Post

የሳምንቱ ስልኬ XIV

የሳምንቱ ስልኬ XIV

By Admin

   ሄሎ ጤና-ይስጥልኝ

   ጤና-ይስጥልኝ ጎደኛዬ … እንደምን አለህ?

   እንደፈለግነውም ባይሆን እንደፈለጉት አለን እንግዲህ … ነገን ለእርሱ ሰጥተነው

   ለማን? ለአቶ ደመቀ መኮንን ነው ወይንስ … .

   ኤዲያ! “እህል አቅርብ ቢሉት … ባቄላ ይዞ መጣ”  አሉ ወይዘሮ ብርቄ። ለፈጣሪ ነው እንጂ

   ኦ! እንደሱ ከሆነማ … አይዞን! ነገም አይረሳችሁም። አሁንማ  በሁለት ሲኖዶስ ከግራ እና ከቀኝ ልታጣድፉት አይደል … እንዳውም ቶሎ ነው የሚሰማችሁ

   እየቀለድክ ነው?

   ለምንድነው የምቀልደው?  ባይሆን ኣንድ ጥያቄ ልጠይቅህ፦ እነዚያ እርጉሞች ቀኖናውም ላይ ኣንቀፅ 39’ን ጨምረውበታል እንዴ? “የራስን ጳጳስ በራስ መሾም … ሲኖዶስ እስከ  ማቋቋም”  ብለው?

   ምን አውቅልሀለሁ! ቄስ ነኝ እኔን የምትጠይቀኝ?

   ቄስ አይደለህም … ግን ቀስ በል! አትቆጣ። ደግሞ ዛሬ ድምፅህ ወፈረብኝ  … ክረቫትህን አጥብቀህ ነው እንዴ ያሰርከው?

   አንተ ምናለብህ፤ ዘንድሮ … ኣንድ ክራቫት ገዝቶ ከማሰር፥ የኣንድ ክፍለ ከተማ ህዝብ አፍሶ ማሰር እንደሚቀል አላወክም

   ይህን ያህልማ naïve አታድርገኝ። ወላፈኑ እንደ እናንተ ባያቃጥለኝም ግለቱ በደንብ ይሰማኛል። ግን እንዴት ነው ይሄ ነገር … policy እየመሰለ መጣሳ?

   ማለት?

   ማለትማ … ከየቤቱ ሰው እየዘገኑ ኣዋሽ አርባ፣ ሁርሶ ድረስ ወስዶ ማሰር ምንድነው? የመደመር ደብተር፦  “የቤተሰብ ምጣኔ (family planning) የሚሳካው አራርቆ በመውለድ ሳይሆን አሮቆ በማሰር ነው ” ይላል እንዴ?

   እሱን የፃፉትን ወይ ደግሞ ያነበቡትን ብትጠይቃቸው አይሻልም?

   ምነው? አንተ ንባብ ተውክ እንዴ?

   ምን ሆኜ ተዋለሁ?

   ምን አውቃለሁ … ጋዝ እንደ እጣን እያጨሱ ታቦት የሚያጥኑ መናፍቃን … የኣንተ የስጋ ለባሹን ዓይን በአስለቃሽ ጭስ አጥበው ከማሳወር አይመለሱም ብዬ ነዋ

   እሱስ ልክ ብለሃል፤ ለአረጋውያን እና ለህፃናት ያልራሩ  …

   ህፃናት ስትል … ከንቲባዋ ግን እንዲህ በርበሬ እንደምታጥን ክፉ የእንጀራ እናት ህፃናትን በጋዝ የሚያሳጥኑት … ልጆች የላቸውም?

   የቤት ስሙ “ጥቅማ-ጥቅም” የውጭ መጠሪያው ደግሞ “ሙስና” የሚባል አንድ ወጠምሻ ወንድ ልጅ እንዳላቸው አውቃለሁ

   እንዴት ነው ነገሩ …  እንዲህ  ውስጥ ኣዋቂ የሆንከው?  በጋብቻ ነው ወይስ በጉዲፈቻ እኔ ሳልሰማ የተዛመድከው?

   ኧረ የሰው ስም አታጥፋ፤  እኔም ጎረቤት … “የሙስና እናት … ቡና ፈልቷል ኑ ጠጡ “ እያሉ ሲጠሯቸው ሰምቼ ነው

   “ግብር ደርሱዋል ኑ ብሉ እያሉ” አትለኝም 

   “እሳት ካየው ምን ለየው” ይላል የሀገሬ ሰው። አሁን አሁንማ ገና በቴሌቪዥን መስኮት ሳያቸው ደሜ ይፈላ ጀምሯል

   ኧረ በህግ አምላክ! ሴትየዋ እንዳይሰሙህ

  ቢሰሙስ?!

