Post

የሳምንቱ ስልኬ

የሳምንቱ ስልኬ

By Admin

ምን ማለት ነው ይሄ?

ምኑ?

እንዴት ምኑ ትለኛለህ?

ምን ልበልህ ታዲያ?

በቃ ነገር አለሙን ተውከው? ማንበብ-ማየት አቆምክ?

ማንበብም ማየትም አላቆምኩም፤ አንተ ግን ስለምን እንደምታወራ አልገባኝም

ስለ ሀገርህን ጉድ ነዋ! ጮኸ ጓደኛዪ

የሀገሬ ጉድ ከህዝቧ ቁጥር በልጦ አሁን ሰለየትኛው ጉድ እንደምታወራ በምን አውቄ ልመልስልህ?

ከዚህ በላይ ምን ጉድ አለ?

አንተ ሰው ኮከብ ቆጥሬ የአንተን ጉድ ለመተንበይ እኔ ጋር ገና ቀን ነው፤ ሰማይ ላይ የሚታየኝ አንድም ኮከብ የለም።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣት ዜጐች ስራ-አጥ ሆነው ባዶ ሆዳቸውን ከረሃብ ጋር እየተላፉ ውለው በሚያድሩባት ከተማ፡ ከ5ሺህ ማይል በላይ ተጉዞ፡ የውጭ ዜጋ አምጥቶ መቅጠር ምን ይባላል? ሲለኝ ሰለምን አንደሚያወራ ገባኝ። የንዴቱ ትኩሳት በድምፁ ጩኸት ውስጥ አልፎ ጆሮዪን አጋለው

ምን አውቃለሁ፦ ንቀት ይሆናላ – ‘ምን ታመጣላችሁ’ ተብለን

እንዴት ምን ታመጣላችሁ? ባለቤት አይደለንም? ሀገራዊ በሆነ ሀብታችን እንደ ዜጋ ተቆጥረን የቅድሚያ መብት ሊሰጠን አይገባም? ነው ወይስ የአብዛኛው የአየር-መንገዱ ሰራተኞች ቋንቋ ትግርኛ ስለሆነ እሱም በክልል 1 ስር ተጠቃለለ?

ባለቤት ብንሆን፣ ቢያገባን ኖሮማ አየር-መንገዱን ከህግና ስርዓት ውጪ አቶ ተዎልደ በተዋልዶ ሲያስተዳደሩት፡ የአይን ሰረዝ – የግንባር ላይ ጭረት እንደ ሸቀጥ ባር ኮድ (bar code) እየተነበበ ሃምሳ ፐርሰንት የትኬት ቅናሽ፣ መቶ ፐርሰንት የታክስ ምህረት ሲደረግ ለምን ብለን በጠየቅን ነበር። ግን አልሆነም።

ይኸው ዛሬ ኢትዮዽያዊ እህቴን የዓረብ ቆረቆራም እየደፈረ ቤሩት (Beirut) አውራ ጎዳና ላይ እንደ ጉድፍ ይጥላታል፤ አቶ ተዎልደ የቻይናዋን ወጣት እንደ ልዕልት ደረት-ትከሻዋን በብሔራዊ ኩራታችን አርማ አጊጦ፡ በአዲስ አበባ አውራ-ጎዳና በማርቸዲስ ሰርቪስ ያንፈላስሳታል። ምስኪን የሀገሬ ልጅ ለግርድና በተሰደደችበት ምድር አልጋዪን በደንብ አላነጠፍሽም ያለ አሳዳሪ ከፎቅ ላይ ወርውሮ ቁልቁል ይፈጠፍጣታል፤ አቶ ተዎልደ ቻይናዊ የእድሜ እኩያዋን ኩሎ እና አሳምሮ ከፎቅ በላይ … በላይ በላይ … ከዛም በላይ አንቀባሮ ያበራታል። ታዲያ እነሱ ምን ያድርጉ? ኢትዮጵያዊው ስደተኛ በደርባን ሳውዝ-አፍሪካ ቀበቶ ሽጠህ አደርክ ተብሎ ስጋው እንደ ጧፍ ሰም ነዶ ይቀልጣል፤ አቶ ተዎልደ በድርብ ደሞዝ የቀጠሩት ቻይናዊ የበረራ አስተናጋጅ ዶላሩ በዝቶበት የገንዘብ ቦርሳው ዚፕ ይተረተራል፣ ማንገቻ ቀበቶው ይበጠሳል …

ሃሎ?

