነው እንዲህ በአደባባይ  በአዝማሪ style “ተቀበል … ድገመው”  እያለ ሲዝራጠጥ የከረመው?  ለ”ትልልቆቹ”  ማነስ ማን   ይከሰስ?  ንጉሰ ነገስቱ  ወይንስ ፕሬዚደንት መንግስቱ?

   ኢሳት፦ የውስጥ ስብሰባውን  ውሎ … እንደ ቴዲ አፍሮ single  “እለቃለሁ” ብሎ፥ ሶሻል ሚዲያው በኣውራ ጣቱ ቆሞ ሲጠብቅ እንደነበር  አስታውሳለሁ

   ሶሻል ሚዲያው ምን  ያድርግ?  የወሬ ቋት ከተገኘ በእግሩ ጣት አይደለም በጭንቅላቱስ ቆሞ ቢጠብቅ  ማን ይፈርድበታል? እንኳን ለእርግጫ፥  ለመርገጫ  ወሬ  እንዴት  እንደሚንጫጫ  እያየህ  አይደል

   ምን ልትል ነው? የምክትል ከንቲባው ጫማ ሐሜት  ቀልቤን አልሳበውም ለማለት ነው?

   አዎን  አልሳበውም። ሐሜቱን  ተመልክቼ  አለፍኩት  እንጂ ቆም ብዬ “እውነት”  “ሀሰት”  ለሚል  ፍርድ  ሰከንድ  ማጥፋት ፍላጎቱ  አልነበረኝም፤  አሁንም የለኝም። ከንቲባው ካዝና  ሰብረው  ያምጡት  casino  ቆምረው፥  እጃቸው  ላይ  ያለው ደም እንጂ  እግራቸው  ላይ  ያለው  ጫማና  ካልሲ  ለእኔ  ቁም-ነገር  አይደለም። ደግሞስ  በሰፋች  አዲስ- አበባ፥  አዳራሹ ሳይጠብ፣ ምግቡ  ሳይቆመጥጥ  ናዝሬት ድረስ  ተሰዶ  ኣራት  ኣምስት  ቀን የሚቆየው  የቢሮዋቸው seminar  እና  workshop  ተረፈ- ምርት  ባይኖረው ለጫማ  የሚሆን  ትርፍ  ሂሳብ  ይታጣበታል  ብዬ  የማስብ  ይመስልሃል? ነው ወይንስ  የናዝሬት ሆቴልና ሎጅ ባለሀብቶች  ‘commission’  የማይቆርጡ  ቆራጥ  ኮሚኒስቶች ናቸው ብለህ  ልትሳደብ  ፈልገህ  ነው?

   እኔ  አልተሳደብኩም!  አንተ  እራስህ  እንደ  ጀመርክ  አንተው እዛው  ጨርሰው …  እኔን  አታነካካኝ

   ምነው ፈራህ?  አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር፦  ጯሂና  አኩራፊ  የሌለውን   እየመረጡ፣  ምስኪን – ደሃውን  ነው  የሚያስሩት  ብለህ  ነው? አይዞህ  … Amnesty  ዝም  ቢል  ኣምስት  ሰውም ቢሆን  ይዤ  እኔ  እጮህልሃለሁ።  ደግሞም   “እውነቱን  ተናግሮ  የመሸበት  ማደር”  ሲባል  አልሰማኽም?  

   የት-አባህ ነው የምታድረው? ማነው  የሚያሳድርህ? ሀገሬው  እራሱ  እንደ  ከረሜላ  ወረቀትና  ላስቲክ  ተጠቅልሎ ውጪ ነው የሚያነጋው።  ባይሆን  “እውነቱን  ተናግሮ  በአቅራቢያው  መታሰር” በል

   ቄሮ ባመጣው”  ለውጥ …  ጠቅላይ  ሚንስትሩና  ከንቲባቸው  ሳይታሰሩማ  እኔ  አልታሰርም

   እነዚህን  ሰዎች  ዛሬም  አልተውካቸውም?

   ምን ብዬ  ልተዋቸው?  ይቅርታ  ሲጠይቁ  ሰማኃቸው  እንዴ?

   አልሰማሁም፤  ግን …

   “ግን”  ምን?  ጨርሰው  እንጂ

   አለ  አይደል … እንደው  ደምግባታቸው  ሲታይ   “አጋዳይ”  አይመስሉም  ብዬ  ነው

   ታዲያ  የእኔ  ደምግባት  ነው “አጋዳይ”  የሚመስለው?

   ምናልባት!  ያውም  ገዳይ!