   “ደም ፈልቷል ኑ ጠጡ” ተብለን ነው ብለው እንዳይመጡ ብዬ ነው

   አንተ ምን ታደርግ … እንደ እኛ አልመረረህም!

   የተመኛችሁት ተሰጥቷችሁ ምን ያስመርራችኋል?

   ምንድነው ተመኝተን  የተሰጠን?

   “ሙሴን” ነዋ! ያው ኢትዮጵያን እንደ “ቀይ-ባህር” ከፍለው እያሻገሯችሁ አይደል? ደሞ ገና ከ40 ዓመቱ የበረሃ ጉዞ ኣሥሩን እንኳ ሳታጋምሱ ታጉረመርማላችሁ? ስንዴው እንደሆነ ለውጭ ገበያ ቀርቧል ተብሏል … ያው መናህን እየበላህ ቻለው

   አንተ ሰው እንዴት ነው ለወገኖችህ እንዲህ …? ብቻ ይቅር ይበልህ!

   ይቅር የሚል ከሆነማ እኔን ሳይሆን እናንተን ይቅር ይበላችሁ እንጂ!  

   ምን ኃጢያት ሰርተን ነው ይቅር የሚለን?

   ኣምላክ አዕምሮ በየግል ሰጥቷችሁ በጋራ እንጂ … ኣንድ በኣንድ ማሰብ ባለመቻላችሁ ነዋ። የኢትዮጵያ ህዝብ  ሲገባና ሲወጣ ብቻ ሳይሆን ሲያስብም ግር ብሎ ነው። ድንጋይ ያነሳ ሁሉ መዝሙረኛው ዳዊት፣ ዱላ የጨበጠ ሁሉ ሙሴ ይመስለዋል። ግር ብሎ ወጥቶ … ሐረግ መትቶ፣ ዜማ ቃኝቶ … “ንጉሴ” “አሻጋሪዬ” ሲል ይቀውጠዋል። “ዳዊት” ነው ያለው በወረወረው ድንጋይ፣ “ሙሴ” ሲል ያሞገሰው በጨበጠው ዱላ አናቱን ሲወቃው ነው ከእንቅልፉ የሚነቃው፤ ዳውድና ዳዊትን … ሙሴና ሞሲሳን የሚለየው

   ስብከት ነው ግሳፄ የያዝከው?

   በተመቸህ … ከፈለክም በሁለቱም ውሰደው

   በሁለቱም ውድቅ አድርጌዋለሁ

   Ha ha ha … ለምን?

   ምክንያቱም ባለፈ ነገር ነዋ የምትወቅሰን። አሁን እንኳን ቆሞ የሚራመደው ሰው … ሞቶ ያልተቀበረው በድኑ ድርጅት ብኣዴንም ሳይቀር ባኗል

   ይኸውልህ ሌላው ስህተትህ … እንዳውም ሀጢያትህ

   እንዴት?

   ብኣዴንን እንደ ድርጅት ማሰብህ ነዋ

   ታዲያ ምንድነው?

   ደም! ብኣዴን ደም ነው … የአሽከርነት ደም! የባንዳነት ደም ነው ብኣዴን! ኣንድ ሺህ ጋን ሙሉ ውሃ ብትጠጣ ወይ ኣንድ ሺህ ቀናት ብትጠማ … የደምህን chemical composition ቀይረህ  ደምህን ማቅጠን ወይም ማወፈር እንደማትችል ሁሉ፤ ብኣዴንም ኣንድ ሺህ እድል ብትሰጠው፣ ኣንድ ሺህ ሰው ብትሾም – ብትሽር ባርነቱን አይቀይርም። መለስ ቢሞት (ነፍስ ይማር) – ኃይለማርያም ቢነሳ … ቧ ያለው ቢገባ – ገዱ ቢወጣ …  ብኣዴን ብኣዴን ነው … የባንዳ ዘለላ!

   በዚህ እንኳን አልከራከርህም። አሁንስ ፖለቲካው እያስጠላኝ መጣ … 

   እና ምን መሆን ፈለክ? Investor?

   ገንዘብ ካበደርከኝ? ከስሙ ጀምሮ ወርቅ ወርቅ የሆነ የኢንቨስትመንት መስክ ነበረኝ

   ለምሳሌ?

  ተው ይቅርብኝ … በሌላ ሰው እንዳታስቀድመኝ

   ኣንድ እንኳ … ለስንብት

  አንተ ካልክ መቼም “ታማኝ የጫማ ቀለም” … አይበቃህም?

   ለዛሬ ይበቃል። በል የከርሞ ሰው ይበለን … መልካም ሰንብት!

   አሜን! አንተም ሰላም ሰንብት!

Comments are closed.