ሃሎ?

አለህ? አልኩኝ ዝምታው ስለበዛ

የት ልሂድልህ? አሁንም ንዴቱ አልበረደለትም መሰለኝ ቀና ነገር አያስመልሰውም

ስማ? አለኝ

አቤት

እስቲ አሁን እኛ ቻይናዎችን የማናውቃቸው ሆነን ነው የሀገራቸውን ቋንቋ የሚያወራ የበረራ አስተናጋጅ መቅጠራችን የተሻለ ገበያ እንዲኖረን ያስችለናል የምንባለው? በገበያ ስርዓት’ኮ የደንበኛ ስነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ፀባይ ጥናት (customer behavioral analysis) የሚባል ነገር አለ

አውቃለሁ

ታዲያ? ቻይና 1 ዩኣን (Yuan) ቀንስለት እንጂ እንግሊዝኛ አይደለም ግዕዝ ብታወራ ጉዳይ አይሰጠውም። ኣስራ-አንድ ሰዓት በማንደሪን ቋንቋ ጙኦዩአ (Guoyue) እየዘፈንክ፣ በአንዳች ምትሀት በመስኮት ወጥተህ ከደመና ደመና እንደ ሚዳቋ እየዘለልክ ብታበረው እንኳን፡ የዋጋ አማራጭ ካለው አፍንጫህን ላስ ብሎህ ነው የሚሄደው። ለትርፍና ለጥቅም ነፍስ ያላወቁ ህፃናትን ወተት ነው እያለ መርዝ የሚያስቅም ነጋዴና ኢንቨስተር፡ ዛሬ ለአቶ ተዎልደ ሲባል ግብረገባዊ ሆኖ -ከገንዘብ ይልቅ ቋንቋውን አስቀድሞ እንደ ሆላንድ ከብት ሊታለብ – ያ ነው የተፈለገው?

እኔ ምን አውቃለሁ? ባይሆን ጉዳይህ በአግባቡ እንዲታይ ጥያቄህን በትግርኛ አስተርጉመህ በፖስታ አድራሻ 1755 ላከው

እየቀልድክ ነው?

ምን ላድርግ፥ ከአቶ ተዎልደ ተምሬ’ኮ ነው። እሳቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ስራ-አጥ ላይ ሲቀልዱ እኔ አንድ ጓደኛዪ ላይ ብቀልድ ምን ይለኛል?

ቆይ ግን እስከዛሬ ድረስ አየር-መንገዱ ትርፋማ ሲሆን፦ ለፈረንሳዊው ተሳፋሪ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሆስተስ፣ ለዓረቡ ደግሞ ዓረብኛ የሚያወራ አስተናጋጅ እየቀጠረ ነበር እንዴ? ቻይናዎቹ በኢትዮዽያ አየር መንገድ ውስጥ የሚኖራቸው ቆይታ የሰአታት እንጂ የአመታት ነው? መሬት ተመርተው ጎጆ ይወጣሉ? በአየር ላይ የሚበረው ሁሉ እንግሊዝኛ አያወራ፤ ምንድነው እነሱን ይህን ያህል ልዩ ያደርጋቸው?

ምናልባት የበረራው ሰዓት ረጅም ስለሆነ አሰልቺ እንዳይሆን፡ የብሔር-ብሔረሰቦችን መብት እና ህገ-መንግስቱን አንቀጽ 39’ን ጨምሮ በአስተርጉዋሚ ሊያሰጠኑዋቸው አስበው ይሆናላ፦ አልኩ ቀልዱ የጓደኛዪን ንዴት ለማብረድ የታለመ ቢሆንም አልተሳካም

ይኼ ነው መልስህ? ብሎ አምባረቀ

ታዲያ፥ ቋንቋው አስፈላጊ ከሆነ ለምን ዜጎቻችን ተቀጥረው መሰረታዊውን መግባቢያ አይማሩትም? ስንል፦ ኢትዮዽያውያኑ ቻይንኛውን ሀ-ብለው ጀምረው ተምረው ሊሞክሩት አይችሉም፤ መቶ ዓመት ያወሩትም እንግሊዝኛ አያምርባቸውም፤ ሲናገሩት አክሰንት (accent) አለው ተባልን

ማን ነው ያለው? አቶ ተዎልደ ናቸው?

