
By Admin
ልምድ ነውና ኣዲስ ዜና ፍለጋ ከድረ-ገፅ ወደ ድረ- ገፅ “ስፈናጠር” ድንገት “ቦርከና” ውስጥ ጥልቅ አልኩ። ቦርከና ወንዙ ሳይሆን የዜና መረቡ። ከሁለት ቀናት በፊት borkena.com “የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)” ምስረታን አስመልክቶ ያቀረበው የዜና ዘገባ መዝጊያ ምዕራፍ፥ ትንሽ አረፍ ብዬ ይቺን አጭር ጽሑፍና ቪዲዮ እንዳዘጋጅ አደረገኝ።
Yet, there are voices who seem to be somewhat skeptical if the party could be different in a good way from the other parties that we see in Ethiopia. Those who are even more critical question the consciousness of the leadership simply by pointing to the logo they picked as an emblem of the party which is “double-headed eagle” ; they say the traditional emblem in history has always been a lion.
ምንጭ ጽሑፍ ፦ National Movement of Amhara party officially founded in Bahir Dar
የእራሴን ትርጉም ስሰጠውም፦ ይሁንና ንቅናቄው (አብን) ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታዮት ሌሎች ድርጅቶች በተለየ በጎ አስተዋፆኦ ይኖረዋል ብለው ለማሰብ የሚቸገሩ ግለሰቦች አሉ። ከዚህም አልፎ ጠንከር ባለ መልኩ የሚተቹት ደግሞ፦ ድርጅቱ ከልማዳዊው የአንበሳ ምስል ውጪ እንደ አርማ የመረጠውን ባለ መንታ ጭንቅላት ንስር በቀላል ማስረጃነት በመጠቆም፥ የድርጅቱ አመራር ያላቸውን ብስለትና ንቃት በደማቅ የጥያቄ ምልክት ስር ያስቀምጡታል፤ ይላል።
ስለ አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር ብስለትና ክንዋኔ ዛሬ ላይ ሆኖ መናገርም ሆነ መፃፍ ይከብዳል። ያንን በይደር እናቆየውና፥ የዛሬ የድርጅት አርማ የነገ ተግባር መለኪያ ሚዛን መሆን ይችላልን? ስንል መጠየቅ ግን እንችላለን።
ፖለቲካ ጥንቆላ ሆኖ አያውቅም። የድርጅት አርማ እንደ ገድ (ዕድል) መተንበያ ምልክት (Zodiac) እየቆጠሩ፦ አንተ Leo ነህ አንተ ደግሞ Scorpio እያሉ፥ ትላንት ስለተወለደው አብን ትንቢት ለመናገር መሞከር ተራ ጠንቋይነት እንጂ በሳል ተቺነት ሊሆን አይችልም። ጉብዝና በስራ እንጂ በስም እና በአርማ መች ሆኖ ያውቅና?
ይህንን ስል፦ ድሮ ልጆች እያለን በየሰፈራችን በሚደረግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የምንመሰርተው ቡድን ትዝ አለኝ። ያኔ ገና ለጋ የሆነው እግራችን፡ በአየር የተነፋ ኳስ አክርሮ ሦስት ሜትር እንኳ አርቆ መምታት ሳይችል፥ ለቡድናችን የምንሰጠው ስም ግን፡ መረብ – በጣሽ ነበር። ድንቄም ነው ያሉት ወይዘሮ ብርቄ። እና አሁን ” አርማችሁን አንበሳ ካላደረጋችሁት በስተቀር ጥቃት መካች ኣማራ መሆን አትችሉም ” መባሉ ለምን ይሆን? አብን ፦ የዘረኝነትን ማንቁርት ነክሶ፣ የአድሎን አክርካሪ ለመስበር የሚያበቃ ጠንካራ መንጋጋ እንዳለው ለማሳየት አርማው ግዴታ ባለ-ዳልጋ እንስሳ መሆን አለበትን?