   ሃሃሃ  … አንተ ሰው አዴፓ ሆንክ እንዴ?  

   ለምን … እንዴት?

   ንጉሱ  ጥላ  ሆንካ    

   ስማ … እኔ ለእውነት  እንጂ  ለማንም  አፈ-ቀላጤ  አልሆንም

   ካልሆንክ  ንገረኛ?  ደም-ግባት  ያለው  ‘ተገዳይ’፥  ደምግባት  የሌለው  ደግሞ  ‘ገዳይ’  ነው  የሚለውን   logic  ከየት  አመጣኸው? የድንግሏ ልጅ፣  የዓለም ቤዛ  ክርስቶስ … ወዝ፣ ደምግባት  የሌለው   ደካማ  መስሎ  ይታይ እንደነበረ  አላነበብክም ? ደግሞስ፦  ከላይ  የተወረወረው  ልክ  እንደ  እኔ  ስልክክ  ያለ  እንጂ  እንደ አንተ  Shriek’ን ይመስል ነበረ?

   ለዛ  እኮ  ነው “ገዳይ”  ነህ  ያልኩህ

   በእርግጥም  አሁን  ገደልኩህ፤  ደምግባታም  የደም ሰው ሊሆን  እንደሚችል  አሳመንኩህ

   እሺ  የእኛ አሳምነው …  ሌላስ ምን አለህ? የምናምንልህ?

   መተማመኑ  ጊዜውን  ይጠብቃል። ይልቅ እንደ  ያኔው  ዛሬም ደግሜ ልምከረህ።  ኣይንና ጆሮ  የስሜት  እንጂ  የእውነት   ህዋሳት  አይደሉምና  ያየኽውን  እና  የሰማኸውን  ሁሉ  ሳትመረምር  እንደ  አምላክ  ቃል “አሜን” ብለህ አትቀበል። በተለይም  በጥርጣሬ  ሞገድ  ስትናወጥ፥  የልብና  የአእምሮህን  ፍርድ አዳምጥ። ልብና  አእምሮህ  በፍርዳቸው  ሲለያዩ  ደግሞ ብኩርናውን  ለአእምሮህ  ስጠው። ይገባኃል የምልህ?

   አበዛኽው እንጂ ገብቶኛል

   “አበዛኽው”  ስትል?

   የማንም በረት ኣፍ፣ ቧንቧ  በሚያፈሰው  ፕሮፓጋንዳ  ክንፍፍፍ  የምል እንከፍ  አድርገህ ሳልከኛ። ያም ይኼም እየመጣ በብርሌ የሚግተን  የኩሬ ውሃ ሆዳችንን  ከመቁረጥ  አልፎ  … ጠጅ  ሆኖ ነፍሳችንን ሞቅ የሚያደርገው አስመሰልከው

   ጠጃም ነገር ነህ! ካልጠፋ ምሳሌ ዘለህ ብርሌ ትጨብጣለህ

   ስድቡን ተወውና  ምክሩን ቀጥል

   ምክሬን ጨርሻለሁ። ጥያቄ ካለህ እጅህን አውጥተህ ጠይቅ

   ለካ አንተ  ከሀገር  ከወጣህ ቆይተኃል፤ ለምርጫ  እንጂ  ለጥያቄ  እጅ  ማውጣት ቀርቷል

   እሺ  እጅህን  አውጥተህ  ምረጠኝ

   አንተን?

   ምን ይልሃል? ከዶዘሩ እከፋለሁ?

   ማናቸው ዶዘሩ?

   ይቅርታ ዶክተሩ ለማለት ፈልጌ ነበር … ፕሮፌሰር ብርሃኑ

   ደሞ ምንህን  አፈረሱት?

   በሚቀጥለው  ስንገናኝ …  ኣስር ጣት ብቻ  ስላለኝ ያፈረሱትን ሳይሆን ያላፈረሱትን  ጥምር  እቆጥርልሃለሁ። በፊት  እንኳን  “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” ብለን ነበር ዝም ያልነው፤ ዘንድሮ ግን የቀን-ጅብ  በቀደደው ቅልብ-ጅብ እስኪወጣ  ድረስ  አንላቀቅም። በል አሁን አታረሳሳኝ  ድምፅህን ስጠኝ

   መዓት እንጂ ሌላ ምን ታመጣልኛለህ ብዬ ድምፄን ልስጥህ?

   መዓትማ አሁንስ መች ቀረልህ?  ብትመርጠኝ ግን ብዙ የህዝቡ ጥያቄዎች እንዲመለሱ አደርግ ነበር

   ለምሳሌ?

