Post

የሳምንቱ ስልኬ XV

የሳምንቱ ስልኬ XV

By Admin

   ሄሎ – ጤና ይስጥልኝ

   ጤና ይስጥልኝ ሰውየው … እንዴት ይዞሃል?

   ይመስገን ነው! እንደ ፋኖ ምርኮኛ አሽሞኑሙኖ ይዞኛል

   ልክ ብለሃል። ፋኖ ምርኮኛና እስረኛ አያያዙ ሸጋ ነው። ከብልፅግና ሚንስትር … ፋኖ እጅ ውስጥ የገባ ምርኮኛ ወታደር ይሻላል

ለመማረክ አስበሃል መሰለኝ። ዛሬ ሳትከራከረኝ ከሃሳቤ ጋር ቶሎ ተስማማህ

  ለምን እክራከርሃለሁ? ብልፅግና የሚንስትሩን ቤተሰብና ፍራሽ እንደ ኮብል stone  መንገድ ላይ አውጥቶ ሲያነጥፍ እያየሁ፤ በኣንፃሩ ደግሞ ፋኖ የትግራይ ኮረኔሎችን ከእስር ቤት አውጥቶ አንቀባሮ ወደ ቤተሰባቸው ሲመልስ እየሰማሁ ለምን ልከራከርህ?  

   ስለ ምርኮኛ አያያዝ ስናወራ ምን ትዝ አለኝ መሰለህ … ባለፈው ህወሃት ‘ፖለቲካ ልሰራ’ ብላ ነው መሰለኝ ‘የምርኮኛውን ልደት አከበርኩ!’ የሚል ዜና ይዛ መጣች። እኔም ተገርሜ ምኑ እድለኛ ሰው ነው … በተባረከ ቀን ተውልዶ ልደቱም በምርኮ የሚከበርለት ብዬ በማሰብ ቀኑን ከኣውሮፓ ወደ ሃበሻ ቀመር ለመመለስ ማስላት ጀመርኩ

   እና? የዓመቱ አቡነ-አረጋዊ ላይ ዋለ?

   እሱማ ቢሆን በተሻለ! የካቲት 11 ሆኖ አረፈው እንጂ

   ሠላም በጨነገፈበት ቀን የማህፀንን ድንበር ጥሶ ወጥቶ ታዲያ ምኑን ነው ‘በተባረከ ቀን የተወለደ’ የምትለኝ? ሳይሞት መማረኩም አምላክ  መሃሪ ሆኖ ነው

ሠላም በጨነገፈበት’ ነው ያልከው? የተውለደውንስ ቢሆን መቼ አሳደጋችሁት?

   ማለት?

   ያው የሰላም ሚንስትሩን ዘብጥያ ወረወራችኋቸው አይደል

   ህምምምም … ሰሞኑን ወይዘሮ ብርቄን ጋር ደውለህ ነበር እንዴ?

   ኧረ አልደወልኩም፥ ምነው?

   ንግግራችሁ ተመሳስሎብኝ ነው

   እንዴት?

   ባለፈው ሰሞን ወደ ሰፈር ስንሄድ ሚኒ-ባስ ውስጥ ተገናኘንና … ሰው እንዳይሰማ ብዬ በለሆሳስ ‘ታዬን እኮ አሰሩት’ አልኳቸው ፥ ድንግጥ ብለው ‘ውይ ልጄን! እኔን ይሰረኝ! ፋኖ ነበር?’ አሉኝ  ጮኸው። አሁንም በዝግታ ‘ኧረ አልነበረም፤ ታዬ ደንደአን’ኮ ነው የምሎት … የሠላም ሚንስትሩን’ ስላቸው፥ ‘ኡይ የት አውቄው ብለህ?  እኔን ከሚያስረኝ እርሱን ይፍታው። ግን እንዲያው … ለየለት በለኛ! የሰላሙን ሚንስትር ካሰሩት ሰላማንችንን ማን ሊጠብቅ ነው እንግዲህ?’ ሲሉ…  ከኋላ ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረ ኣንድ የኣዲስ ኣባባን ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሰ የኦህዴድ ወታደር ድንገት ወሬያችን መሃል ገብቶ … ‘አይዞት ማዘር አያስቡ፥ ብልፅግና አለ’ አላቸው

   ሃሃሃ … ‘ድንቄም!’ አላሉም ወይዘሮ ብርቄ?

  እሷማ መች ትቀራለች። አንገታቸውን ብቻ በከፊል ወደ ኋላ አዙረው ‘ይኑር ልጄ’ ብለው ከመለሱለት ቦኃላ … ለእኔው በለሆሳስ ‘ድንቄም ብልፅግና! ንቦች አለቁና ዝንቦች ንብ ሆኑ’ አሉኝ። ፈገግ እንደማለት ስል ‘ምነው? ንቡ ቀፎው ውስጥ ገብቶ ተቀርቅሮ ነው እንጂ ገና አላለቀም ብለህ ነው?’ አሉኝ እሳቸውም ፈገግ እያሉ።

   ወይዘሮ ብርቄ እኮ ነገር የገባቸው ናቸው

   ነገር የማይገባው ማን አለ?