አይደሉም። ግን ያው ተዋልዶ ነው

እንዴት ያለ ንቀት ነው? በቁልቋል እሾህ የቆሰለ ምላስ ኣንድ መቶ አመት አይደለም ኣንድ ሺህ ዘመን ተምሮ እንግሊዝኛ አስተካክሎ ባያወራ አይገርምም። እንዲህ ብሎ የአንድን ህዝብ ብሩህ አእምሮ በጅምላ ማሳነስ ግን ከማስገረምም አልፎ በጣም ያማል

ትክክል ብለሃል!

እንደው ቀጠለ ጓደኛዪ ለተጓዦቹ ልማዳዊና ምቹ (homely environment) ማቅረብ ከተፈለገ እንኳን ከደሃ ህዝብ ላይ የስራ ዕድልን ነጥቆ ለባዕድ ከመሸለም ይልቅ ሌላ አማራጭ ይጠፋል?

ለምሳሌ?

ለምሳሌማ … ለምን አስተናጋጁዋን ሳይሆን መስተንገዶውን ቻይንኛ አያደርገውም?

ማለት? አልገባኝም?

በቃ’አ! ከፈለገ ስፓጌቲውን በኑድል (noodle)፣ ማንኪያ ሹካወን በቾብ ስቲክ (chopstick) …

አሃ የሻዩንም ሲኒ ቀይሮ በጣባ ያቅርብለት ማለትህ ነው?

ለእኔ ሲል ለምን በእንስራ አይሰጠውም! እኔ የማወራው ስለ ብሔራዊ ክብር፣ ስለ ህዝብ ጥቅም ነው – ይገባሃል?

ታዲያ’ኮ እነዚህ ሰዎች ብሔርተኞች እንጂ ብሔራዊ አይደሉም። ምን አድርጉ ነው የምትላቸው? አልኩት እንደ መሳቅ እየቃጣኝ

መማር አለባቸዋ! ማወቅ! ወገንን ማስቀደም! ወደ ኢትዮዽያዊነት መመለስ! አሁን ትክክል ገባልኝ … ደስ አለኝ፤ ብድሬን እንድመልስ ቀዳዳ ሰጠኝ።

ስማ- እኔን ማንበብ-ማየት አቆምክ ስትል አንተ እራስህ ማሰብ-ማገናዘብ ተስኖህ አረፍከው? አያቱ ከቱርክ፣ አባቱ ከጣልያን ተጣምሮ ወገኑን ስያደማ የነበረ ባንዳ፥ እሱ እራሱ በአረብ ገለብ እየተጋለበ ሀገር፣ ህዝብ ሲሽጥ እያየኸው እንዴ ተደርጎ ነው ይማር – ይመለስ የምትለው? ነፍዘሃል ልበል?

ታዲያ ምን ይሻላል?

ነገርኩህ! እነሱን የሀገር ፍቅር አስተምሮ ወደ ኢትዮዽያዊነት ከማምጣት፡ ሉሲፈርን አመንኩሶ ወደ መንግስተ-ሰማይ መመለስ ይቀላል። የባንዳ አጋንንት በጥይት እንጂ በትምህርት፣ በፀበል ወይንም በፀሎት አይለቅም

ተቀብያለሁ! አንድ ደግሞ በጣም ያናደደኝን ታሪክ ልንገርህ። ስለዚሁ ጉዳይ ከአንድ ጓደኛዪ ጋር ካፌ ውስጥ ቁጭ ብለን ስናወራ – አንዲት ወጣት ከጀርባዪ ከትትት ብላ ስትስቅ ሰማሁና ዞር ስል ‘ስለ ቻይናዎቹ ሆስተሶች ነው የምታወሩት?’ አለችኝ በግድ በሚሞላቀቅ አማርኛ። በአንገቴ ንቅናቄ አዎንታዪን አሳውቄያት፡ እሷንና አብረዋት የተቀመጡትን ሁለት ጓደኞቿን ተራ በተራ ቃኘኋቸው። እንደ ግንደ-ቆርቁር ወፍ እንጨት እየፈለጡበት አድገው ነው መሰለኝ ያንጋደዱት፡ የሶስቱም ጥርስ ከላይም ከታችም በብረት (braces) ተወጥሮ ታስሯል። ‘ውይ ስታሳዝኑ ስልጣኔና ቢዝነስ ገና አልገባችሁም ማለት ነው። ቻይኖቹኮ ተቀጥረው በሃገራችን ወስጥ በሚኖራቸው ቆይታ ለሃገራችን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ማለት ናቸው’ አለችኝ። በንዴት አይኔ ተጎልጉሎ ግማሹ ከመክደኛው ቢወጣም ባለጊዜ ናት መሰለኝ እሷ ማንን ፈርታ? ቀጠለች ‘ያአ! አታውቅም እንዴ? ለሆቴል ለምግብ እህህ … ደግሞ’ ሰትል ትቻት ፊቴን ወደ ጓደኛዪ መልሼ ወሬያችንን ቀጠልን።

አታስጨርሳትም ነበር?