   ብርጋዴር  ጄነራል  አሳምነው ጽጌ (ነፍስ ይማር) መቼ  ተገደሉ?

   ሰኞ ነዋ … ከሁለት ቀን ቦኃላ

   ቂል … የነገሩህን  በሙሉ  አሜን  ብለህ  አትቀበል  አላልኩህም? በእለቱ … ቅዳሜ  ለሊት  ተገድሎስ ቢሆን?

   ይኼ የህዝቡ ሳይሆን  በህዝብ  ስም አስርገህ ያስገባኽው ያንተ ጥያቄ  ነው

   ቢሆንስ? እኔ  የህዝብ  ኣካል አይድለሁም?  ጄነራሉ  ቀድመው ተገድለው መንግስት ዜናውን ደብቋል ብዬ አስባለሁ።  ጠቅላይ ሚንስትሩ ተሽቀዳድመው … ኮሚቴ  አደራጅተው  ለሁለት  ቀናት ከፍተኛ  የስብዕና  መመረዝ  ዘመቻ  የከፈቱት  ሆን ብለው የኣማራይቱ  ልጅ  ለጄነራሉ  ያለውን  አክብሮት  ለማበለዝ፣ የግለሰቡን  “ጥፋት”  በማግዘፍ  ሊነሳ  ይችል  የነበረውን  ቁጣ ማደብዘዝ  ፈልገው ነው ብዬ ብጠይቅ በመከላከያ ልታስከስሰኝ  ነው?

   ጄነራል ብርሃኑ ጁላ መከላከያ ደምሳሽ እንጂ ከሳሽ አይደለም ስም አታጥፋ

   አስደምስሰኛ!

   OK … መጀመሪያ  ግን  የ”ህዝቡን”  ጥያቄ   ጨርስ። ህዝብ እንዳይደመሰስ

   ስማ … ትላንትና፦ በደርዘን  በጅምላ  ህዝብ ከፈጁት  ወንጀለኞች ጋር እንኳን ሳይቀር፥ “ይቅር እንባባል” … “ፍቅር ያሸንፋል” … “ቂም እንርሳ፣ እንታረቅ”  ብለው  ከመስበክም  አልፈው  ከ psychic እስከ ካቶሊክ  በኣንድ ኮሚቴ የደመሩት ጠቅላይ ሚንስትር፥ ዛሬ  ለምን  እንዲህ  አምርረው፣  አስክሬን  ከመቃብር  ቆፍረው እያወጡ  ይወቅራሉ  ብለህ  ጠይቀሃል?  ቁጣ፣  ግንፍል ማለታቸውስ  ከ guilty conscience  ሙቀት  የተነሳ ሊሆን  እንደሚችል  ጠርጥረሃል ?

ለሰላምና  ዕርቅ … ከሀገር ሀገር እየበረሩ፣  ከድንበር  ድንበር  እየተሻገሩ፣  ከሱዳን  እስከ  ኤርትራ፣ ከሶማሌ  እስከ  ኬንያ  “ሃሌሉያ!”  የተባለላቸው  ግለሰብ፥  በወሎና  ጎንደር … ያውም በኣንድ  መንደር ሳይታክቱ  ቂም  መኮትኮት ለምን ፈለጉ  ብለህ  ጠይቀኃል? እንደው … ያለ ፌደራል መንግስቱ  የልዩነት-ፈጣሪ  እርሾ  ወንድማማቾቹ  እርስ በእርስ ተገዳደሉ ብንል እንኳ፥ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደሆኑት መሆን ይገባቸው ነበር? ሲሆን ሲሆን መሪ  ናቸውና እሳቸው እራሳቸው፥  አለበለዚያም ቀዳሚ እመቤታችንን  የመሰረት ድንጋይም ባይሆን የስርየት አበባ አሳቅፈው በጎንደሯ  እና  በወሎዋ  መበለት መካከል በማዋል  ከመቃቃር መቃብር  ዕርቅን  መዋጀት  ይሻል ነበር ብለህ ጠይቀሃል?  እንዲያ ቢያደርጉ ኑሮ፦  በዘመናት  ጉልበት  የማይዘም፣ ዝንተ-ዓለም  የሚዘከር  ታላቅ  የስም ሀውልት  በምድር በተከሉ ነበር ብለህስ  አስበሃል?  እዚህም  እዚያም  ቤት መከታ አባት ነው የተነጠቀው፥  የትዳር አጋር ነው የጎደልው፥  የቱን ከማን  ነው የምታበላልጠው?

