Post

የባልቻ ልጆች

የባልቻ ልጆች

By Admin

የአዲስ አበባ ከተማን ማዝመን” የሚል ሽፋን የለበሰውን የህወሀትን ስሌታዊ ብልፅግና ከደጅ ወጥተው በአደባባይ የተቃወሙትን የኦሮሞ ተወላጅ ወጣቶች – ጀግኖች! የደጅ አዝማች ባልቻ ልጆች! ብያቸዋለሁ። የኦሮሞ ማህበረሰብ በታሪኩ ባንዳዎችን ሲዋጋ እንጂ ለባንዳዎች አጋፋሪ ሆኖ የፈፀመው አሳፋሪ ታሪክ የለም።

እነዚህ ወጣቶች ላለፉት 25 አመታት በዘረኛው የህወሀት መንግስት በውዴታ ግዴታ የተጋቱትን የዘረኝነት መርዝ አርክሰው፡ ዛሬ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በጋራ ለመቆም ያሳዩት አንድነትና ውህደት “ባልቻ ” የሚለውን የኦሮምኛ ቃል ትርጓሜ ደግሜ እንዳሰምርበት አድርጓኛል። ዳግም በቆረጠ መንፋስ የተጀመረው የለውጥ ፍላጎት ባነሰ መስዋዕትነትና ባጠረ የጊዜ ገደብ ከወደቡ ለማድረስ ከተፈለገ፡ ደቡብ ከሰሜኑ – ምስራቅ ከምዕራቡ አንድ ሆኖ ተላምዶ የጋለውን ትግል ሳይበርድ፣ ሳይቀዘቅዝ ባለበት ትኩሳት ወደፊት መግፋት የግድ ይላል።

ትግል እንቅስቃሴ ነው። እንቅስቃሴ ደግሞ የራሱ የሆነ ሳይንሳዊና መርህ አለው። ይህንን የምለው፦ በተለምዶ Newton’s first law (the law of inertia) የሚባለውን የፊዚክስ ህግ በማስታውስ ነው። አንድ የቆመን አካል እንቅስቃሴ ለማስጀመር ብዙ ሀይልና ጉልበት ይጠይቃል። ለዚህም ደግሞ ከ1997 እስከ 2008 ያባከነው ኣስራ-አንድ አመታትና በዜጐች እስር፣ ስደትና ግድያ የከፈልነው ታላቅ ዋጋ በቂ ማስረጃ ነው። ይህ ብቻም ሳይሆን፥ ዛሬ እንደ ሰደድ እሳት መሮጥ የጀመረው አመፅ፡ ነገ በውጫዊ አካል ያለውዴታው በድንገት ቢቆም፡ በትግሉ ባለቤቶች ላይ የሚያደርሰው አፀፋዊ የበቀል እርምጃ መጠነ ሰፊና እጅግ የከፋ እንደሚሆን አያጠራጥርም።  

አሁን ያለውን የነፃነት ትግል በእንቅስቃሴ ላይ በማቆየት ረገድ ከሀገር ውጭና በሀገር ወስጥ ያሉ የፖለቲካ ምሁሮች፣ የጥበብ ሰዎች (ዘፋኞች፣ ገጣሚዎች፣ ፀሀፍትና ደራስያን) እንዲሁም ተማሪዎች የራሳቸው የሆነ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል ብዪ አምናለሁ። በተለምዶ ከምንጠቀምባቸው ህዝብን የማነቃቂያ እና የማነቃነቂያ ስልቶች በተጨማሪም፡ በግፍ የተገደሉ የሰላማዊ ሰለፈኞችን ምስልና ስም የያዙ አልባሳትን (ቲ-ሸርት፣ ካኔተራ፣ ወዘተ) ማሳተምና ማሰራጨት፣ ሁኔታዎች በሚፈጥሩት አጋጣሚዎች ሁሉ በመጠቀም ክልላዊውም ሆነ በክልሉ ውስጥ ያለው ሃገራዊው ሰንደቅዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲወለበለብ መጠየቅና አመቺም ሆኖ ሲገኝ ማስገደድ – ትግሉ እስትንፋሱን ጠብቆ እንዲራመድ ከማስቻሉም ባሻገር ለዚህ ሰብዓዊ ዓላማ በመቆም ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድ የተጨፈጨፉትን ዜጎች ለማስታውስ ይጠቅማል።

