
By Admin
መብላት፣ መበ’ላት እና እርስ-በርስ መባላት እንጂ ፍቅር እና መተሳሰብ የአራዊት ስርዓት እንዳይደለ ጠንቅቄ አውቃለሁ። እናም እነዚህ የጫካ ሰዎች መውደድ – መዋደድን ማወቅ ቢሳናቸው እንኳ ጥላቻን መለየት እንዴት ይከብዳቸዋል? ያደጉበት፣ የኖሩት፣ ከ 17 አመት በላይ የዘመሩት ዴዚዴራታ አይደለምን?
ከመደብር እስከ ጉልት-መደብ፥ ከህፃናት ትምህርት ቤት እስከ ትላልቅ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተዘጉ። መንገድ፣ ቤት ፈረሰ! ንብረት ነደደ – ጨሰ! ከዚያም አልፎ ህይወት አለፈ – ተቀጠፈ። ታዲያ እነዚህ ሰዎች አለምወደዳቸው፣ አለመፈለጋቸው የሚገባቸው መቼ ነው? የኢትዮዽያ ህዝብ ለስርዓቱ ያለውን ጥላቻ፣ እምቢተኝነቱን፣ ለለውጥም ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ምን ቀረውና ምን ያድርግ? የግዴታ ትግራይ ተጉዞ፦ የአክሱምን ሀውልት አፍርሶ ታሪክ መናድ አለበት? ለዛ አይነት ተግባር ደግሞ “ወላይታውም ” ይሁን ሌላው “የአክሱም ሀውልት ለእኔ ምኔ ነው? ” የሚል እብሪተኛ ዋልጌ አይመስለኝም።
የህዝብ ጥላቻ እኮ “አብዮት” አይደለም አይቀለበስም፤ “ፊውዳሊዝም “ አይደለም አይደመሰስም። ከደም፣ አጥንት እና ሥጋ ጋር አብሮ የተቃኘ፥ ከነፍስ ጋር የተቆራኘ የማይጠፋ ነበልባላዊ ስሜት ነው። በለውጥ ነፋስ – ያ ካልሆነም – በደም ባህር እንጂ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማይከስም፣ የማይዋጅ።
ሲራራ ነጋዴ ከሀገር ሀገር፣ ከድንበር ድንበር ያለድካም የሚዞረው፥ ተደላድሎ በሚቀመጥበት ፈረስ ሳይሆን በሰለለ እግሩ ጡንቻ ይመስለዋል። ህወሀትም እንዲሁ ናት፥ አቅም – ጉልበቷን ትረሳለች። በድል ማግስት፦ የድል አጋሯን ንቃ፣ የዕድል ገዷን ዘንግታ – በከበሮ “አይበልናንዶ ” ይቀናታል። ያ ግን ዛሬ ታሪክ ሆኗል። የሚሸከማትም፣ የምታሸክመውም ከጐኗ ሸሽተው፦ “አይበልናንዶ ” በ “ወይ ነዶ! ” ሊተካ ጥቂት ምዕራፍ ብቻ ቀርተዋል። እንደው የማይሆነው ሆኖ የስልጣን ኮረቻዋን በሞት-ሽረት ትግል ከከአቶ ኃይለማርያም ወደ አቶ ደመቀ ጫንቃ ብታሻግር እንኳ፥ ላይድን የቆሰለ መቀመጫዋን ከፈረስ ወደ አህያ ጀርባ ማውረድ እንጂ ሌላ ምን ሊረባ?
አዎ ህወሀት አብቅቶላታል! አቅም ጉልበት አጥታለች። ለመደራደር አይደለም ለመግደርደር በማያፈናፍናት ሽምቀቆ ታንቃለች። ዛሬ ላይ ሆኖ ከዚህ ዘረኛ እና ጎሳ-ገነን ስርዓት ጋር በጋራ መንበር ለመዳኘት የሚያስብ ማንኛውም አካል ቢኖር ደግሞ፥ በግፍ በተገደሉ ዜጎች ደም አፈር እያቦካ የስልጣን እርከን የሚሰራ ጥቅመኛ እንጂ ለህዝብ ፍትህ፣ “ለሀገር ሰላም” የቆመ ፖለቲከኛ አይደለም። ድርድር ካስፈለገም “ከሰማይ በታች ባለ ማንኛውም ነገር ” ሳይሆን ከከርሰ-ምድር በታች ባለ መቃብርና ገሃነም ብቻ መሆን ይገባዋል!
ዛሬ እምቢተኝነቱ እንደ ንጋት ጀንበር ጨረር ከዳር እስከ ዳር እየደመቀ፣ እየከረረ መጥቷል። “ተኝቷል” ለማለት ባልደፍርም አድብቷል ለምለው ከተማም ጥቂት ወግ ይኖረኛል። የባርነት መልካም የለውም። ያም ሆኖ አንድ ታላቅ ህዝብ በገዛ ሀገሩ፣ በእናት ምድሩ ላይ በጥቂቶች ተገዝቶ፥ በባርነት ቀንበር ተጠምዶ ጀርባው ሲላጥ፣ ትከሻው ሲጎብጥ ግን የባርነት ትርጉሙ እጅግ ይከፋል – ይከረፋል! ክቡር ሰብዓዊ ስብዕናን ከእንስሳ አሳንሶ ያዋርዳል!
እንደ እኔ ግላዊ ፍልስፍና የሰውን ልጅ ህያው የሚያደርገው እስትንፋሱ ሳይሆን መብቱ ነው። በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ ነፍስ ማደሪያ ሰማያዊ መብቱ እንጂ ምድራዊ ስጋው አይደለም። ያለ መብት የሚኖር ህይወት ከሞት አይሻልምና። ከአምላክ የተሰጣትን ሰብዓዊ መብት የተነፈገች ነፍስ እና ቀፎ-አልባ ንብ ሁለቱም አንድ ናቸው። ከንቱ ኖረው ፣ በከንቱ የሚያልፉ! በአጭር ቃል፦ ረብ-አልባ ዝንብ!
ዛሬ መብትህን ነጥቆ ሲሄድ ቸል ያልከው፥ ነገ ለነፍስህ መመለሱ የማይቀር ነው። ለመብት መዋደቅ ደግሞ ሽብርተኝነት፣ አጥፍቶ መጥፋት ሳይሆን፥ ሰማዕትነት፣ አሳርፎ ማረፍ ነው። ስለዚህ ይበቃል! ደግሞም በቅቶናል!