   ብዙ አለ … ለምሳሌ አንተ

   እንዴት?! ለመሳደብ ነው እንዴ ከርመህ ከርመህ የደወልከው?

   ቀስ በል እንጂ … እኔ መች ተሳደብኩ?

   ይኽው ‘ነገር አይገባህም‘ እያልከኝ

   ታዲያ ይኼ ስድብ ነው?

   እና ምንድነው?

   ነገር አይገባህም ማለትኮ ‘ነገረኛ አይደለህም’ ማለት ነው። እንዴት ነው ነገሩ … እኔ ነኝ ወይስ አንተ ኣማርኛ የጠፋን?

   ኣንተ ይጠፋህ ይሆናል እንጂ እኔማ ሀገሬ ውስጥ እየኖርኩ እንዴት ነው አማርኛ የሚጠፋኝ?

   እኔ ምን አውቃለሁ? ከሽማግሌ እስከ ቄስ ገበዙ ‘ሆደ-ሰፊ ሁኑ!’ እያላችሁ ስትመክሩ ትውሉና ሰው ሆደ-ሰፊ ሲሆን ‘ሆዳም!’ ብላችሁ ትሳደባላችሁ። ሓበሻ እኮ …

   ሓበሻን ለቀቅ አድርገው! ፈረንጅ ሃገር ስትኖር ፈረንጅ የሆንክ መሰለህ?

   እኔ መቼ ፈረንጅ ነኝ አልኩ?

   እና ታዲያ?

   በል ተወው።  በስንት ጊዜያችን ተገናኝተን ሰዓታችንን ለምን በጭቅጭቅ እንጨርሰው

   እንደዛ በል። መጥፋትህ ሲገርመኝ …

   እኔ እንኳን የጠፋሁት አየሩን በጄትና በሄሊኮፕተር ጩኸት ስትረብሹት ስለነበር ደውዬ ከምንደነቋቆር አንደኛዬን ስትረጋጉ ብደውል መደማመጥ እንችላለን ብዬ ነው

   የምን ጄትና ሄሊኮፕተር ነው የምታወራው?

   የ UAE ነዋ

   የት ነበር ‘ስልብ ባሪያ በጌታው እንትን ይፎክራል’ የሚል ነገር ያነበብኩት?

   መደመር መጽሓፍ ላይ ይሆን? ደራሲው በቅርቡ ከ’እንትን’ ጋር ስለተያያዘው ‘ሸለፈት’ ምናምን ሲሉ የሰማኋቸው መስሎኛል

   ሳይሆን አይቀርም፤ የባሪያን ሥነ-ባህሪ የሚያውቅ ባሪያ ነው

   እኔ የምልህ ግን … እንዴት ነው ዘንድሮ  ከከረሜላ ይልቅ የቦንብ እና የጥይት ዋጋ ረከሰ ማለት ነው?

   ማለት?

   ማለትማ … ሙሽሮች የሰርጋቸውን ዕለት የሚያደምቁት  ከረሜላ በሚበትኑ ህፃናት ሳይሆን ቦንብ በሚያዘንቡ የጦር ጀቶች ሆነ ብዬ ነው

   ገና ምን አይተህ! በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ በችጋር ጅራፍ ሥጋው ተገሽልጦ ወድቆ በአጥንቱ ደርቆ እየሄደ  ‘ለጦር መሣሪያ መግዣ የሚውል ፲ ቢሊዮን ዶላር አለኝ’ ብሎ በሚመፃደቅ ሀገር … ትንሽ ከታገስክ … ታንክ የሙሽራ መኪና ሆኖ  አበባና ፊኛ  ታስሮበት ታያለህ

   ያኔ ነበራ … ለሙሽራው ታንክ ማጀቢያ ነው ብለህ ZU-23 ይዘህ ገብተህ ‘አሃይ ሎጋው!’ ማለት። እስቲ ግን ለማንኛውም የሙሽሮቹን መጨረሻ ተከታተልልኝ

   ምነው? ክርስትና ስጡኝ ብለህ ልትጠይቅ ነው?

   አሁን ወይዘሮ ብርቄ ቢሰሙህ ኑሮ ‘ድንቄም ክርስትና’ ይሉህ ነበር

   እና?

   ሰውየው የነኩት ይቅርና  ታግለው ያጠለቁትም ቃልኪዳን አልፀናም ብዬ ነው እንጂ። ለማንኛውም የአብይና የኢሳያስ ሳይሆን የኣብረሃምና የሣራ ጋብቻ ያድርግላቸው ብዬ በምርቃት ብንለያይስ?

   እንደዛ ይሻላል። በል ሰላም ያክርምህ

   አሜን አብሮ ሰላም ያክርመን!

Comments are closed.