   ኧረ ባክህ በፈጠረህ!  “ህዝቡ”  ከአቅላይ  ሌላ  ኣንድ  እንኳ  ገንቢ  ጥያቄ  የለውም  እንዴ?

   የሆንክ አዴፓ ነገር ነህ! ፖለቲከኞቹ  “ልዩ-ሀይል”  “ግብረ-ሀይል”  እያሉ  … ከሰው-ሥጋ እስከ  አፈር- ግድግዳ  ሲያፈርሱና  ሲያስፈርሱ  እያየህ  ግንባታ  ከማን  ተምሮ ነው ህዝቡ “ገንቢ”  ጥያቄ  የሚኖረው? ደግሞም  ዘንድሮ  የሚያምሰን  ቅይጥ ኢኮኖሚው  ሳይሆን  ቅይጥ ፖለቲከኞች መሆናቸው ጠፍቶህ ነው?

   ደግሞ  እነማን  ናቸው ቅይጥ ፖለቲከኞቹ?

   ስንቱን ልቁጠርልህ? ባለፈው ኢንጅነር  ታከለ  ኡማ  “ቶቶ”ን  አስመልክቶ  የሰጡትን  አስተያየት  ተመልክቼ፥ ጐሽ! አበጁ!  ምንም እንኳ የእግሩ መረገጫ የዙፋናቸው መቀመጫ መሆኗን ቢያውቁም፥  በድፍረት ከአዲስ-አበባ ከንቲባነት  የአርያምን ወራሽነት መረጡ ብዬ አጭብጭቤ ሳላበቃ

   ሂድ እንግዲህ …

   የት ነው የምሔድልህ?

   ወደ አቅላይነትህ ነዋ

   አስጨርሰኛ መጀመሪያ …

   ስትጨርስ አይደል … እሺ ቀጥል

   Elizabeth Bowser’ን  ጋብዣለሁ  አሉ  

   ታዲያ ምን አለበት? የእራት፣  የአልጋ  አንተን  አያስከፍሉ

   ዝም በል! አዴፓ!  እንዳውም አይገርምህም … ይህቺ  ሴትዮም በላት ሰውዬ “መስቀል”  እሳለማለሁ  ብላ  በለምጥ  ብትወረስ  ወይንም  ደግሞ  “ለሀጢያን የመጣ ለጻድቅ ይተርፋል”  እንደሚባለው፥  የቄሱ  እጅ  እንደ  መቋሚያ  ደርቆ ቢቀር ከአንተና  ከእሳቸው ራስ  አልወርድም

   የእኔስ  ይሁን … እሳቸው ራስ ላይ ግን ማን አስወጥቶህ?  ጠባቂ  እንደቀየሩ  አልሰማኽም  እንዴ?

   ድንቄም! አሉ ወይዘሮ ብርቄ። የትግሬም  በለው  የጉራጌ  ጀበና  ሰባሪ  ጀግና  … ስጋን  ከጦር  እንጂ  ነፍስን  ከጡር ሀሩር የሚያስጥል  መስሎኃል።  ቁጭትና  ፀፀት  በብረት  እንደማይመከት  ጠቅላይ  ሚንስትሩን  ጠይቃቸው … ይነግሩኃል

   በል አሁን ይበቃኃል

   እኔም  የህዝቡን  ጥያቄ  ጨርሻለሁ … ብትፈልግ  አሁን  አስደምስሰኝ

   ጓደኛዬ አይደለህ  ምሬሃለሁ …  ወደ እስር ቀይሬልሃለሁ

   ተባረክ! ታዲያ ሸዋሮቢት፣ ቂሊንጦ ሳይሆን  አዲስ-አበባ ወይ ባህር-ዳር እሰረኝ

   ለምን?

   አፍሪካዊቷ  Jew  ህወሃት  አቶ በረከትን  ከባህር ዳር፣ ጄነራል  ክንፈን  ከአዲስ-አበባ  በሚቀጥለው “መፈንቅለ-መንግስት” አስፈትታ  ስትከንፍ፥  እኔንም  በለስ ይቀናኛል።  እጅ  እግራቸው  በደምና  ጉቦ  ጨቅይቶ  ቢያሟልጭም፥  የታሰሩበትን  ካቴናም ቢሆን  ጨምድጄ አብሬ  መቀሌ መግባቴ  አይቀርም።

   ለማንኛውም  እስከሚቀጥለው  መፈንቅለ-መንግስት  “ሁለት ወርም”  ቢሆን  ትታሰራለህ …  በል ደና እንሰንብት

   አሜን! ደና ሰንብት … መልካም ሰንበት

Comments are closed.