ሰሞኑን አደባባይ ወጥተው የተመለከትናቸው በዕድሜያቸው ብዙም ያልገፉ የኣንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም፡ ህግን ከማያከብሩ “ህግ አስከባሪዎች” ጋር ፊት ለፊት ገጥሞ ሰለባ ከመሆን፡ ታፍሰው የታሰሩት ጓደኞቻቸው እስኪፈቱ ድረስ በትምህርት ቤቶቻቸው ቅጥር ግቢ ለመገኘት እንጂ ወደ መማሪያ ክፍሎቻቸው ለመግባት እምቢተኛ በመሆን፣ የመለያ ልብሶቻቸውን (uniforms) – ሸሚዝ፣ ሹራብ፣ ኮት ገልብጠው በመልበስና ሌሎች ከዕድሜያቸው ታናሽነት ጋር የሚመጣጠኑ ተቋውሞችን በማከናወን፡ ለፋሽስታዊው መንግስት ስርዓት አለመታዘዛቸውን በማሳየት የዚህ ታላቅ ማህበረሰባዊና ሀገራዊ ትግል ባለድርሻነታቸውን ማስመስከር ይችላሉ። ለዘረኛው የወያኔ መንግስት ባለስልጣናት፡ መተኪያ ከሌለውና ዋጋ ከማይወጣለት የኦሮሞ ህዝብ ደም ይልቅ፡ ስድስት ብር የከፈሉባት ግማሽ ሊትር የኤደን ሚንራል ውሃ የበለጠ ክብር አላት። ይህንንም ሃቅ፦ የስምንት ዓመት ህፃን ልጅን ጨምሮ በሰባ የሚቆጠሩ የወጣት እና አዛውንቶችን ደም ያለ አግባብ በግፍና በገፍ ማፍሰስ አስመስክረውታል።

ዛሬ ህወሀት ኢህአዴግ በሚል ሽፋን የፈጠረው ግንደ-ዘውድ አንጓው ተለያይቷል። ያም ሆኖ ግን፡ ደም ያደለባቸው የወያኔ ወናፍ፣ ወይፈኖች – ሀቅን ተቀብሎ ስልጣንን ከመልቀቅ ህዝብን ማስተላለቅ ምርጫቸው ሆኗል። ትላንት እንዳልተሳካ ሁሉ ወደፊትም አይሳካም እንጂ! አቶ ጌታቸው ረዳ፡ ማህበረሰብን ከማህበረሰብ ጋር በማጋጨት ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈፀም የቀሰቀሱባት የአደባባይ ኢንትራሃምዌ (Interahamwe) ስብከትም፡ ለአብዛኛው ኢትዮዽያዊ በተለይም ደግሞ ድልድይ አፍራሽ”  የሚለውን የወል ገላጭ ስማቸውን ለምናስታውስ ዜጎች ይህቺን ይህቺን ለMr. Bean ብለን የምናልፋት የህወሀት ቀልድ-ተረት ናት።

ኣንድ ብሔረሰብ ከሌላው ብሔረሰብ ጋር እንዳይገናኝ ማህበራዊ ድልድዩን ማፈረስ፣ ኣንድ እምነት ከሌላው እምነት ጋር በመቻቻል አብሮ እንዳያድር ሀይማኖታዊ ግድብ (ግንብ) ማቆም የህወሀት ፖለቲካ መሀንዲሶች ልዩ ችሎታ ነው። በዚህ አጋጣሚ ሳልናገር ማለፍ የማልፈልገው እውነታ ቢኖር – የትግራይ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ነፃ አውጪ የሚፈልግባት ኣስራ አንደኛዋ ሠዓት ላይ ደርሷል። በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያሉ የማህበረሰቡ ተወላጆች፡ ትዝብት-ዝምታቸውን አደፍርሰው በሰፋ መልኩ መውጣት-መናገር ካልቻሉ፡ “ነፃ አወጣንህ” ያሉት ዘረኞች ከኢትዮዽያዊነቱ አውጥተው፣ ከወገኑ አራርቀው ለ”ነፃ እርምጃ” እያሰናዱት መሆኑን በአጽንዎት መገንዘብ ያስፈልጋል።

ህወሀት መክኗል! የከፍተኛ አመራሩም ራስ ምታት ይኸው ነው። ድርጅቱን በመካነ-መቃብሩ በማሳረፍ የተፈፀመውን ግፍና በደል በወደቀ ሰንደቁ ለመሸፈን መሞከር – በወንጀል የወዛ ማንነትን ማራቆት ነው። ያኔ ደግሞ ግዙፍ ዳሌና አርብ፡ ለጓዳ በርጩማ እንጂ ለፍርድ ወንበር አይሰፋም። ይህም ሳይሆን ቀርቶ፦ ወያኔ የወደቀ ሰንደቁን ከግፍ ሰለባዎቹ ላይ በመግፈፍ እንደገና ለማንሳት ገድል ሳይሆን ገድ ቢኖረው እንኳ፥ ደም ቀጥኖ በደም-ስር ውስጥ ሲሸከሙት እንጂ፡ በግፍ ፈሶ ከአካል ውጭ ሲረጋ ከብረት ይከብዳልና በንፁሀን ደም የወየበውን የወያኔን የትግል በርኖስ (ሰንደቅ) ተሸክሞ የሚቆም ጠንካራ ዘንግ የለም። በዚህም ተሄደ በዚያ- ከኢትዮዽያ ህዝብ ፍርድ ለማምለጥ የመለስ እንጂ የማርያም መንገድ አይኖርም!

Comments are closed.