አርማ ወይንም ሰንደቅዓላማቸው ላይ ክርስቶስ ከተሰቀለበት መስቀል የገዘፈ ግማድ አጋድመው ወዲህ ወዲያ የሚሉት ሀጉራትና ድርጅቶችስ ቢሆኑ፥ አይደለም ከሰው ከዲያብሎስ ብሰው በክፋትና ተንኮል ሲራቀቁ፣ በፍቅርና ሰላም ሲሳለቁ እንጂ ከመለያ አርማቸው ጋር የሚታረቅ ምን በጎ ምግባር ሲከውኑ ተመልክተን እናውቃለን? ችቦና የገብስ ዘላላ እንደ ድርጅት አርማ ይዘውልን የመጡት ህወሀቶችስ ቢሆኑ፥ በጥይትና ረሃብ ረፍርፈው የቀበሩት ህዝብ እንጂ አጭደው የከመሩት አዝመራ የቱ ነው? ሃያ-ሰባት ዓመት ሙሉ የምናጭደው ስንዴ ሳይሆን ስንክሳር ነው። ችቦውስ ቢሆን መች ብርሃን ሆነን? አመት ሙሉ ከተማ ገጠሩ ጨለማ ነው። በምሽት ብርሃን የሚታየው እነ እንትና ሲጋራ ሲለኩሱ አለበለዚያም ጎጆ፣ መስጂድ፣ ወይ ደግሞ ቤተክርስቲያን ሲያቃጥሉ ነው።
ነገሩ ገርሞኝ ይህን ያህል ተጓዝኩ እንጂ፥ አብን አርማውን ንስርም ሆነ አንበሳ ቢያደርገው ልዩነቱ ለእኔ አይታየኝም። ለምን ቢባል አንበሳና ንስር ግዛታቸው እንጂ ልዩ አገዛዛቸው ኣንድ ነው፤ ድንገት ብቅ ሲሉ ያም በሰማይ – ይሄም በምድር ፍጥረትን ያርዳሉ። ሁለቱም በወሰናቸው አፄዎች ናቸው። እንዳውም ንስር ግዛቱን አልፎና አስፍቶ፥ ህዋውን ብቻ ሳይሆን ባህር የብሱንም ጭምር በፍርሃት ያምሰዋል። ውሃ ጠልቆ ከአሳ እስከ እባብ ያለ መንጠቆ ነጥቆ ሽቅብ ይመጥቃል። ጥጃን ከገደል ላይ ወርውሮ፣ ተኩላና ቀበሮን ምድር ለምድር አባርሮ – እንደ ቆሎ ዘግኖ ወደ ግዛቱ ይሰግራል። ይህ ባለ ክንፍ ፈረስ በሙሉ ሀይሉ ህዋውን ሲቀዝፍ፦ ሰማይ ቀውጢ ይሆናል፣ ደመና እንደ ትቢያ ይቦናል።
አብን፦ ከአንበሳ ይልቅ የምድርና የህዋ ንጉስ የሆነውን ንስር መለያው በማድረጉ በፍርሃት የሚነስረው አንጃ ካለ ደግሞ፥ ይህንን ጉልበታም ጋላቢ ለመግራትና ለመግታት እርሱም በተራው ድርጅት መስርቶ፣ አርማውንም ቢሻው የቃጫ ልጓም፣ ቢሻውም የነሃስ ሰንሰለት አድርጎ ይምጣ! ከተሳካ። እውነቱ ግን፦ ንስር አፈጣጠሩ- ፈጣሪውን ብቻ እንጂ ተፈጥሮንና ፍጥረትን እንዳይፈራ ሆኖ ነው። ንስር፦ የሰላም አለቃ፣ ድንቅ መካር፣ ሀያል- ተዋጊም የሆነው የአብ መቀመጫ ዙፋን (ኪሩቤል) ነውና።
አብንን የምስራች ብያለሁ! ዛሬም እንደ ትላንቱ ደግሜ ማሳሰብ የምወደው ሐቅ ደግሞ ይህንን ነው፦ ለሦስት አስርት ዓመታት በኣንድ ዘረኛ መንግስት የተገዛነው፥ በእኛ – በተገዢዎቹ ድክመት እንጂ በእነርሱ – በገዢዎቻችን ጥንካሬና ጉልበት አይደለም! ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት፦ የምንገነባው ውስጣዊ ድካም እንጂ የምናፈርሰው ውጫዊ (የጠላት) ብርታት የለም!
ንስር ያየ አንበሳን አይቷል፤ አንበሳንም ያየ ንስርን ተመልክቷል። ይህን እውነት የሚጠራጠር ካለም፥ ከዚህ በታች ያለው ተንቃሳቃሽ ምስል ተፈርዶበታል።