ለምንድነው የማስጨረሳት? አሁን ማን ይሙት ቻይና ነው ዶላር ከፍሎ ሆቴል ውስጥ ሩም (room) ይዞ የሚተኛው? ኣንድ ክፍል ቤት ተከራይቶ እንደ ሙሽራ ኬክ ኣንዱ በኣንዱ ላይ ተነባብሮ ለኣሥር ያድራታል አንጂ?

አንተ ሰው በል ይበቃሃል

እህሳ? ውሽት ነው?

ውሽት አይደለም

ታዲያ? ለምንድነው የሚበቃኝ?

ማለቴ … እኔም፣ አንተም፣ የኢትዮዽያ ህዝብም የእነዚህ ሰዎች ቅጥር ሀገራዊ ይዘት ያለው ምንም አይነት ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅም እንደሌለው ይገባናል። በአንድ በኩል ቻይናዎቹ እንግሊዝኛ አይችሉም እየተባልን፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚኛዎቹ አቀላጥፈው ከተናገሩት ሀገራቸው ውስጥ ያላቸውን ልዩ እና አድሎአዊ መብት (privilege) ይጠቁምሃል። የቅጥሩን ድር እና ማግ ስትተረትረው፦ የማን ልጆች እንደሆኑ፣ ለአቶ ተዎልደና ለመሰሎቻቸው ምን ውለታ መመለስ ከሚችል ከየትኛው የህብረተሰብ ክፍል ወይንም ቤተሰብ እንደተመዘዙ ትደርስበታለህ

በአጭር ተረት ‘እዛም ቤት እሳት አለ’ ነው የምትለኝ?

ታዲያ – እንኳን ወዲያ ከ5000 ማይል በላይ ተርቆ አይደለም፡ እዚሁ አይንህ ስር የሚተወነውን ድራማ እያየኸው – ቻይናዎቹ የተቀጠሩት ተወዳድረው ነው ብትለኝ እኔኑ እራሴን በቻይንኛ ታስቀኛለህ

እሱስ ልክ ነህ፤ መቼም ጉንጭሸ ላይ የማርያም ምልክት አለ እያለ የሚጥል መስሪያ ቤት ያለ አንዳች የማወራረጃ ሒሳብ ፊቱዋ ላይ ዓይን የሌለባትን ሆስተስ አርድጎ አይቀጥርም

በል ባክህ አደከምከኝ። አንድ ከዛው ከአየር መንገድ ሰሞኑን የበረረ ትኩስ ዜና ልንገርህና ይብቃን

ምን ልትለኝ ነው ደግሞ? ህንዶቹ ስላኮረፉ በቦርዱ ታቀፉ?

ይሻል ነበር። አየር መንገዱ ጠቅላላ የዱቲ ፍሪ’ውን (duty free) መደብር ለኣንድ የክልል 1 ተዋልዶ በጨረታ ይቅርታ በጨረቃ ሸለመው – በመቶ ኣስር የትርፍ ስሌት ድምር።

እንዲህ ነው እንጂ ከፀደቁ አይቀር! … ህዝባችን ግን ምን ነካው? ፖለቲከኞቻችን … ተቃዋሚ ነን – የሀገር የወገን ተቆርቋሪዎች ነን የሚሉን … ?

እስቲ አትቸኩል

እውነት … አሁን ነው ከልቤ መሆን የተመኝሁት

ምን መሆን? ሲስቅ ለማለት የፈለገው ገባኝ

ምነው? ሽብረተኛ አጥፍቶ-ጠፊ ልትለኝ ነው?

ኸረ አንተ ሁን እንጂ እኔ ምን በወጣኝ፤ እንዲያውም አልምቶ ጠፊ፣ ለፍልፎ-አስለፍላፊ ብዪ እሸልምሃለሁ እንጂ።

Comments are closed.